ኤቦላ ከምዕራብ ወደምሥራቅ አፍሪቃ | ጤና እና አካባቢ | DW | 26.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ኤቦላ ከምዕራብ ወደምሥራቅ አፍሪቃ

ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈዉ የኤቦላ ተኀዋሲ ምሥራቅ አፍሪቃ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ዉስጥም መከሰቱን በሳምንቱ መጨረሻ የሀገሩቱ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።

ለሙከራ በተዘጋጀ መድኃኒት ሁለት በኤቦላ የተያዙ አሜሪካዉያን ዶክተሮች ታክመዉ ድነዋል፤ ቀደም ብሎ መድኃኒቱ የተፈተነባቸዉ ስፔናዊ ግን አልተረፉም።

«ላይቤሪያ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት በህመም አልጋዬ ላይ ተኝቼ በየቀኑ ህመሜ እየጠናና እየደከምኩ ባለሁበት ሁኔታ ፈጣሪ ታምሜ እያለሁም እንደሚረዳኝ አምኜ በህይወቴም ሆነ በሞቴ እሱ እንዲከብር እፀልይ ነበር። ያኔ አላወቁም ነበር ግን አሁን እንደሰማሁት በዚያ ሳምንትም ሆነ ዛሬ በመላዉ ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለእኔ ይፀልዩ ነበር። እኔም ይህ ሁኔታ በመላዉ ዓለም የሰዎች ህይወት ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳሳደረ የሚተርኩ ታሪኮችንም ሰማሁ።እናም ቤተሰቦች ጓደኞችንም ሆነ ጭራሽ ፍፁም የማላዉቃችሁን ሰዎች ሁሉ ላደረጋችሁልኝ ድጋፍ የማመሰግንበት አቅም የለኝም። ግን አንድ ነገር ልነግራችሁ እችላለሁ የማገለግለዉ ለፀሎት መልስ የሚሰጠዉን ታማኝ አምላክ ነዉ። »

Dr. Kent Brantly

ዶክተር ኬንት ብሬንትሊ

ይህን የተናገሩት ላይቤሪያ ዉስጥ በሙያቸዉ ለመርዳት ተሰማርተዉ ሳለ በኤቦላ ተኅዋሲ ተይዘዉ ለሳምንታት ህክምና ላይ ከቆዩ በኋላ ለበሽታዉ ተብሎ በተዘጋጀዉ የሙከራ መድኃኒት ከቀናት በፊት ድነዉ ከሃኪም ቤት የወጡት አሜሪካዊዉ ዶክተር ኬንት ብሬንትሊ ናቸዉ። ኤቦላ በምዕራብ አፍሪቃ ሳይገደብ በተለያዩ አካባቢዎችም ብቅ እያለ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊ የዘመን ቀመር 1976ዓ,ም ኤቦላ ተኀዋሲ የታየዉ በሱዳኗ ናዛራ እና በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ግዛት ያምቡኩ እንደነበር የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ስሙም ያምቡኩ ከተማ ኤቦላ ከተሰኘዉ የኮንጎ ወንዝ አቅራቢያ ስለምትገኝ ከዚያዉ የተቀዳ ነዉ። በመጀመሪያ ኤቦላ የታየባት ሀገር ታዲያ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ዳግም ችግሩ መከሰቱን ይፋ አድርጋለች። የሀገሪቱ ባለስልጣናት እንደገለጹት በሰሜን ምዕራብ ኢኳቶሪያ ክፍለ ሃገር በርከት ያሉ ሰዎች በከባድ የትኩሳት ህመም መያዛቸዉን እና ምርመራ ከተደረገላቸዉ ስምንት ሰዎች መካከልም ሁለቱ በኤቦላ መያዛቸዉ ተረጋግጧል። ዳጂራ በተባለችዉ ከተማም 13 ሰዎች በተመሳሳይ ትኩሳት ህመም ህይወታቸዉ አልፏል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ሌሎች 11 ተገልለዉ እየተጠበቁ መሆኑን ከ80 ሰዎች በላይ ደግሞ ክትትል እየተደረገባቸዉ እንደሆነ አመልክተዋል። ተኅዋሲዉ በመጀመሪያ ኮንጎ ዉስጥ በኤቦላ ወንዝ አካባቢ ከታየ አንስቶ በተደጋጋሚ በመጠነኛና በከፍተኛ ወረርሽኝ መልክ ተከስቶ እንደሚያዉቅ በመጠቆም የአሁኑ በምዕራብ አፍሪቃ ከሚታየዉ ጋ ግንኙነት አለዉ ለማለት እንደማይቻል ነዉ ተኀዋሲ ላይ ምርምር የሚያካሂደዉ በሃምበርግ ጀርመን የሚገኘዉ በርናርድ ኖህት ተቋም ኃላፊ ዶክተር ሽሚት ቻናዚት የሚፈልጹት፤

«በዚህ አካባቢ በተለይ ባለፉት ዓመታት ኤቦላ ተኀዋሲ እየደጋገመ በአነስተኛም ከፍተኛ ወረርሽኝ መልክ ተነስቷል። እናም ምናልባት ይህ የአሁኑ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪቃ ከሚታየዉ ወረርሽኝ ጋ ግንኙነት ላይኖረዉ ይችላል።»

ኤቦላ አፍሪቃ ዉስጥ ካለፈዉ የካቲት ወር አንስቶ አሁን በአምስተኛ ሀገር ዉስጥ መገኘቱ ነዉ። ጊኒ፣ ላይቤሪያ፤ ሴራሊዮን፣ ናይጀሪያ እና ኮንጎ። የዓለም የጤና ድርጅትም የህክምና ባለሙያዎችና የታማሚዉን አካል ላለመንካት የሚረዱ የመከላከያ መሣሪያዎችን ወደኮንጎ መላኩን ትናንት አስታዉቋል። ኮንጎ ዉስጥ በሽታዉ የተቀሰቀሰበት አካባቢ ገጠር ነዉ። የበሽታዉ ወረርሽኝ ተቀስቅሶበታል በተባለዉ ስፍራም ተመሳሳይ የህመም ዓይነት ከሚታይባቸዉ እስካሁን ምርመራ ከተደረገላቸዉ የሁለቱ ብቻ ነዉ የተረጋገጠዉ። የተቀሩት ምርመራም ቀጥሏል። ዶክተር ቻናዚት እንደታማሚዎቹ ብዛት ተኀዋሲዉ የተገኘባቸዉ ቁጥር ማነሱ ምናልባት ምዕራብ አፍሪቃ ከተቀሰቀሰዉ የኤቦላ ዓይነት ይኸኛዉ ጉዳቱ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚገምቱት፤

«ምናልባት ይህ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነዉ ከምዕራብ አፍሪቃዉ ጋ ስናወዳድረዉ፤ በወደ20 በመቶ ገደማ ነዉ። ስለዚህ ምናልባት ይህኛዉ ከፍተኛ ጉዳት የማያስከትል የተለየ የኤቦላ ተኀዋሲ ዓይነት ሊሆን ይችላል።»

ኤቦላ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የገደላቸዉ ሰዎች ቁጥር ከ1,400 ከፍ እንደሚል ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። የዓለም የጤና ድርጅት ግን የለም ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል እያለ ነዉ። እንደድርጅቱ ግምትም በአካባቢዉ የሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች ታማሚዎች ሃኪም ቤት እንዲገቡ ስለማይፈቅዱ የታማሚዎችም ሆነ የሟቾች ቁጥር ከሚጠቀሰዉ እጅግ ሊበልጥ ይችላል። ይህን በማገናዘብ ይመስላል ሴራሊዮን ታማሚዎችን የደበቀ የሚቀጣበት ሕግ አዉጥታለች። ሴራሊዮን ዉስጥ በኤቦላ ተኀዋሲ የተያዙ ሰዎች ህክምና እንዳያገኙ የሚሠዉር በወንጀል በሁለት ዓመት እሥራት እንደሚቀጣ ታዉጇል። የሀገሪቱ የጤናና የንፅሕና ጥበቃ ሚኒስትር ሚያታ ካርገቦ፤ ታማሚዎች ከያሉበት እየተፈለጉ ባለዉ አቅም ክትትል የሚደረግበት ሁኔታ መጠናከር እንደሚኖርበት ነዉ ያሳሰቡት።

«የታመሙ ሰዎችን የምናገኝበትን የግንኙነት መስመር ማጠናከር መቻላችንን ማረጋገጥ አለብን፤ የታመሙ ሰዎችን የምናስስበትን የቅኝት እንቅስቃሴያችን ይበልጥ የተጠናከረ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ የታመሙ ሰዎች የሚያዙበትን ሁኔታ በማሻሻልም ታማሚዎች ወደእኛ የህክምና ማዕከል እንዲመጡ ማድረግ መቻል አልብን እንዲሁም ተነጥለዉ ለሚጠበቁበትም በበቂ ሁኔታ በሰዓቱ ተገቢዉን ርዳታ መስጠታችንንም ማረጋገጥ አለብን።»

ሴራሊዮን ለኤቦላ ለተጋለጡ ዜጎቿ የሚደረገዉን ክትትል ለማጠናከር ብትዘጋጅም በተኀዋሲዉ የተያዙ ወገኖቻቸዉን ለመርዳት ሲጥሩ በኤቦላ ተይዘዉ ህይወታቸዉን ያጡት የሀገሪቱ ዶክተር ነገር ግን አሁንም እንዳብሰለሰላት ነዉ። ዶክተር ሼክ ዑመር ካን ባለፈዉ ሐምሌ ወር መጨ,ረሻ ገደማ በኤቦላ ተይዘዉ አልጋ ላይ ሲወድቁ ከነበሩበት ገጠራማ አካባቢ በድንበር የለሽ ሃኪሞች ወደሚተዳደረዉ ሃኪም ቤት ነበር የተወሰዱት። መሃል ከተማ በምዕራባዉያን ሃኪሞች በሚንቀሳቀሰዉ የህክምና ማዕከል መድረሳቸዉ አንድ ነገር ቢሆንም አብነት አግኝተዉ ማገገማቸዉ ግን የሚታለም አልሆነም። በወቅቱ በሰዎች ላይ ያልተሞከረዉ ነገር ግን በቤተ ሙከራ በእንስሶች ላይ የተፈተሸዉ Z ማፕ የተሰኘዉ መድኃኒት ይሰጣቸዉ አይሰጣቸዉ በሚል ክርክር ተፈጠረ። ሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸዉ ለመሄድ ወደፈሩበት በኤቦላ የተበከለ አካባቢ በድፍረት ሄደዉ ዜጎቻቸዉን ሲረዱ የቆዩትን ዶክተር ማን ደፍሮ ያልተፈተነ መድኃኒት ይስጣቸዉ? ብሔራዊ ጀግና በዚህ ሁኔታ ከመግደል በሚል ሁሉም እጁን ሰበሰበና መድኃኒቱ ሳይሰጣቸዉ ዶክተር ካን አሸለቡ ላይነቁ። በሰዉ ላይ ባልተሞከዉ መድኃኒት መታከማቸዉ የተነገረዉ ሁለቱ አሜሪካዉያን ዶክተሮች አገግመዉ ከሃኪም ቤት የመዉጣታቸዉ ዜና ሲሰማ ግን በደፋሩ ዶክተር ህልፈተ ህይወየት ያዘኑ ሴራሊዮናዉያን ምነዉ በተሞከረባቸዉ ኖሮ የሚል ቁጭት ዉስጥ ገቡ። ትረፊ ያላት የዛሬ ሁለት ዓመት ወደላይቤሪያ ያቀኑት የአሜሪካዊዉ ዶክተር ኬንት ብሬንትሊ ነፍስ በሙከራዉ መድኃኒት ከመንገድ መመለሷ ያስደነቃቸዉ ዶክተር የሃኪም ቤት ሲወጡ እንዲህ ነበር ያሉት፤

«ዛሬ ተዓምራዊ ዕለት ነዉ። ነፍሴ በመትረፉ፣ ደህና በመሆኔና ከቤተሰቦቹም በመደባለቄ በጣም ተደስቻለሁ፤ እንደህክምና የበጎ ፈቃድ ባለሙያ እራሴን በዚህ ሁኔታ አስቤዉ በፍፁም አላዉቅም። ባለፈዉ ጥቅምት ወር ለሁለት ዓመታት ከሳምራዉያን በርስ ጋ ለመሥራት እኔና ቤተሰቤ ወደላይቤሪያ ስንሄድ ኤቦላ አልነበረም።»

ኤቦላ ከሰዉ ወደሰዉ የሚተላለፈዉ በተኀዋሲዉ ከተያዘዉ ሰዉ ሰዉነት የሚወጣ ማንኛዉን ፈሳሽ በመንካት መሆኑ ነዉ ተደጋግሞ የሚነገረዉ። ታማሚዎች ወደላይም ወደታችም የሚላቸዉ ሲሆን ከዉስም ሆነ ከዉጭ አካላቸዉ መድማት ይጀምራል በሽታዉ የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ። ይህ ማለትም ይህ ነዉ የሚባል ህክምና ማግኘት የማይችሉት በገጠራማዎቹ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሚገኙት ታማሚዎች አካል በሙሉ በተኀዋሲዉ የመመረዝ አጋጣሚዉ ከፍተኛ ነዉ የሚሆነዉ። በሽተኞቹን በመርዳት ላይ የሚገኙ ሃኪሞች ለኤቦላ መጋለጣቸዉ የሚያመላክተዉም ይሄንኑ ነዉ። የብሪታኒያ ዜጋ የሆነ አንድ ወጣት ነርስም እዚያዉ ሴራሊዮን ዉስጥ በተኀዋሲዉ ተይዞ ወደሀገሩ ተወስዷል። በሌላ በኩል ላይቤሪያ ዉስጥ በተመሳሳይ ተግባር ተሠማርተዉ ሳለ በኤቦላ የተያዙት ላይቤሪያዊ ዶክተር እንደነ ዶክተር ብሬንትሊን የሙከራ መድኃኒት ቢሰጣቸዉም ሳይተርፉ መቅረታቸዉ ነዉ የተሰማዉ። አብርሃም ቦርቦር ላይቤሪያ ዉስጥ በZ-ማፕ እንዲታከሙ ተወስኖ መድኃኒቱ ከተሰጣቸዉ ሶስት ዶክተሮች አንዱ ነበሩ። የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር እንደሚሉት ከሆነም የዶክተሩ ሞት ከፍተኛ ድንጋጤ ነዉ የፈጠረዉ፤ ምክንያቱም እሁድ ዕለት የነበሩበት ሃኪም ቤት ዉስጥ ከመኝታቸዉ ተነስተዉ ሲንጎራደዱ ታይተዉ፤ በጥቂት ቀናት ይወጣሉ የሚል ተስፋ በሁሉም ዘንድ አሳድረዉ ነበር። ግን አልሆነም ማምሻዉን አረፉ። ሌሎቹ ማለትም አንደኛዉ ዩጋንዳዊ ሌላኛዉ ናይጀሪያዊ የሆኑት እና ላይቤሪያ ዉስጥ የሚሠሩት ሁለቱ ዶክተሮች ግን አሁንም ህክምናቸዉን ቀጥለዋል። የተጠቀሰዉ መድኃኒት ቀደም ሲልም ከላይቤሪያ ወደሀገራቸዉ የተወሰዱት የስፓኝ ዜጋ ለሆኑት ወንጌላዊ ቄስ የተሰጣቸዉ ቢሆንም አላዳናቸዉም። ጃፓን አሁን ለከባድ ኢንፍሉዌንዛ የሚረዳ አንድ መድኃኒት የኤቦላ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ሊጠቅም ይችላል በሚል ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን አሳዉቃለች። የሀገሪቱ ካቢኔ ዋና ጸሐፊ ዮሺሂዴ ሱጋ ትናንት እንደገለፁት የዓለም የጤና ድርጅት ጥያቄ የሚያቀርብላቸዉ ከሆነ መድኃኒቱ ዝግጁ ነዉ። እንዲያም ሆኖ ጃፓን አለኝ የምትለዉ መድኃኒት ኤቦላን ለማከም ይችል እንደሁ የአሜሪካን የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ሙከራ እንዲያደርግበት ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ ነዉ። ጃፓን ከ20,000 በላይ ሰዎች ለማከም የሚችል የመድኃኒት ክምችት አለኝ ባይ ናት፤ መፈተን ግን ይኖርበታል።

በሌላ በኩል በምሥራቅ አፍሪቃ እንደኬንያ ሁሉ በርካቶችን የምታስተናግደዉ ኢትዮጵያ የኤቦላ ታማሚዎች ቢያጋጥሙ ለብቻ የሚቆዩበት አስር አልጋዎች ያሉት ሃኪም ቤት መዘጋጀቱን የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ማስታወቃቸዉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ እስካሁን በተኀዋሲዉ የተያዘ ሰዉ አለመገኘቱን በመግለፅ ሃኪም ቤቱ 50 አልጋዎች እንዲኖረዉ ለማድረግ መታቀዱንም አስተድተዋል። ሃኪም ቤቱ ቢዘጋጅም ለጊዜዉ አጣዳፊ ነገር የለም ማለታቸዉም ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ኤቦላን ለመከላከል የምታደርገዉን ዝግጅት እንዲያብራሩልን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የህዝብ ግንኙነት ጠይቀን ኤቦላን በሚመለከት መግለጫ የሚሰጡትን ሁለት ተጠሪዎች አድራሻ ብናገኝም ይመለከታቸዋል የተባሉትን ደዉለን ልናገኛቸዉ አልቻልንም። በተለይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የጤና ተቋም ኃላፊ ዶክተር ዳዲ ጂማ ጸሐፊያቸዉ ለጊዜዉ ሥራ ላይ መሆናቸዉን ገልጸዉ አድረን እንድንደዉል ነግረዉናል። ሆኖም ዛሬም ብንደዉል ልናገኛቸዉ ባለመቻላችን የሚደረገዉን በትክክል ማካተት አልቻልንም።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic