ከሊባኖስ የውጭ ሰራተኞችን ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት
ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017የመካከለኛው ምስራቅ በተለይም የእስራኤልና ፍልስጤሞች፤ ብሎም የእስራኤልና ሊባኖስ ጦርነት ያፈናቀለውና ለስጋት የዳረገው አረብ እስራኤሎችን ብቻ ሳይሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የሌሎች አገር ዜጎችንም ጭምር ነው። ልክ እንደ ጋዛ ሁሉ ባሁኑ ወቅት ሊባኖስም የጦርነት ኣውድማ እንደሆነችና ህዝቧም ለስደትና መፈናቀል የተዳረገ መሆኑ ግልጽ ነው። በተለይ በደቡብ ሊባኖስና በቤይሩት በተከታታይ በሚፈጸሙ የቦምብ ድብደባዎች ምክንያት ሁሉም ነዋሪዎች እራሳቸውን ከጥቃት ለመከልከል አካባቢውን በመልቀቅ ላይ ናቸው።
ከአፍሪካ የመጡ ሰራተኖች የተለዩ ችግሮች
ተፈናቅለውና መጠለያ አተው ወይም ወደ አገራቸው ለመሄድ መንገዱና ዘዴው ጠፍቶባቸው በጎዳና ላይ ጭምር የሚገኙት በተለይ ከአፍሪካ የመጡ የቤት ሰራታኞች መሆናቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀንና በቤይሩት የዲደብሊው ዘጋቢ ጭምር ተዘግቧል።
ብዙዎቹ ሰራተኞች በሁኔታው አስገዳጅነት ምክንያት አሰሪዎቻቸው ትተዋቸው በመሄዳቸው ለከፋ ችግር እንደተጋለጡና መጠለያም እንዳጡ ነው የሚናገሩት። በሊባኖስ የውጭ አገር ሰራተኞቾ መብቶች ላይ የምትሰራው ወይዘሪት ዳራ ፎይ ለDW እንደገለጸችው፤ በሊባኖስ የውጭ አገር ሰራተኞች በተለይም የቤት ሰራተኞች ሁኔታ እጅግ አሣሳቢ ነው፤ “ በሊባኖስ የውጭ አገር ሰራተኞች ሁኔታ በአሁኑ ውቅት እጅግ በጣም አሳስቢ ነው፡ መኖሪያ ሰፈራቸው በቦምብ የተመታባቸውና የተፈናቀሉ በርካቶች ናቸው”፤ በማለት በተለይ ጦርነቱ ባየለባቸው ደቡብ ሊባኖስና በደቡብ ቤይሩት የነበሩት ምንም አይነት የግል ንብረት ሳይዙ የወጡና የሸሹ መሆናቸውን ገልጻለች።
የተፈናቃዩ ብዛትና የሚፈጸም አድልዎ
አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከሚሆነው የሊባኖስ ህዝብ ቢያንስ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ከቤት ንበረታቸው እንደተፈናቀሉና እንደተሰደዱ በራሱ በሊባኖስ መንግስት ተገልጿል። በሊባኖስ 175 ሺ የሚሆኑ ከ98 አገሮች የመጡ የቤት ሰራተኞች እንዳሉም ዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ደርጅት አይ ኦ ኤም መረጆዎች ያሳያሉ። ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉ የምራብ አገሮች ዜጎቻቸውን በልዩ የበረራ ፕሮግራሞች ማስወጣት ጀምረዋል። ሆኖም ግን በተለይ ከአፍሪካና እስያ የመጡ ሰራተኞች መጠለያም መውጫም አተው በክፈተኛ ችግርና ስጋት ውስጥ እንዳሉ ነው የሚነገረው።
ኬንያዊቷ ሪጊና ብሌሲንግ ክያሎ “አፍሪካውያን ተፍናቃዮች ከመጠለያዎች ተለይተው እንዲወጡና የትም እንዲወድቁ እይተደረገ ነው” በማለት የሚታየውን መድሎ ለዲደብሊው ተናግራለች ። ከሴሪያሊዮን የመጣችው ሌላዋ ሰራተኛም መጠለያ አጥታ በጎዳና ላይ እንደወደቀች ነው የምትናገረው። የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሰራተኖች ግን፤ አለማቀፍ ድርጅቶች ለሌሎች አገሮች ተፈናቃዮች የሚሆኑ መጠለያዎችን ቢያዘጋጁ የተሻለ እንደሚሆን ይመክራሉ።
ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች
የሰራተኞች ችግር ግን ከመጠለያም አልፎ ብዙና ውስብስብም እንደሆነ ነው የመብት ተከራክሪ ድርጅቶች የሚናገሩት።፡በሊባኖስ የመጤ ሰራተኞችን ሁኒታና መብቶች የምትከታትለው ወይዘሪት ፎይ፤ እዚያ ለሚገኘው የዲደብሊው ባልደረባ እንደገለጸችው፤ ወደ ሊባኖስ የሚመጡ ሰራተኖች እንደደረሱ የጉዞ ሰነዳቸውን ወይም ፓስፖርታቸውን ለአሰሪዎቻቸው እንዲያስረክቡ የሚያደርግ ትክክል ያልሆነ አሰረር እንዳለና፤ አሁን እንደዚህ አይነት የደህንነት ስጋት ሲፈጠር ችግሩን ያባባሰውም የዚህ አይነቱ አሰራር እንደሆነ ገልጻለች፤ “ አሁን እንደዚህ አይነት የደህንነት ስጋት ሲፈጠር ብዙዎቹ ከሊባኖስ እንዳይወጡና ወደሌላ ቦታ እንዳይዛወሩ ያደርጋቸዋል። ሰነድ የሌላቸው በመሆኑም ምንም አይነት እርዳታም እንዳያገኙ ሁኗል” በማለት ጦርነቱ የሰዎቹን የመብት ጥሰት ያሰፋውና ያባባሰው መሆኑን ገልጻለች
ከዚያም አልፎ የብዙዎቹ ሰራተኞች አገሮች በቤይሩት ኢምባሲ የሌላቸው በመሆኑ ሰነዳቸውን ለማስተካከል ችግር መኖሩንና ቢሮክራሲውም አስቸጋሪ እንደሆነ ፎይ ገልጻለች። ይህ ሁሉ ታልፎም በአሁኑ ወቅት ወደ ቤይሩቱና ከቤይሩት የሚደረጉ በረራዎች ውስን በመሆናቸው ባሁኑ ወቅት ካንድ ወር ባነሰ ግዜ ትኬት ማግኘት እንደማይቻልና ከተገኘም ዋጋው ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጸችው።
ገበያው ንጉሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ