1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስት የሥልጣን ዓመታት

Eshete Bekele
እሑድ፣ መጋቢት 29 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበት ስድስተኛ ዓመት ደጋፊዎቻቸው በሰልፍ ተቃዋሚዎቻቸው በትችት አስበውታል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ጆን አሕመድ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ሙከርም ሚፍታህ፣ ከጁሐንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ዶክተር ሰይፈ ታደለ የተሳተፉበት ውይይት ለመሆኑ ዐቢይ ምን አሳክተው ምን አጎደሉ? ሲል ያጠይቃል

https://p.dw.com/p/4eVSP
ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መጋቢት 24 ቀን 2010 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ-መሐላ ሲፈጽሙ
ዐቢይ አሕመድ ከውጪ በተቃውሞ ከውስጥ በአለመግባባት ችግር ውስጥ የወደቀው የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር ሆነው በመመረጣቸው ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በመተካት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት መጋቢት 24 ቀን 2010 ነበር። ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

እንወያይ፦ኢትዮጵያ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስት የሥልጣን ዓመታት

ዐቢይ አሕመድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀ-መንበር ሆነው ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መጋቢት 24 ቀን 2010 ከኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲረከቡ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ የታሰሩ ተፈቱ፤ የተሳደዱ ፖለቲከኞችም ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት የገባችበትን ፍጥጫ የቋጩት ዐቢይ የሰላም የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል።

ዐቢይ ሥልጣን ሲይዙ የፈነጠቀው ተስፋ ግን እንደ ጅማሮው አልዘለቀም። ከ600 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ የሚታመንበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና የኤርትራ ተሳትፎ ዐቢይ በኃይል ከሚወቀሱባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። ጦርነቱ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ብርቱ ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ቢሆን የዐቢይ ስድስት የሥልጣን ዓመታት በተለይ የግጭት እና የመፈናቀል ጥላ የተጫናቸው ሆነው ይታያሉ። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የበረታው ግጭት አሁንም ማባሪያ አላገኘም።

ሦስት እንግዶች የተሳተፉበት ውይይት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስት የሥልጣን ዓመታት እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ፈትሿል። በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ጆን አሕመድ፣ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሙከርም ሚፍታህ እና በደቡብ አፍሪካ ጁሐንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሰይፈ ታደለ ተሳትፈዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ