ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ወቅታዊ ግንኙነት "ሰላማዊ" ነው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሐሙስ፣ መስከረም 30 2017የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ወቅታዊ ግንኙነት "ሰላማዊ" ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገለፁ።
የአዲስ አበባ እና የአስመራ ግንኙነት "በነበረበት ሁኔታ እንደቀጠለ ነው" ያሉት ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው "ሁለቱ ሀገራት መልካም ጉርብትና እና ወዳጅነት አላቸው" ሲሉ ወደ ኤርትራ ሲደረግ የቆየው መደበኛ የስልክ አገልግሎት ስለመቋረጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አካባቢውን ለማተራመስ ከሚጥሩ ጋር ትንቀሳቀሳለች ያለቻትን ሶማሊያን አስጠነቀቀች
ሊባኖስ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ 51 ኢትዮጵያውያን በጆርዳን እና በካይሮ አየር መንገዶች በኩል መውጣታቸውን የገለፁት ቃል አቀባዩ፣ እስካሁን ከ 3 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።//
በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ቤይሩት ሊባኖስ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ የተባሉ 51 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከመደረጉ በተጨማሪ እዚያው በሚገኘው ቆንስላ ጽ/ቤት እስካሁን ከ 3 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አመባሳደር ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል። ሥራው የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት መሆኑንም ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤይሩት የሚያደርገውን በረራ በማቋረጡ እነዚህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በሌሎች አየር መንገዶች መሆኑንም ገልፀዋል። እንደታሰበው ሰዎች በስፋት ሊመዘገቡ አለመቻላቸውን፣ የሰነድ ማጣራት ሥራዎች አሁን የሚጠየቁ አለመሆኑን ሆኖም ግን ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በአግባቡ እየተጣራ የሚመዘገቡ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ አፍሪቃ ሕብረት ምን አለ?
የተባበሩት መንግሥታት በአማራ ክልል በረድዔት ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጥቃት ተከትሎ መሠረታዊ የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የሚያቀርበውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቋረጥ ውጥን መያዙ ተጠቅሶ የመንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ "ጉዳዩ ለእኔ አዲስ ነው" በማለት በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ትናንት ለዶቼ ቬለ በሰጠው ምላሽ ግን እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች "ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ናት ብሎ ዓለም አቀፋዊ ድምዳሜ የመስጠት" ፍላጎት እንዳላቸው በመግለጽ ሆኖም ግን "መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም" የመሸፈን ንቅናቄ ውስጥ መሆኑን ተናግሮ ነበር።
ኢትዮጵያ ከ2025 እስከ 2027 ዓ.ም ባሉት ሦስት ዓመታት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ም/ቤት አባል ሆና መመረጧን የገለፁት ቃል አቀባዩ በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ጉዳዮች በስፊው ማስገንዘብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ ያደርግ የነበረው በረራ መቋረጡ ቀድሞውኑ የታወቀ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት መደበኛ የስልክ አገልግሎት ስለመቋረጡም ከትናንት ጀምሮ ተሰምቷል። ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ሁለቱ ሀገራት አሁንም መልካም ጉርብትና እና ወዳጅነት እንዳላቸው ከመግለጽ በቀር ስለ ጉዳዩ እንዲህ ነው አላሉም።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ