ኢትዮጵያ የድርድር አማራጭ ይኖር ይሆን? | ዓለም | DW | 25.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ኢትዮጵያ የድርድር አማራጭ ይኖር ይሆን?

በርስበርስ ግጭትና ፖለቲካዊ ቀዉስ ጊዜ የየሐገሩ ምሁር፣ ታዋቂ ሰዎችና ሽማግሌዎች ይሳካም አይሳካ ብዙ ሙከራዎችን አድርገዋል።ኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያዉያን ደሕንነት የሚያሳብ፣ «እብዶቹን ለመፈወስ» የሚመክር ወይም የሚሞክር ምሁር አላት ይሆን?

የኢትዮጵያ ቀዉስ ያደረሰዉ ጥፋትና መፍትሔዉ

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን ያዉ እንደወታደር  «አንድ ቆጥ ላይ ሁለት አዉራ አይሰፍርም» ያሉ መስለዋል-ዛሬ።አሉም አላሉ ሱዳን ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት በጠቃቀስነዉ ፖለቲካዊ ፍቲጊያ ጄኔራሎቹ የበላይነታቸዉን እያረጋገጡ ነዉ።ከሱዳን ደቡብ ምሥራቅ የአዲስ አበባ-ባሕርዳር ፖለቲከኞች፣ ከመቀሌ ባላንጦቻቸዉ ጋር የገጠሙት እስጥ አገባ፣ አምና በጫሩት ጦርነት ንሮ ዛሬም የሺዎችን ሕይወት፣አካል፣ሐብት ንብረት እያጠፋ፣ ሚሊዮኖችን ለረሐብ-መፈናቀል ዳርጎ ቀጥሏል።አሸናፊና ተሸናፊ መኖሩ ሲበዛ ያጠራጥራል።ለድርድር፣ ዉይይት፣ ሰላማዊ መፍትሔም ጊዜዉ በርግጥ መሽቷል።«አልጨለመም» ማለት ይቻል ይሆን? ባለሙያ አነጋግረናል ላፍታ እንጠይቅ።

                                            

ዛሬ ከመቀሌ ደሴ ጥግ የደረሱት የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አብዛኞቹ ፖለቲከኛ-የጦር አዋጊዎች የሚያዙት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ተዋጊዎች ደብረ-ታቦር፣ ወይም ሐሙሲት ጥግ መድረሳቸዉ በሚዘገብበት ወቅት፣ የያኔዉ ወጣት ኢትዮጵያዊ ባይሳ ዋቅወያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያ ሆኖ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በጦርነት ከምትተረማማሰዉ አፍቃኒስታን ገባ።

በትምሕርት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸዉ።ዛሬ ግን የግጭት ጦርነቶችን አስከፊነት በመገናኛ ዘዴ ሰምተዉ፣ ከመፀሐፍ አንብበዉ ወይም ክፍል ዉስጥ ተምረዉ ሳይሆን አይተዉ ያወቁ፣አንዳድ ሥፍራ መፍትሔዉን ጠቁመዉ ያቃለሉ፣ የሰላሳ ዓመት ልምድ ያካበቱ የዓለም አቀፉ ድርጅት ባለስልጣን የነበሩ ናቸዉ።አንቱም ጭምር።ባይሳ ዋቅ ወያ።

 «የርስ በርስ ጦርነት ሰዉን ባጭር ጊዜ ከሰዉነት ወደ አዉሬነት ይቀይራል» ይላሉ።ዩጎዝላቪያን የበታተነዉ ጦርነት ሲጫር ክሮኤሺያ ነበሩ።ከዕለታት አንድ ቀን የሚኖሩባት ከተማ ነዋሪዎች ባንድ ኃይማኖታዊ ድግስ ላይ እንዲገኙ ጋበዟቸዉ።አልቀሩም።ቄሱ ለእድምተኞች በግ ሲያርዱ አዩ።ሲባርክም ሰሙት።ደነገጡ።«ሰቀጠጠኝ» ይላሉ «ኢትዮጵያ ዉስጥም እንደዚያ ነዉ» ቀጠሉ።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ አቀንቃኞች «እብደት» ከጀመሩ 50 ዓመት አልፈ አከሉም።

                                    

እብደቱ ኢሕአፓን፣ መኢሶንን፣ኢዲሕ፣ጀበሐን ወዘተ ሲያዳካም ወይም ሲያጠፋ፣ ሻዕቢያን ሲያጠረቃ ሕወሓቶች ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ተካፋዮች ነበሩ።እብደቱ ደርግን ሲያስወግድ፣ኤርትራን ሲያስገነጥል፣ ኢሕአዴግን ምንኒሊክ ቤተ-መንግሥት ሲዶል ሕወሓቶች ዋና ተዋኞች ነበሩ።

እብደቱ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ሲያዋጋ የጠቡ ጫሪ-መሪ አስተባባሪዎች ሕወሓቶች ነበሩ።እብደቱ ከአዲስ አበባ እስከ ጋምቤላ፣ ከፊንፊኔ እስከ ጂጂጋ፣ ከሰመራ-እስከ ድሬዳዋ፣ ከባሕርዳር እስከ ሐረር፣  ከአሶሳ እስከ ሐዋሳ  የሚገኙ ፖለቲከኞችን ሲፈለፍል፣ አስፈልፋዩ ሕወሓት ነበር።እብደቱ የሕወሓት መራሹን ኢሕአዴግ-በኦሕዴድ መራሹ ኢሐአዴግ ሲተካ፣ ዛሬ ከመቀሌ እስከ ደሴ የሚገኘዉን ግዛት የሚቆጣጠሩት ፖለቲከኞች ዋና ተዋኝ ነበሩ።

ጠበልም-ዱዓም፣ ፆሎት-ምሕላ ሐኪምም የማያድነዉ እብደት የስንት ኢትዮጵያዉያን ደም፣አካል፣ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት ጭዳ ቢደረግለት ይሶረፋል? ስንት ሕፃን፣ስንት እናት፣ ስንት አዛዉንት በረሐብ መማቀቅ፣በፍርሐት መሳቀቅ፣ በስደት መሸማቀቅ አለባቸዉ? ደግሞስ እስከ መቼ?አይታወቅም።አለመታወቁ ነዉ ሰቀቀኑ።

                                

አቶ ባይሳ በሰሩና በጠቀሷቸዉ ሐገራት የተደረጉና የሚደረጉ የርስበርስ ግጭቶችን ለማርገብ ወይም «እብደቶችን ለመፈወስ»  ዓለም አቀፍ ከሚባለዉ ማሕበረሰብ እስከ አካባቢ እድርና ማሕበራት ብዙዎች ብዙ ጥረዋል።በተለይ በርስበርስ ግጭትና ፖለቲካዊ ቀዉስ ጊዜ የየሐገሩ ምሁር፣ ታዋቂ ሰዎችና ሽማግሌዎች ይሳካም አይሳካ ብዙ ሙከራዎችን አድርገዋል።ኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያዉያን ደሕንነት የሚያሳብ፣ «እብዶቹን ለመፈወስ» የሚመክር ወይም የሚሞክር ምሁር አላት ይሆን?

                                            

አቶ ባይሳ በጠቀሱት ሐምሳ ዓመት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልተለዩት ሕወሓቶችና ሕወሓቶች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ለመሪነት ያበቋቸዉ ፖለቲከኞች ዛሬ አንዱ ሌላዉን «አሸባሪ»፣ «ሁንታ» እና «ፋሽስት» እየተባባሉ።ደጋፊዎቻቸዉንም እያስባሉ-እያጋደሉም ነዉ።ተፋላሚ ኃይላት ተኩስ አቁመዉ ልዩነታቸዉን በድርድር እንዲፈቱ ለሚደረገዉ ጥሪና ግፊት እስካሁን ቀና መልስ አልሰጡም።የጦርነቱ ጊዜ እየረዘመ አመት ተቃረበ።የሚሞት፣የሚፈናቀል፣ የሚራበዉ ሕዝብ ቁጥርም ዕለት በዕለት እየጨመረ ነዉ።የሰላም አማራጭ ይገኝ ይሆን?  «ከድርድር ሌላ ሌላ አማራጭ የለም» ይላሉ አቶ ባይሳ።ግን እንዴት?

                                       

አሁንም ሠላም ለኢትዮጵያዉያን በርግጥ ሩቅ ናት።ለፈለጋት ግን ዛሬ ማዝገም ከጀመረ መድረሱ አይቀሩም።ባንድ ቆጥ ላይ ሁለት አዉራ አይሰፍርም።አንዱን አስፋሪዉ ግን፣ ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንደሚሉት  አፈሙዝ ሳይሆን የሕዝብ ድምፅ መሆን አለበት።በጎራዴ የኖረ በጎራዴ ይሞታል እንዲሉ ነዉና።ሙሉ ቃለ መጠይቁን መስማት የምትፈልጉ አምደ መረባችን ጎብኙ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

 

 

                                                 

  

 

Audios and videos on the topic