″እንደ በሬ እየታረስኩ ለሶስት አመት ቆይቻለሁ″-በታንዛኒያ ከእስር የተፈታ ኢትዮጵያዊ | ኢትዮጵያ | DW | 09.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

"እንደ በሬ እየታረስኩ ለሶስት አመት ቆይቻለሁ"-በታንዛኒያ ከእስር የተፈታ ኢትዮጵያዊ

ባለፉት ሶስት ወራት 800 ገደማ ኢትዮጵያውያን ከታንዛኒያ እስር ቤቶች ተፈተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢትዮጵያውያኑ በቀን አንድ ጊዜ እየተመገቡ የጉልበት ሥራ ይሰሩ ነበር። የታሰሩት ተፈተው ሲመለሱ አዲሶቹ መንገድ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ግን በታንዛኒያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፈታኝ ሆኗል

ለአመታት ከታሰሩባቸው የታንዛኒያ ማረሚያ ቤቶች ተፈተው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጅት የጀመሩ ወጣቶች አብዛኞቹ ጸጉራቸውን በአጭር ተቆርጠዋል፤ የተላጩም አሉበት። ፊታቸው የገረጣ፤ ያለፉ አመታት የታንዛኒያ እስር ቤት ኑሯቸው በፈተና መሞላቱን የሚመስክር ወጣቶችም ከመካከላቸው ይታያሉ። ነገር ግን ደስተኛ ናቸው። ቢያንስ ከእስር አስፈትተው ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ላመቻቹላቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረቦች ያን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ባለፈው ሳምንት ከታንዛኒያ ባጋሞዮ በሚባል ግዛት ኪንጎንዶኒ ከሚባል ማረሚያ ቤት የተፈቱ ናቸው። በዳሬ ሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተፈቺዎቹ ኢትዮጵያውያን ያለፉበትን ውጣ ውረድ በትውልድ ቀያቸው ላሉ እንዲያጋሩ በፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው ቪዲዮ "የኃያላን ሁሉ ኃያል ነው፤ የነገስታት ሁሉ ንጉስ ነው" እያሉ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑት ወጣቶች እንደሚሉት በታንዛኒያ እስር ቤቶች በጉልበት ሥራ ሰርተዋል፤ ተደብድበዋል፤ በቂ ምግብም ሳያገኙ ቆይተዋል።

ጥቂት ምግብ ብዙ የጉልበት ሥራ፤ -ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት

በዱራሜ ዞን ከምትገኘው ዱዬ ገና ወረዳ የትውልድ ቀዬው ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት መንገድ የጀመረው ጸጋዬ ወልደ ኪዳን በታንዛኒያ ጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ለአመታት አስከፊውን ኑሮ በእስር ቤት ግብግብ ከገጠሙት መካከል አንዱ ነው። "አመት ሙሉ ለሊት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ እየወጣሁ ማታ አስራ ሁለት ሰዓት እየገባሁ ቀን እና ለሊት እየሰራሁ ቆይቻለሁ" የሚለው ጸጋዬ ያለፈበት ስደት በእሱ ብቻ እንዲበቃ ይመኛል።

ጫካ መመንጠር እና ሩዝ መትከል ጨምሮ የጉልበት ሥራ ላይ የቆየው ጸጋዬ "ምግብ በ24 ሰዓታት አንድ ጊዜ ኡካሊ የሚባል በበቆሎ የተሰራ ገንፎ አለ። እሱ አንድ የ15 አመት ሕፃን ልጅ እንኳ በልቶ የማያጠግበው ነው። ከባድ የሆነ ስራ ሰርተን ያንን እንበላለን። ያንን ከ24 ሰዓት በኋላ ነው እንደገና ከሥራ መልስ የምናገኘው። እሱንም ቶሎ ብሉ ተብለን በዱላ እንመታለን" ሲል ያለፈባቸውን አመታት አስከፊነት ይገልፃል። በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምኒስትር ካውንስለር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ "ከታንዛኒያ መንግሥት ጋር ባደረግንው ውይይት አግባብነት የሌላቸው ሥራዎች እንደማያሰሯቸው ነው የሚነግሩን። ልጆቹ ደግሞ ውሀ እንቀዳለን፤ እርሻ እናርሳለን፤ ድንጋይ እንፈልጣለን ይላሉ" ሲሉ ስለ ሁኔታው አስረድተዋል። 

130 ሺሕ ብር ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ የሚከረው ጸጋዬ እሱ እና መሰሎቹ በእስር ቤት የደረሰባቸውን ግልምጫ እና ስድብ ከባድ ይለዋል።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምኒስትር ካውንስለር አቶ ቴዎድሮስ ግርማ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያንኑ በመንገዳቸው ስለሚገጥማቸው ውጣ ውረድ ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም። አቶ ቴዎድሮስ ከ120 እስከ 150 ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የከፈሉት ኢትዮጵያውያን "ከአገራቸው ሲወጡ በደላላ ከሶስት እስከ ሰባት በሚደርሱ ቀናት ደቡብ አፍሪካ ትደርሳላችሁ ተብለው ነው። ምንም የሚያውቁት ነገር የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ በታንዛኒያ እስር ቤቶች ባደረገው አሰሳ ከተገኙ ሰዎች መካከል "በጣም የታመሙ ሰዎች" መኖራቸውን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ በቂ ምግብ አለማግኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ከአዲስ አበባ ተነስቶ አውስትራሊያ ሊሻገር መንገድ የገባው ሐፍቱ በርሔ በበኩሉ "ጎሞዦ የተባለ መጥፎ እስር ቤት ጉድጓድ ውስጥ ሳይሞቱ የተቀበሩ ልጆች አሉ። እኛ ሳንሞት ተቀብረን የነበርን ሰዎች ነን" ሲል ያለፉበትን ፈተና ይገልጸዋል። "ከዚህ አገር ለመውጣት እንኳን እግዚአብሔር አበቃኝ እንጂ ይቺን አገር ዞሬም አላይም" ባይነው ሐፍቶም።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሰሳ

ጸጋዬ እና ሐፍቱ በታንዛኒያ ባጋሞዮ በሚባል ግዛት ኪጎንዶኒ በተባለ እስር ቤት ከተገኙ 80 ኢትዮጵያውያን መካከል ናቸው። በታንዛኒያ ዋና ከተማ ከሶስት ወራት ገደማ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅድሚያ ከሰጣቸው ሥራዎች መካከል የአገሪቱን ማረሚያ ቤቶች ማሰስ ነበር። የኤምባሲው ምኒስትር ካውንስለር ኢትዮጵያውያኑ "ያሉበትን እስር ቤት ለመለየት ሞከርን። ከዚያ አንድ ባንድ መዞር ነው የጀመርንው" ሲሉ ጅማሮውን ይገልጹታል። ወደ ደቡብ አፍሪካ መንገድ ጀምረው የታሰሩት ኢትዮጵያውያን "በየግዛቱ እስር ቤት ነው ያሉት። መጀመሪያ ብዙ ቁጥር ያለው እስረኛ ያለበትን ነው የለየንው። እነሱ ላይ አሰሳ ጀመርን። ሔደን ያየንው ነገር ልባችንን ነው የሰበረው" የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ  ታንጋ በተባለ እስር ቤት ብቻ በአንድ ቀን 447 ኢትዮጵያውያን መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በታንዛኒያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቱ እስር ቤቶች ባደረገው አሰሳ የሚያገኛቸውን ዜጎች አስፈትቶ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወዲያውኑ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያደርጋል። አቶ ቴዎድሮስ "ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ወደ 800 የሚደርስ ኢትዮጵያዊ ልከናል" ሲሉ ተናግረዋል። ከእስር የተፈቱትን ወጣቶች ወደ አገራቸው ለመመለስ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ከ187 ሺሕ ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) ኢትዮጵያውያኑን ለመመለስ መጠነኛ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ

በተለያዩ መንገዶች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ያጠኑት አቶ ዮርዳኖስ ሰይፉ ከኬንያ እና ከታንዛኒያ ሕግ አስከባሪዎች ለመሸሽ ስደተኞች እና አሻጋሪዎች በጀልባ በመሳፈር በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች መጓዝ መምረጣቸውን ይናገራሉ። አቶ ዮርዳኖስ "ከኬንያ እና ታንዛኒያ ድንበሮቹን ተሻግረውም ሆነ ሙስና ሰርተው አሊያም በሕንድ ውቅያኖስ ተሻግረው ታንዛኒያ እና ማላዊ ድንበር እንዲሁም ታንዛኒያ እና ሞዛምቢክ ድንበር የሚያርፉ ወጣቶች በጣም ቁጥራቸው ብዙ ነው።በተለይ በማላዊ ፓሮንጋ እና ዛሌካ የሚባሉ ቦታዎች አሉ። በእነዚህ ቦታዎች በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የሌላ አገር ስደተኞች በብዛት አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ዮርዳኖስ «ከማላዊ ተነስተው ወደ ዚምባብዌ እና ሞዛምቢክ የሚዘልቁ ብዙ ልጆች አሉ። ማላዊንም ተሻግረው ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ የሚሰፍሩ ብዙ ወጣቶች አሉ። ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ ወደ ደቡብ አፍሪካ መግቢያ የጎረቤት አገራት ስለሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እነዚያ አገራት ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ስለዚህ ማላዊ ሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ ብዙ ስደተኞች ሊገኙ ይችላሉ» ሲሉ ይናገራሉ። 

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያንን አኗኗር የፈተሸ ጥናት በሰሩበት ወቅት በማላዊ፣ በሞዛምቢክ እና በዚምባብዌ ጫካዎች፤ ሥራ ፈት ሕንፃዎች፤ የድሮ ትምህርት ቤቶች እና በደላሎች ማጎሪያዎች ይቆዩ እንደነበር መረጃ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ዮርዳኖስ "ያልተያዙ፤ ያልታሰሩ፤ በአሻጋሪዎች እጅ፤ በደላሎች እጅ ያሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ" ብለዋል።

ውሀ ቅዳ ው መልስ?

በዳሬ ሰላም የሚገኘው ኤምባሲ ሁለት ሕፃናት እና ከሶስት እስር ቤቶች የተፈቱ 25 ወጣቶችን ወደ አገራቸው በሸኘበት ባለፈው ሳምንት ሌሎች ሌሎች 31 ኢትዮጵያውያን በታንዛኒያ የጸጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ይኸ የአቶ ቴዎድሮስን እና የባልደረቦቻቸውን ሥራ ፈታኝ አድርጎታል።

አቶ ቴዎድሮስ "እኛ ወደ አገር ቤት ከምናስገባው ባልተናነሰ ቁጥር ሌላው ወደዚህ እየመጣ ይታይሃል። ተስፋ የምናደርገው ምንድነው አብዛኞቹ ከአንድ አካባቢ የመጡ እንደመሆናቸው በእዚያ አካባቢ ጠንከር ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ቢሰራ ቶሎ ይኸን ነገር ማስቀረት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ተስፋ ይሰጠናል" ሲሉ ቀሪው የቤት ሥራ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ወራት በተለያዩ አገሮች በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ብርቱ ሥራ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት እንደገለጸው ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የተፈቱ 1,400 ኢትዮጵያውያንን ለመመስ ዝግጅት ላይ ይገኛል። የርስ በርስ ጦርነት ባደቀቃቸው የመን እና ሊቢያን በመሳሰሉ አገሮች መፈናፈኛ ያጡ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ