1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ከሰሞኑ ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተር ሥርዓት ብልሽት ጀርባ ያሉ እውነታዎች

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016

በቅርቡ በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ በተከሰተ ችግር በመላው ዓለም በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ መስተጓጎል አስከትሎ ነበር።ችግሩን ፈጥሯል የተባለው ክራውድስትራይክ የተባለው የቴክኖሎጅ ኩባንያ ለችግሩ ይቅርታ ጠይቆ ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን ገልጿል። ለመሆኑ ችግሩ እንዴት ተከሰተ? ያስከተለው ጉዳት እና መፍትሄውስ?

https://p.dw.com/p/4ix2J
በቅርቡ በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው የመረጃ ቴክኖሎጂ ብልሽት የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከሎችን፣ ሆስፒታሎችን፣የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ፣ባንኮችን እና የገበያ ማዕከሎችን የመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማትን  ስራ  በማስተጓጎል በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን ለእንግልት ዳርጓል ።
በቅርቡ በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው የመረጃ ቴክኖሎጂ ብልሽት የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከሎችን፣ ሆስፒታሎችን፣የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ፣ባንኮችን እና የገበያ ማዕከሎችን የመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማትን  ስራ  በማስተጓጎል በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን ለእንግልት ዳርጓል ።ምስል Markus Scholz/dpa/picture alliance

ከሰሞኑ ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተር ሥርዓት ብልሽት ጀርባ ያሉ እውነታዎች

«ሰማያዊ  የሞት  ስክሪን»/Blue Screen of Death / እየተባለ የሚጠራው በቅርቡ በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው የመረጃ ቴክኖሎጂ ብልሽት በመላው ዓለም የፈጠረው ትርምስ ቀላል አልነበረም።ብልሽቱ የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከሎችን፣ ሆስፒታሎችን፣የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ፣ባንኮችን እና የገበያ ማዕከሎችን የመሳሰሉ ወሳኝ ተቋማትን  ስራ  በማስተጓጎል በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን ለእንግልት ዳርጓል ። በጀርመን ኪል የሽሊዝቪግ ሆልሽታይን የዩንቨርሲቲ ሆስፒታል የአስተዳደር ቦርድ ሊቀመንበር የን ሾልዝ በጤና ተቋማት ያጋጠመውን  ችግር በወቅቱ እንዲህ ነበር የገለፁት።
«መገመት ትችላለህ? በሆስፒታሎች ውስጥ የትኛው በሽተኛ የት እንደተኛ እታውቅም ? እና ምን ዓይነት መድሃኒት እየደሚወስድ ? ምን ዓይነት ቀዶ ጥገና እንደታቀደ?  ይህ ሁሉ መረጃ በቀላሉ አይገኝም።»ብለዋል።
በፈረንሳይ አንድ የአየር ጉዟቸው በመሰረዙ መጉላላት የገጠማቸው መንገደኛ ደግሞ፤ «ትንሽ የሚያስጨንቀው ግን አንድ ኩባንያ በዓለምአቀፍ ኢኮኖሚ እና በፕላኔቷ ህይወት ላይ እንዲህ አይነት ተጽዕኖ ማሳደሩ ነው።» ብለዋል።ክራውድስትራይክ /CrowdStrike/ የተባለው በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰራው የአሜሪካ የቴክኖሎጅ ኩባንያ በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒውተሮች ላይ የተከሰተው ችግር የተፈጠረው ኮምፒተሮችን ከጥቃቶች ለመከላከል በተሠራው ፀረ-ቫይረስ መተግበሪያ ላይ የማዘመን (update) ስራ ባደረገበት ጊዜ መሆኑን አምኗል።የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ እንደሚሉት የሰሞኑ ችግር ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የማያውቅ ነው።

በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው ሙሉ በሙሉ የሚባል የስርዓት ብልሽት ተጽዕኖ በአሜሪካ ብቻ ወደ 8.5 ሚሊዮን የሚጠጉ በዊንዶው  የሚሰሩ መሳሪያዎችን ከስራ ያስተጓጎለ ሲሆን፤ ማይክሮሶፍትን ሳይጨምር  ወደ  500 ኩባንያዎች  ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስባቸው  ተገምቷል።
በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው ሙሉ በሙሉ የሚባል የስርዓት ብልሽት ተጽዕኖ በአሜሪካ ብቻ ወደ 8.5 ሚሊዮን የሚጠጉ በዊንዶው  የሚሰሩ መሳሪያዎችን ከስራ ያስተጓጎለ ሲሆን፤ ማይክሮሶፍትን ሳይጨምር  ወደ  500 ኩባንያዎች  ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስባቸው  ተገምቷል።ምስል Chris Young/The Canadian Press via AP/picture alliance

ለመሆኑ የተከሰተው ችግር በትክክል ምንድነው? ባለሙያው እንደሚሉት ከደህንነት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች በተለያዩ ጊዚያት የሚከሰቱ  የደህንነት ክፍተቶችን በማጣራት እነዚያን ክፍተቶች ለመሙላት  የሚያስችሉ የደህንነት ጥበቃን በሁለት አይነት መንገድ የማዘመን ስራ ይሰራሉ። አንደኛው የማዘመኛ /አፕዴት/ መንገድ አውቶማቲክ ወይም የሰዎች ጣልቃገብነት ሳይኖር በቀጥታ የሚደረግ  ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ «ማኑዋል» ወይም ሰዎች ዕቅድ ይዘው የሚሰሩት መሆኑን ይገልፃሉ።ይህም እንደየ ችግሩ አጣዳፊነት ይወሰናል ብለዋል።ባለሙያው እንደሚሉት ከማይክሮ ሶፍት ጋር በደህንነት ጥበቃ ላይ የሚሰራው ክራውድስትራይክ በአብዛኛው ከዊንዶስ ጋር የተያያዙ ማዘመኛዎችን አውቶማቲክ በሆነ መንገድ ነበር የሰራው።ይህም ድርጅቶች በስራ ላይ እያሉ የተደረገ በመሆኑ ችግሩ የተፈጠረው አዲሱ የደህንነት መጠበቂያ የማዘመን ሂደት ቀደም ሲል  ከነበሩ ሌሎች የኮምፒዩተር ስርዓቶች ጋር ባለመጣጣም  መሆኑን ያስረዳሉ።

አቶ ይግረማቸው እሸቱ፤የሶፍትዌር መሀንዲስ
አቶ ይግረማቸው እሸቱ፤የሶፍትዌር መሀንዲስምስል Privat

በዚህ ሁኔታ ማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒዩተሮች ላይ ያጋጠመው ሙሉ በሙሉ የሚባል የስርዓት ብልሽት ተጽዕኖ በአሜሪካ ብቻ ወደ 8.5 ሚሊዮን የሚጠጉ በዊንዶው  የሚሰሩ መሳሪያዎችን ከስራ ያስተጓጎለ ሲሆን፤ ማይክሮሶፍትን ሳይጨምር  ወደ  500 ኩባንያዎች  ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስባቸው  ተገምቷል።የ«ዊንዶ 7»ተጠቃሚዎች ስጋት
ከዚህ በተጨማሪ የመረጃ መንታፊዎች የክራውድ ስትራይክ ደንበኞችን ኢላማ ለማድረግ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀማቸውም እየተነገረ ነው።ይህንን ተከትሎ የክራውድ ስትራይክ ዋና ስራ አስኪያጅ ጆርጅ ኩርዝ   ችግሩን ለመቅረፍ ኩባንያው ማስተካከያ በማደረግ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ ለተፈጠረው ችግር እና ለደንበኞች መጉላላት  ይቅርታ ጠይቀዋል።
«ላደረስነው ተጽዕኖ ከልብ እናዝናለን። በደንበኞች፣ በተጓዦች፣ ድርጅቶቻችንን  ጨምሮ  በዚህ ለተጎዳ ማንኛውም ሰው።ስለዚህ አሁን ጉዳዩ ምን እንደሆነ እውቀናል። ችግሩን እየፈታን ነው ። ፈትተናልም። አሁን እዚያ ያሉት ስርዓቶች መልሰው እያገገሙ ነው።»በማለት ገልፀዋል።

ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ደህንነት ፕሮግራም እና የሳይበር አካዳሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ስኮት ዋይት ለዩኤስኤ ቱዴይ እንደገለፁት ኩባንያዎቹ ያስተናገዱት   የብልሽት ችግር የተከሰተው  በቴክኖሎጅ ኩባንያው ትክክለኛ ቅድመ ትንተና ባለመደረጉ ነው።የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ በሀሳቡ ይስማማሉ።እሳቸው እንደሚሉት ኩባንያው የማዘመን ስራውን ከመስራቱ በፊት ሙከራ ማድረግ እንዲሁም ከደንበኞች ጋር ቀድሞ መነጋገር ነበረበት።

በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒውተሮች ላይ የተከሰተው ችግር የተፈጠረው ክራውድስትራይክ  የተባለው በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰራው የአሜሪካ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ፀረ-ቫይረስ መተግበሪያ ላይ የማዘመን  ስራ ባደረገበት ጊዜ ነው።
በማይክሮሶፍት ዊንዶ ኮምፒውተሮች ላይ የተከሰተው ችግር የተፈጠረው ክራውድስትራይክ የተባለው በሳይበር ደህንነት ላይ የሚሰራው የአሜሪካ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ፀረ-ቫይረስ መተግበሪያ ላይ የማዘመን ስራ ባደረገበት ጊዜ ነው።ምስል Haven Daley/AP Photo/picture alliance

የሰሞኑ ችግር በአብዛኛው በተቋማት ኮምፒዩተሮች ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ከፍተኛ የኮምፒዩተር ሥርዓት ብልሽት የገጠማት ሀገር ደግሞ አውስትራሊያ ነች።ይህም ባለሙያው እንደሚሉት ዊንዶን ብቻ ከመጠቀም የመጣ ነው።ከዚህ አንፃር  በተጠቃሚዎች በኩል አንድ አይነት የኦፐሬቲንግ ሲስተም ከመጠቀም ይልቅ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም መፍትሄ መሆኑን ኢንጅነር ይግረማቸው ያስረዳሉ።የኮምፒተር ጠበብትና የመገናኛ ሥነ ቴክኒክ
ከጎርጎሪያኑ  2017 ወዲህ ከፍተኛው ነው የተባለው ይህ የኮምፒዩተር ሥርዓት ብልሽት፤ ምንም እንኳ  በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ የተመለሰ ቢሆንም፤እያንዳንዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ከዲጅታል ቴክኖሎጅ ጋር በተያያዘበት በአሁኑ ወቅት እንዲህ አይነቱ  ችግር መከሰቱ ለተጠቃሚዎችም ሆነ ለቴክኖሎጅ ኩባንያዎች አማራጭ መንገዶችን ለመፈለግ የማንቂያ ደወል ነው ተብሏል።ስለሆነም ይህ መሰሉ ችግር እንዳይፈጠር በጊዜ ሰሌዳ  የታቀደ ማዘመን ማድረግ፣ ባካፕ መያዝ፣ በአቅራቢ ድርጅቱም ሆነ በተጠቃሚዎች ዘንድ ቀድሞ ሙከራ ማድረግ መፍትሄ መሆኑን የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ አስምረውበታል። የተለያዩ የኦፕሬቲንግ ስርዓቶችን መጠቀም ደግሞ ዋናው እና አራተኛው መፍትሄ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ