ኢትዮ-ቴሌኮም እና የግል ድርጅቶች ያቀናጀው የኢንተርኔት አገልግሎት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 16.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ኢትዮ-ቴሌኮም እና የግል ድርጅቶች ያቀናጀው የኢንተርኔት አገልግሎት

በኢትዮጵያ ብቸኛ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጠዉ መንግስታዊው ኢትዮ-ቴሌኮም፤ የግል ድርጅቶች ከተቋሙ ጋር በመተባበር አገልግሎቱን እንዲሰጡ ፈቅዷል፡፡ ፈቃዱን ካገኙ ድርጅቶች መካከል አንዱ ባለፈው ስራውን በአጭር ጊዜ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይህን እንደ በጎ እርምጃ ቢወስዱትም ሁነኛ መፍትሄ አይደለም ብለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:43

ኢትዮ-ቴሌኮምንና የግል ድርጅቶችን ያቀናጀው ኢንተርኔት

“ሎንሊ ፕላኔት” የተሰኘው ተቋም ከጉዞ ጋር በተያያዙ መጽሐፍቱ እና ሌሎች ህትመቶቹ በዓለም ትልቁ  ነው፡፡ ተቋሙ ስለየሀገራቱ በሚያደራጀው መረጃ ለበርካታ ተጓዦች እንደ ቁልፍ ጉዳይ የሚታየውን የኢንተርኔት አገልግሎት አጽንኦት ሰጥቶ ያነሳል፡፡ “ሎንሊ ፕላኔት” ኢትዮጵያን በሚያስተዋውቅበት ክፍሉ በሀገሪቱ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎት በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ጋር በማነጻጸር ያስቀመጠ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትን ኢንተርኔትን “ክፉኛ የሚጠራጠር” በሚል ተችቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞ በገጠመው ወቅት የማህበራዊ ድረገጾችን መዝጋቱን እንደዚሁም ተቃዋሚ እና በመንግስት ላይ ትችት የሚያቀርቡ ድረገጾች በሀገሪቱ እንዳይነበቡ ማገዱንም በማስረጃነት ጠቅሷል፡፡  

በኢትዮጵያ ያለውን የኢንተርኔት አገልግሎት በአህጉሪቱ “የከፉ” ከሚባሉት መካከል የመደበው “ሎንሊ ፕላኔት” ነገሮች ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ ቢሆንም የኢንተርኔቱ “ባንድ ዊድዝ” በቂ አይደለም ይላል፡፡ ሌሎች በርካታ ጥናቶችም ይህን ይጋራሉ፡፡ ብዙዎች ለዘገምተኛው የኢትዮጵያ ኢንተርኔት ተጠያቂ የሚያደርጉት ብቸኛውን የአገልግሎቱን አቅራቢ ነዉ።ኢትዮ- ቴሌኮም።  የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በዘርፉ የግል ኩባንያዎች እንዳይሰማሩ በመከልከሉ ኢትዮ- ቴሌኮም እንዳሻው አዛዥ ናዛዥ መሆኑ ዘርፉን እንደጎዳው ይናገራሉ፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ስራቸውን እንኳ በቅጡ ማከናወን አለመቻላቸውን በማንሳትም ያማርራሉ፡፡

መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ኢትዮ- ቴሌኮም ዘወትር ቅሬታ በሚቀርብበት በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ከግል ኩባንያዎች ጋር አብሮ መስራት መጀመሩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ ተደርጓል፡፡ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ለመስራት ከተስማሙ  ኩባንያዎች አንዱ ጂ ቱ ጂ አይቲ ግሩፕ ይሰኛል፡፡ የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሞገስ ጉዳዩ ባለፈው ሳምንት በይፋ ይነገር  እንጂ ስምምነት የተደረሰው ባለፈው ጥር ወር  መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ አይነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ፍቃድ እንዲያገኙ በህግ ከወሰነ ዓመታት መቆጠሩንም ያስረዳሉ፡፡ 

“የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል በህግ እና በፖሊሲ ደረጃ የግል ዘርፉን አስገብቶ በዚህ አሁን በተጀመረው መልኩ ማሰራት የሚቻልበትን ህጉን እና ፖሊሲውን መንግስት አጽድቆ ነበር፡፡ እስከሚተገበር ጊዜ ፈንጂ እንጂ ሀሳቡ አዲስ አይደለም፡፡ ቴሌኮም መስመሩን እና መንገዱን አመቻችቶ የሚሰራበትን እስኪያስተካክል ድረስ ጊዜ ፈጀ፡፡ [እሴት የተጨመረበት አገልግሎት] (Value added service (VAS) የሚባል ምድብ አለ፡፡ ምንድነው? በቴሌኮም በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ያንን የቴሌኮምን አገልግሎት ሊያስፋፋ ይችላል የሚል ነገር ነው፡፡ በዚያ ውስት ስድስት ምድቦች አሉ፡፡ 

አብዛኞቹ እየተሰራባቸው ቆይቷል፤ እኛም ደግሞ ስንሰራበት ቆይተናል፡፡ ምናልባት በደንብ የሚታወቀው የSMS አገልግሎት ነው፡፡ የጥሪ ማዕከል (call center) አገልግሎት እንደ 8123 ያሉትን የጥሪ ማዕከል አቋቁመው በዚያ በ VAS ምድብ ሲሰሩበት ቆይተዋል፡፡ የግል ዘርፉን አሳትፎ ማሰራት የሚለው ነገር የተጀመረው በሲም ካርድ ነበረ፡፡ በሲም ካርድ ላይ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ሲያደርግ የሲም ካርድ ሽያጭ ጣሪያ ነካ፡፡ እና ያንን የቴሌኮም ዘርፍ በዚያ ስራ ስላሰፋ እንደዚሁ እሴት እየጨመሩ የግል ኩባንያዎች ቢሳተፉ ተጨማሪ ቢዝነስ ያመጣሉ የሚል እምነት አለ፡፡ ደግሞ ተረጋግጧልም፡፡ እና አሁን ምንድነው? በመጨረሻ የቀረው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ነበር፡፡ ለእርሱ እንግዲህ እኛ የተፈራርመነው በጥር ነው፡፡ ግን ያው አመቻችተን፣ ቴሌኮምም ከፍለን፣ አንዳንድ ነገር አዘጋጅተን እስክምንል ድረስ ያው የተወሰኑ ወራቶች ፈጁ” ሲሉ ለምን ይህን ያህል እንደዘገየ ያብራራሉ።

 መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ጂ ቱ ጂ አይቲ ግሩፕ አሁን የጀመረውን የኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዙ አራት ዘርፎች የተሰማራ ድርጅት ነው፡፡ ኩባንያው ለጊዜው የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለማቅረብ የመረጣቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሰባት ናቸው፡፡ በተለምዶ ቦሌ፣ ሲምሲ (CMC) እና ሃያ ሁለት የሚባሉ አካባቢዎች የኩባንያውን አገልግሎት ያገኛሉ ከተባሉ ቦታዎች መካከል ተካትተዋል፡፡ የኢትዮ-ቴሌኮምን መሰረተ ልማት የሚጠቀመው ኩባንያው የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች የሚያደርሰው የራሱን ሰርቨሮች፣ የማከፋፈያ ማዕከሎች እና የፋይበር መስመር ተጠቅሞ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ይገልጻሉ፡፡

“እኛ ከኢትዮ-ቴሌኮም backbone ወይም የኢትዮ-ቴሌኮምን gateway በመጠቀም ከዚያ ላይ ጥቅል ኢንተርኔት ወይም ጥቅል ባንድዊድዝ አንገዛለን ማለት ነው፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም የእኛ gateway ነው፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ደግሞ ዓለም አቀፍ gateway ይገዛል፡፡ ስለዚህ እነርሱ ከዓለምአቀፍ ሲገዙ እኛ ደግሞ ከእነርሱ እንገዛለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአሰራር ደረጃ ተመሳሳይ የሆነ ቅርጽ አለው ማለት ነው” ይላሉ አቶ ብሩክ።   

ኢትዮ-ቴሌኮም በርካታ ገንዘብ የፈሰሰበት መሰረተ-ልማት መዘርጋቱን የሚናገሩት አቶ ብሩክ ይሄም 99 በመቶ አስተማማኝ የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የሚስተዋለውን ችግር መንስኤ ደግሞ እንዲህ ያብራሩታል፡፡ 

“የኢትዮ-ቴሌኮም ተግዳሮት ምንድነው? The last mile delivery የሚባል ነገር አለ፡፡ የመጨረሻው ኪሎሜትር፡፡ በየሰፈሩ የቴሌ የማከፋፈያ ሳጥኖች አሉ፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ስትመጣ ያለው ችግር ከእነዚያ ሳጥኖች ጀምሮ ደንበኞቹ ጋር አስከ ሚገባው አቅርቦት ድረስ ያለው ነው፡፡ ሰው ሁሉም የሚቸገርበት ያ ነው፡፡ ያለው ችግር ከዚያች ሳጥን ነው፡፡ ወይ ያ ሳጥን ከመጠን በላይ ይጨናነቃል (over congested)፣ ወይም የኃይል ችግር ይኖረዋል፣ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ያ ምን ያደርገዋል? 99.9 በመቶ የሆነውን ዋናውን የቴሌ መሰረተ ልማት ወደ 70 እና 80 በመቶ ያወርደዋል፡፡ ያ ማለት ምንድነው እንደየሰፈሩ እና እንደየቦታው ከ10 እስከ 30 በመቶ የደንበኞች ተሞክሮ ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ይመጣሉ ማለት ነው፡፡ ያንን ችግር ከፈታን የአፕልኬሽን ሰሪዎች፣ የተለያዩ አገልግሎቶች ይበልጥ በማደግ ወይም ደግሞ በመለወጥ ውጤት ያመጣል ብለን እናስባለን፡፡  ምክንያቱም ኢንተርኔት አስተማማኝ ከሆነ ድረስ ውጭ ሀገር ባለው ጥራት መሰረት ማቅረብ ይቻላል ማለት ነው” ሲሉ ኩባንያቸው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ያስረዳሉ።  

በኢትዮጵያ በኢንተርኔት አገልግሎት የሚስተዋለው ሌላው ችግር ከዋጋ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አቶ ብሩክ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም መፍትሄ ማዘጋጀታቸውን ይናገራሉ፡፡ “የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ በጣም ወድ ከመሆኑ የተነሳ ሰው በጣም አነስተኛ ፍጥነት [ያለው] ኢንተርኔት ይወስዳል፡፡ አነስተኛ ኢንተርኔት ይወስድና አሁን ለምሳሌ አንድ ቢሮ አንድ ሜጋባይት ፐር ሰከንድ ቢያዝ፣ እዚያ ቢሮ ውስጥ 10 ኮምፒውተር እና 10 ሰራተኛ ካለ ያ ሜጋባይት ፐር ሰከንድ በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም 10 ሰው እየተጠቀመ ነው፡፡ ያንን  አንድ ሜጋባይት ፐር ሰከንድ ብታካፍለው የሚመጣው 100 ኪሎ ባይት ፐር ሰከንድ ነው፡፡ በዚያ [መተግበሪያዎችን] አፕልኬሽኖችን እና ድረገጾችን ለመጠቀም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው አቅሙ የሚችለውን ስለሆነ የሚወስደው ያንን ወስዶ ለብዙ ነገር ስለሚጠቀምበት ፍጥነቱ ዘገምተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሄ የቴክኖሎጂ ችግር ሳይሆን የዋጋ ችግር ነው ማለት ነው፡፡ ለዚያ ነው እኛ ዋጋችንን በጣም ቅናሽ ያደረግነው ምክንያቱም ብዙ ተጠቃሚዎች እንዲኖሩን እንፈልጋለን” ይላሉ።  

እነ ብሩክ ደንበኞችን ለመሳብ አሁን ካለው ኢንተርኔት ዋጋ እስከ ሃምሳ በመቶ ቅናሽ ለማድረግ አቅደዋል፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ለኢንተርኔት አገልግሎት በሜጋ ባይት 35 ሳንቲም ይጠይቃል፡፡ ጂቱጂ ለድርጅቶች ከአምስት እስከ 20 በመቶ በሆነ ቅናሽ ዋጋ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ከቅናሹ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የታሰቡት ግን የግለሰብ ደንበኞች ናቸው፡፡ 

አቶ ብሩክ ኩባንያቸው ግለሰቦች ላይ ማተኮር የፈለገው በመደበኛ የስልክ መስመር የሚሰጥን የኢንተርኔት አገልግሎት (fixed line service) ለማስፋፋት ካለው ዓላማ በመነሳት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ በሚሰጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ ሀገሮች እንኳ ስትወዳደር ወደ ኋላ መቅረቷን ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ፡፡ በአንጻሩ በተንቃሳቃሽ ስልክ ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ 

የግሉ ዘርፍ በኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት እንዲሳተፉ መደረጉ በኢትዮጵያ በመንግስት ብቻ የተያዘውን የቴሌኮም ዘርፍ ወደ ግል ለማዛወር አንድ እርምጃ አድርገው የሚቆጥሩት አሉ፡፡ በቴሌኮም ዘርፍ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ ባለሀብቶች አንዱ የሆኑት አቶ አዲስ አለማየሁ ደንበኞች አማራጭ ማግኘታቸው ጥሩ ቢሆንም ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ለባለሀብቶች ክፍት ካልተደረገ አሁን ያለው ችግር አይቀረፍም ይላሉ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ የተዘረጋውን የፍጥነት አውራ ጎዳናን በማነጻጸሪያነት በመጥቀስ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

 “ከኢትዮ-ቴሌኮም ብቻ አይደለም ከሌላ አገልግሎት ማግኘቱ እንደ አማራጭ ጥሩ ነው፡፡ ግን ትልቁ ችግር አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው፡፡ ያንን መንገድ ነው ሁሉም ሰው የሚጋራው፡፡ የእዚህ የአዲስ አበባ አዳማ አውራ ጎዳና አለ አይደለም? እስከዛሬ ኢትዮ-ቴሌኮም ብቻ ነው ያንን አውራ ጎዳና የሚያስተዳድረው፤ ደንበኛውም ያንን ነው መጠቀም ያለበት፡፡ አሁን የሆነው ብቸኛ ነገር አንዱን መስመር ለአንድ ድርጅት፣ አንዱን ደግሞ ለሌላኛው ድርጅት አከፋፍለው ሰጡ ማለት ነው፡፡ አማራጭ ወይም ፈጣን የሆነ አውራጎዳና የለም፡፡ 

የተወሰነ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ግን ትልቅ የሆነ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ በዋጋም፣ በአገልግሎትም አሁን ቢሆን በቴሌ ላይ ነው ጥገኛ የምትሆነው፡፡ ያ እስከሆነ ድረስ ለውጥ አያመጣም፡፡ የእኔ አማራጭ ሁለተኛ ቴሌኮም እንዲያውም ሶስተኛ ቴሌኮም ከመንግስት ጋር ይኑር ነው፡፡ መንግስት ድርሻ ይወሰድ፣ ህዝቡ ደግሞ ሌላ ድርሻ ወስዶ ሌላ ሁለተኛ ድርጅት ይፈጠር፡፡ ያኔ እውነተኛ መሰረታዊ ለውጥ ታያለህ፡፡ ውድድር ይኖራል፡፡ በአገልግሎትም፣ በዋጋም፣ በሁሉም ነገር ያኔ ለውጥ ታያለህ፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን ለውጥ አያለሁ ብዬ አላምንም” ይላሉ አቶ አዲስ።

አቶ አዲስ የቴሌኮም ዘርፉን ልክ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደተደረገው ለውጭ ድርጅቶች መስጠት ሳያስፈልግ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ድርጅቶች መስራት ይቻላል ባይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በአክሲዮን የግል ባንኮች እንዳቋቋሙት ሁሉ የቴሌኮም ድርጅቶችም መመስረት ይችላሉ ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ በየሀገሩ በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ አዲስ በባለሙያም በኩል ሀገሪቱ እምቅ አቅም እንዳላት ይመሰክራሉ፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic