1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦሮሚያ ክልል ከሞት የተረፉ ዜጎች ድምፅ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27 2015

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች አካባቢ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከሞት ያመለጡ በርካታ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው በጫካ ውስጥ ለከፍተኛ ርሐብ በመጋለጣቸው መንግስት እንዲደርስላቸው ጠየቁ።

https://p.dw.com/p/4KYUO
Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

«ለረሐብ ተጋልጠዋል፤ ከበባ ውስጥም ናቸው ድረሱላቸው»

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች አካባቢ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከሞት ያመለጡ በርካታ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው በጫካ ውስጥ ለከፍተኛ ርሐብ በመጋለጣቸው መንግስት እንዲደርስላቸው ጠየቁ። በጉተን ከተማ በነበረው ውጊያ በአንድ መንደር ብቻ የ16 ሰዎች አስከሬን ሲቀበር ማየታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል። ራሳቸውን ለማትረፍ በየጫካው የተበተኑ ሰዎች ለረሐብ ከመጋለጣቸውም ባሻገር ከበባ ውስጥ ናቸው ድረሱላቸው ሲሉም ከሞት ያመለጡ ተፈናቃዮች ተማጽነዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ራሱ ያስታጠቃቸውን ሚሊሻዎች «ጽንፈኛ ፋኖ» በሚል «የሌለ ስም ሰጥቶ እየገደላቸው ነው» ሲሉም ነዋሪዎቹ አሻጥር ያሉትን ተናግረዋል። የኪረሙ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ትናንት ለዶይቼ ቬሌ በሰጠው መግለጫ ደግሞ የተደራጁ የፋኖ ኃይሎች ያላቸው ንብረት ዘርፈው ሕዝብን ሙሉ በሙሉ ከኪረሙ ከተማ አፈናቅለዋል፤ እዚህ ያለው ኃይል ሕዝብ ማዳን አልቻለም ብለዋል። 

Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችምስል Alemenew Mekonnen/DW

ኅዳር 9 ቀን፣ 2015 ዓ ም በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ እስረኞች ይፈቱ አይፈቱ በሚል መነሻነት የተስፋፋው ግጭት ወደ ጊዳ ወረዳ ተስፋፍቶ በእንዶዴና ጉትን በተባሉ ከተሞች ከፍተኛ የሕይወትና የአካል ጉዳት መድረሱን ከጥቃቱ ያመለጡ ሰዎች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ባለፈው ቅዳሜ ጉትን በተባለችው ከተማ ታጣቂዎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈፀማቸውን፣ ንብረት መዝረፋቸውንና ማቃጠላቸውን በርካቶችን መግደላቸውንና ማፈናቀላቸውን፣ አሁንም ብዙዎቹ በከበባ ውስጥ ሰለሚገኙ መንግስት ይድርስላቸው ሲሉ ጥሪ አሰማተዋል፡፡ 

የታጣቂዎች ግድያ ያላባራበት የወለጋ ወረዳዎች

«ከ52 ሺህ ህዝብ 4ሺህ ወይም 5 ሺህ ያልበለጠ ሰው ነው ወደ ባሕር ዳር የገባው፣ ሌላው በጫካ እየራበውም እየደከመውም ነው፣ መስመሩ ተከፍቶልን ብንወጣ፣ ደካሞችን ብናወጣ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፣ አጋምሳ ቡሬ መስመር ተከፍቶ ደካሞችና ብዙ ቁስለኞች አሉ፣ ጦርነት ላይ ብዙ ጋጠማቸው» በማለት ተናግረዋል፡፡ 
ሕይዎታቸውን ለማትረፍ በየጫካው የተበተኑ ነዋሪዎች ተከብበዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ራሱ ያስታጠቃቸውን ሚሊሻዎች «ጽንፈኛ ፋኖ» በሚል «የሌለ ስም ሰጥቶ እየገደላቸው ነው» ሲሉም ነዋሪዎቹ ያክላሉ፡፡ 

Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችምስል Alemenew Mekonnen/DW

«ሰው መሄጃ አጥቶ ወደዚህም ወደዚያም ልጅና ህፃን ይዞ በየገጠሩ ነው ያለው የሚበላው የለውም ከእነርሱ ጋር አብሮ ሲሰራ የነበረውን ሚሊሺያ አማራ አማራ የሆኑትን ካገኟቸው ይመቷቸዋል፣ ሁሉንም በጽንፈኛ ፈረጇቸው፣ እስከዛሬ ሲያዝዟቸው፣ ቀጠና እየሰጡ ሲያስጠብቋቸው የነበሩትን በሙሉ ፋኖ ናችሁ በሚል ፍረጃ ብዙዎቹን መቷቸው፣ እነርሱ ናቸው (የኦሮሚያ መንግስት)፣ ያስታጠቋቸው እነርሱ ናቸው አሰልጥነው ትዕዛዝ የሚሰጧቸው ሲፈልጉ ያስሯቸዋል፣ ሲፈልጉ ትጥቅ ያስፈቷቸዋል፣ ዛሬ ደግሞ ትጥቅ ማስፈታትም ማሰርም አልፈለጉም ቀጥታ ተኩሶ መግደል ነው የፈለጉት ገደሏቸው» ብለዋል፡፡ ከውጊያውም በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ለከፋ ርሀብ መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡ 
«በጣም ቤተሰቦቻችን እየተራቡ ነው፣ መብራት የለ ውሀ የለ፣ ሀኪም ቤት የለም፣ ሀኪም ቤት ሲኬድም ፋኖ ተብለህ ነው የምትረሸነው ሴትም ሁን ወንድም ሁን ቆስለህ ከሄድህ ከዚያ ውጪ ሰው የሚበላው አጥቶ ከማሳ ያልገባ ቦቆሎ እተፈለፈለ በበርሚል እተቀቀለ ሰው እንዳይሞት በማንኪያ እየተቀነሰ ነው ለህፃናት የሚሰጣቸው፣ ከውጊያውም በላይ በጣም አንገብጋቢው ምግብ ነው፣ የወደቀ አትንት ሳይቀር ልጆቹ እነሱ እየጋጡ ነው በጣም ነው የሚያሳዝን፡፡» 

መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ እንዲያስከብር መጠየቁ

የተወሰነ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው ቢደርስም በወቅቱ የሞቱ ወገኖችን ከማስቀበር ውጪ ወደ ቀያችን እንድንመለስ አልተደረገም የሚሉት የዓይን አማኝ ባለፈው ቅዳሜ በአንድ አካባቢ ብቻ 16 አስከሬኖች ሲቀበሩ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ “መከላከያ ሲመጣ ቢያንስ ወደ ቤታችን እንመለሳለን የሚል ሀሳብ ነበረን፣ ግን የሞተውን ሰው ከማስቀበር ውጪ የተሰራ ነገር የለም፣ በየአቅጣቻ ነው የተቀበረው 16 የተቀበረ እኔ በዓይኔ አይቻለሁ፣ ጉትን ወደ መንደር ሁለት ወደ ቱሉ ባና መስመር ያለውን ነው ያየሁት ወደ መንደር አንድም የሄደ አለ፣ አሁንም ያልተቀበረ አለ፣ ቦታው ሰፊ ነው አስቸጋሪ ነገሮች ስላሉ ልተለቀመ ይኖራል።» 

Äthiopien | Binnenvertrieben aus Oromia
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአማራ ተወላጆች ለጥቃቱ ኦነግንና የኦሮሚያን ክልል ልዩ ኃይል ይከሳሉ። የኪረሙ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ከፍያለው ገመዳ ትናንት ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ደግሞ የተደራጁ የፋኖ ኃይሎች ንብረት ዘርፈው ህዝብን ሙሉ በሙሉ ከኪረሙ ከተማ አፈናቅለዋል፣ እዚህ ያለው ኃይል ህዝብ ማዳን አልቻለም፣ ብለዋል፡፡ ስለጉዳዩ ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት እንደሁል ጊዜው ለዛሬም አልተሳካም፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ