1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግል አስተያየት፦ እየሰጡ መንሳት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከኃይለማርያም ደሳለኝ ከተረከቡ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። ዐቢይ በእነዚህ ዓመታት የተከተሉት የአመራር ሥልት በፍቃዱ ኃይሉ “እየሰጡ መንሳት” የሚለው አባባል ይገልጸዋል የሚል አተያይ አለው።

https://p.dw.com/p/4eJJG
በፍቃዱ ኃይሉ
“ገና በስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ብቻ እንዳስተዋልነው ድኅረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ ከቅድመ-ዐቢይ ኢትዮጵያ በእጅጉ ትለያለች። ትለያለች ማለት ግን ትሻላለች ማለት ላይሆን ይችላል” በፍቃዱ ኃይሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የሥልጣን ማማ ከተቆናጠጡ እነሆ ዛሬ መጋቢት 24፣ 2016 ስድስት ዓመት ሞላቸው። በዘመናዊ ፖለቲካ ከአንድ የአገር መሪ የሚጠበቁት መሠረታዊ ኃላፊነቶች ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን፣ ሕግ እና ስርዓት ማበጀት እንዲሁም ሥራ መፍጠር እና ኢኮኖሚ ማረጋጋት ናቸው።

እነዚህ ዘርፎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እምብዛም ናቸው። ይልቁንም በነውጥ እና ወጀብ እየተላጋች በምትሔደው መርከብ ውስጥ ወደ ካፒቴኑ መንበር ለመውጣት እርካቡ ላይ መንጠላጠል እንዲሁም መንበሩ ላይ ተደላድሎ መቀመጥ ግን ይችሉበታል። ይህንን የሚያደርጉት “እየሰጡ መንሳት” የሚለው አባባል በሚገልጸው የአመራር ፈሊጣቸው ነው።

በእርሳቸው የአጭር-ረዥም አስተዳደር ዘመን ዜጎች ብዙ ነገር “ተሰጥቷቸው” እምብዛም ሳያጣጥሙት መልሰው “ተነጥቀዋል”። ነገሩን ለማብራራት ሥልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ምስጋናውን ሳይጠግቡት፣ እርግማን ያስከተሉባቸውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በወፍ በረር እንቃኛለን። እየሰጡ የመንሳት አመራር ፈሊጣቸውም ሥልጣን ላይ መውጫ ብቻ ሳይሆን መሰንበቻ ዘዴያቸው ነው ብዬ እሟገታለሁ።

ሕግ ከልሶ የሕግ የበላይነት ላይ ዳተኝነት፣ ከአንዱ ጋር የሰላም ድርድር ገብቶ፥ ከሌላው ጋር ጦርነት መግጠም፣ የታገዱ ድረ-ገጾችን በመክፈት ዝና ሸምቶ፥ በተደጋጋሚና በስፋት በይነ-መረብን ማቆራረጥ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያላቸውን ሰዎች ሹመት ሰጥቶ፥ የመንቀሳቀሻ ምኅዳር ማሳጣት፣ የመሳሰሉት የዐቢይ መንግሥት ከፊል ገጽታዎች ናቸው።

ጥቂት ምሳሌዎችን እናንሳ፦

በፍቺ ጀምሮ በእስር መቋጨት

“መግረፍ፣ ጨለማ ቤት ማስቀመጥ፣ አካል ማጉደል የእኛ የአሸባሪነት ተግባር ነው” - ሰኔ 11 ቀን፣ 2010 በፓርላማ የተናገሩት

ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ከአፍላነታቸው ጀምሮ ያሳደጋቸው ሰው ናቸው። በታዳጊ ወታደርነት የተቀላቀሉት የኢሕአዴግ ሠራዊት አገረ ገዢ ሁኖ ሲቀጥል ሲቪል አመራር ሆነው ጎልምሰውበታል።

የገዛ ፓርቲያቸው ላይ አመፅ የቀሰቀሱ ተቃዋሚዎችን የፖለቲካ ቋንቋ እየተናገሩ ወደ ኢትዮጵያ መሪነት ሲወጡ ከፍተኛ ተስፋን በምሥራቅ አፍሪቃ ሰማይ ላይ ፈንጥቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥማቸው፣ ለአንድ ሰሞንም ቢሆን የታሰሩትን ከመፍታት፣ የተሰደዱትን ከመመለስ ጋር ተያይዞ ይነሳ ነበር።

እንዳለመታደል ሆኖ፣ ይህ ግን ለረዥም ጊዜ ሊቀጥል አልቻለም። በ2012 በተለይ ከኦሮሚያ ተቃዋሚዎች ጋር በተከሰተ ግጭት እና ውጥረት ሳቢያ፣ በ2013 እና 2014 በትግራይ ጦርነት ሳቢያ፣ በ2015 እና 2016 ከአማራ ተቃዋሚዎች ጋር በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ እልፎች በገፍ እየተነዱ ለእስር ይዳረጉ ጀመር።

ሁኔታው ካቅማቸው በላይ የሆኑ ጋዜጠኞች፣ የመብቶች ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ለስደት ተዳረጉ። ሌሎቹ ደግሞ በዝምታ ማደርን መረጡ። ዐቢይ ሲመጡ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽረው ውዳሴ እንዳልተቀበሉ ሁሉ፥ ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ ለሦስተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳውጀዋል። እርሳቸው ሲመጡ ብዙኃን

ከረዥም የጭቆና ዘመናት የተላቀቁ መስሏቸው ነበር። አሁን ብዙ ሰዎች ተራ በተራ “ትሻልን ሰድጄ፣ ትብስን አመጣሁ ይሆን?” እየተባባሉ ነው።

የሰላም ሲሉት የጦርነት ሥምምነት

“ለሰላም መሠረቱ ፍትሕ ነው፤ ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም በመግባባት ላይ የተመሠረተ ፅኑ አንድነታችን ነው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጋቢት 24 ቀን፣ 2010 ለፓርላማ ያደረጉት ንግግር

ዐቢይ አሕመድ ለ20 ዓመታት በጦርነት እና ዳግም ውጊያ ስጋት ዐውድ ውስጥ የከረሙትን ኤርትራ እና ኢትዮጵያን በሰላም ሥምምነት ፈንጠዝያ ለማስፈንደቅ የፈጀባቸው ጊዜ አራት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወራት ነበር። ይህ ስኬት በሰላም ኖቤል ሽልማት በዓለም አደባባይ ክብር አስገኝቶላቸዋል።

“ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም…” እንዲሉ፣ ዝርዝሩ የማይታወቀው ምሥጢራዊው የሰላም ሥምምነት በቅጡ ሳይጣጣም በፊት የትግራይ ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ ሥምምነቱ የሁለቱም መሪዎች የቀድሞ አጋር ፓርቲ የነበረው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ላይ የተፈፀመ “የጦርነት ቃል ኪዳን” ተብሎ ተተቸ። ሁለቱ መሪዎች የአገራቸውን ሠራዊት በማሰለፍ አሰቃቂውን ጦርነት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በመግጠም የሰላም ሥምምነቱን የጦርነት ፍሬ አሳጨዱት።

ጦርነቱ ኢትዮጵያን ድጋሚ የሚበይን ሆኖ በሌላ (የፕሪቶሪያ) ሥምምነት ተቋጨ፤ ነገር ግን ይህም ግጭት የማቆም ሥምምነት አዲስ ቅራኔ ከኤርትራ መንግሥት ጋር፣ እንዲሁም ግጭት ከአማራ ክልል ታጣቂዎች ጋር ቀሰቀሰ።

በሰላም ረገድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአጀማመራቸው በተቃራኒ ሰላማዊ ስርዓተ ማኅበር መገንባት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሳይዋጣላቸው ቀርቷል። ይልቁንም “ሰላም ሰጡን” ብሎ ያላቸው ሕዝብ “ሰላም አሳጡን” ወደሚለው ተሸጋግሯል።

"እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው"

“የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኛ እና ለፍትሕ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናኢ እንዲሆኑ ነው፤ ሕግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጋቢት 24 ቀን፣ 2010 ለፓርላማ ያደረጉት ንግግር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሥልጣናቸው የጫጉላ ዘመን ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት ከኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር በተወያዩበት ጊዜ ስለ “ሽግግር መንግሥት” አስፈላጊነት ጥያቄ ሲነሳላቸው የሰጡት መልስ “እኔ አሻግራችኋለሁ” የሚል ነበር።

አጀማመራቸውም ከጨቋኝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩ ይመስል ነበር። በርካታ እና አዎንታዊ ተብለው መመዝገብ ያለባቸውን የሕግ ክለሳዎች በገለልተኛ ባለሙያዎች በተዋቀረ ምክር ቤት እና ግብረ ኃይሎች እንዲከናወኑ አድርገዋል። እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የቀድሞው የብሮድካስት ባለሥልጣን የመሳሰሉትን ተቋማትንም በሙያቸው እና ሕዝባዊ አመኔታቸው አንቱታን ያተረፉ ግለሰቦችን በመሾም መልካም ጅማሮ አሳይተው ነበር።

ይሁን እንጂ እነዚህም ለውጦች መሬት እንዳይረግጡ ማድረጋቸው አልቀረም። የሕግ የበላይነት ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ጊዜ ቢኖር አሁን ይመስለኛል። ያለ ሕግ አግባብ ዜጎች በተደጋጋሚ ይታሰራሉ፤ ፍርድ ቤት የፈታቸው ሰዎች በፀጥታ ኃይሉ ታስረው የሚቆዩበት አጋጣሚ አለ፤ ዳኞች ፍርድ ቤት በወሰኑት ውሳኔ ሳቢያ እስከ መታሰር ደርሰው ያውቃሉ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩ ዜጎች በፀጥታ ኃይሎች ያለፍርድ መገደላቸው በሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቶች ተጋልጠዋል።

ለብዙዎች ‘የለውጡ’ ተሿሚዎች ምኅዳሩ ተቆልፎባቸው ከርሟል፤ በፖለቲካው የተሰጣቸው በፀጥታ ኃይሉ በኩል ተወስዶባቸዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ሹመታቸው የለውጥ ማሳያ ተደርጎ ሲጠቀሱ ከነበሩት ሰዎች መካከል ራሳቸውን ሳያሰናብቱ የቀሩት ጥቂቶቹ ናቸው።

የኮሚሽን ‘ሰብስክሪፕሽን’

የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለችግሮች መፍትሔ ብሎ የሚጠቁመው የኮሚሽኖች መቋቋምን ይመስላል። በአፍላነታቸው የተወሰነ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የማንነት እና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ይኼ ነው የሚባል ፍሬ ሳያፈሩ ከስመዋል።

አሁንም ለመክሰም አንድ ዓመት የቀረው አገራዊ ምክክር እንዲያመቻች የተቋቋመው ኮሚሽን፣ በአጀማመሩ ሰሞን የዓለምን ቀልብ እንዳልሳበ ሁሉ፣ በአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተነሳበት የቅቡልነት ጥያቄ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ሳቢያ ፈተና እንደገጠመው ኮሚሽነሮቹ ሲገልጹ ሰንብተዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በጥድፊያ የተቋቋመ ሰሞን፣ እንደ እነ ጃዋር መሐመድ፣ እስክንድር ነጋ፣ እና ስብሓት ነጋ ያሉ ፖለቲከኞች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱበት፣ የትግራዩ ጦርነት በተናጠል ውሳኔ ተኩስ የቆመበት ጊዜ ስለነበር፣ ብዙዎች አገራዊ ምክክሩ ላይ ትልቅ ተስፋ ጥለው ነበር፤ አሁን፣ አሁን ያ ተስፋ እምብዛም አይታይም።

እስካሁን ምንም ፍሬ ማፍራት ያልቻለው የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽንም እዚሁ ተርታ ሊጠቀስ ይችላል። ከፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት በኋላ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲም ቢያንስ ሁለት ኮሚሽኖችን ለማቋቋም አቅጣጫ ያስቀምጣል። እነዚህ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን እና የተቋማዊ ማሻሻያ ኮሚሽን የቀደምቶቹ ጊዜያዊ ኮሚሽኖች እጣ ፈንታ እንደማይገጥማቸው ግን ማረጋገጥ አይቻልም።

ኮሚሽኖቹ በሚቋቋሙበት ጊዜ የሚወሰዱ ርምጃዎች ተስፋን ከፍ የሚያደርጉ ቢሆንም፥ እያዘገሙ ሲሔዱ ግን ምንም ፋይዳ የሌላቸው ሁነውና ተዘንግተው ይከስማሉ።

በእኔ እምነት፣ በነዚህ ሁሉ በቁጥር አጭር፣ በታሪክ ይዘት ረዥም ስድስት ዓመታት ውስጥ የዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ብቻ ሥር እየሰደደ ነው። የትግራይ ጦርነት የሥልጣን ዘመናቸውን ባጭር ቀጨው ተብሎ ሲጠበቅ፣ ባልተገመተ አክሮባት የእርሳቸውን ይሁንታ የሚማፀን ህወሓት-መር ጊዜያዊ መንግሥት ሆኖ ድጋሚ ተዋቅሯል።

በትግራይ ጦርነት ሰበብ የህወሓት ሰዎች ቁልፍ ቦታ ይዘውበታል ይባል የነበረውን የደኅንነት እና መከላከያ ኃላፊነት ቦታዎች በታማኞቻቸው ተክተዋል። ቀድሞ የቅርብ ወዳጆቻቸው የሚመስሉ ፖለቲከኞች በመንገዳቸው አንስማማም ብለው ሲኮበልሉ፣ አዳዲስ ታማኞችን አፍርተው ቀጥለዋል።

“በፖለቲካ ዓለም ቋሚ ወዳጅም ይሁን ቋሚ ጠላት የለም” የሚለውን ኅልዮት በስድስት ዓመታት ብቻ በበርካታ ምሳሌዎች አሳይተዋል።

የዐቢይ አሕመድ እየሰጡ መንሳት የአመራር ፈሊጥ የፖለቲካውን እና ተዋናዮቹን አሰላለፍ ከነማሊያቸው እየፐወዘው ከርሟል። እነዚህ መገላበጦች እና ፈጣን መለዋወጦች ለሥልጣን ተጋፊዎች የመረጋጋት፣ የማቀድ እና የመፈፀም ዕድል አይሰጡም። ፖለቲከኞቹ ለሚከሰቱት የድንገቴ ሁኔታዎች መልስ በመስጠት ብቻ ይጠመዳሉ። ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለታማኞቻቸው ሥልጣን ማደላደያ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ሌላው ቀርቶ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እና ኃያላን አገራት ሳይቀሩ በአዳዲስ ሁኔታዎች እና ለውጦች መደራረብ ሳቢያ ወጥ የዲፕሎማሲ አቋም መያዝ ተስኗቸው ይስተዋላሉ።

በዚህ መሐል ዐቢይ አሕመድ በሚያስገርም ፍጥነት ኢትዮጵያን በሚፈልጉት መንገድ መልሰው እየሠሯት ነው። ገና በስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ብቻ እንዳስተዋልነው ድኅረ-ዐቢይ ኢትዮጵያ ከቅድመ-ዐቢይ ኢትዮጵያ በእጅጉ ትለያለች። ትለያለች ማለት ግን ትሻላለች ማለት ላይሆን ይችላል።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም።