1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት ግድያዉ ማብቂያ ያገኝ ይሆን?

ሰኞ፣ ጥቅምት 24 2012

ኢትዮጵያ ለአዲሱ መሪዋ አዲስ የሰላም ጥረት፣ የዓለምን ታላቅ የሰላም ሽልማት ባስጠለቀች ማግሥት ዘንድሮም እንደ አምና ሐቻምናዉ ለዘር-ኃይማኖት ጥላቻ እኩይ ዛሯ የ86 የዋሕ ዜጎችዋን ሕይወት ጭዳ አደረገች።አዳማ አረገደች።ዶዶላ አንቋረረች።ከድሬዳዋ አስከ ወለቴ ደም-የሰዉ ደም አቀረሹ።

https://p.dw.com/p/3SRnt
Unterstützer von Jawar Mohammed versammeln sich in Addis Abeba
ምስል AFP/Stringer

ኢትዮጵያ አዳኝ ያጣች ሐገር

አምና መስከረም፣ የሐቻምናዉ የኦሮሚያ-ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ግጭት-ግድያ፣ መፈናቀል ካያለፈ ታሪክ ጋር ያለፈ መስሎን፣ ቡራዩ በነዋሪዎችዋ ደምና አስከሬን መርከስ-መጉደፏ አሸማቆን ጉድ-አጃቢ አሰኝቶን ነበር።አምናን ቅማት፣ባሕርዳር፣ ጉሙዝ፣ ካማሺ፣ ቴፒ፣ ጌዲዮ፣ምዕራብ ወለጋ፣ ሲዳማ ወዘተ እያልን ከተማ-መንደር፣ ቀበሌ ወረዳ እየዘረዘርን እስከሬን ሲቀበር፣ ቁስለኛ ተፈናቃይ ስንቆጥር፣የጠፋ ሐብት ንብረት ስናሰላ ከሚያልፈዉ ዓመት ጋር የሚያልፍ መስሎን ነበር።ግን ቀጠለ። ኢትዮጵያ ለአዲሱ መሪዋ አዲስ የሰላም ጥረት፣ የዓለምን ታላቅ የሰላም ሽልማት ባስጠለቀች ማግሥት ዘንድሮም እንደ አምና ሐቻምናዉ ለዘር-ኃይማኖት ጥላቻ እኩይ ዛሯ የ86 የዋሕ ዜጎችዋን ሕይወት ጭዳ አደረገች።አዳማ አረገደች።ዶዶላ አንቋረረች። ከድሬዳዋ አስከ ወለቴ ደም-የሰዉ ደም አቀረሹ።ለምን ደግሞስ እስከመቼ?

 ኢትዮጵያ ዳግማዊት ሶማሊያን፣ ላይቤሪያን ወይም አዲስ አበባ ሞቃዲሾን ወይም ሞንሮቪያን ይሆናሉ የሚል ሥጋት አጥልቶ የነበረዉ የኢሠፓ-ሥርዓት ፍፃሜ የኢሕአዴግ ሥርዓት ጅምር በታየበት በ1983 አጋማሽ ነበር።በርግጥም በርስ ጦርነት ደም ስትቃባ ከሰላሳ ዘመን በላይ ያስቆጠረችዉ፣ሰሜናዊ ክፍለ-ሐገሯ የተቆረሰባት፣ የ80 ብሔሮች፣ የብዙ ኃይማኖች ሐገር፣ እንደ ቀዳሚዎችዋ የልቂት-ፍጅት ጥፋት አዉድ የመሆንዋ መጥፎ እጋጣሚ በግልፅ የሚታይ ነበር-ያኔ።

የኦሮጌዉ ሥርዓት ሹማምንት አንድም ተሸሽገዉ ሁለትም ተማርከዉ፣ ከጫካ የመጡት የወደፊት ገዢዎች በቅጡ ሳይደላደሉ እንበለ መሪ-አስተባባሪ የቀረዉ ሕዝብ፣ ያለ አዛዥ ከነጠመጃዉ የተበተነዉ ሠራዊት፣ ብዙዎች እንደመሰከሩት የተፈራዉን እልቂት ፍጅት ካከሸፈባቸዉ ምክንያቶች ሁለቱን ብዙዎች ብዙ ጊዜ ይጠቅሷቸዋል።

አብዛኛዉ ህዝብ ከዘር-ሐይማኖት ልዩነቱ በላይ አንዱ ያለሌላዉ መኖር አለመቻሉን ማሰቡ፣ ታጣቂዉ ወይም ጉልበተኛዉ ሊዘርፍ ከሚችለዉ ሐብት ንብረት በላይ ኢትዮጵያዊ ወገኑን የራሱን ያክል እንዲያከብር፣ እንዲወድና እንዲመለከት ተደርጎ የመኮትኮቱ ስነልቡና ማየሉ-አንድ።የየመንደር ቀበሌዉ የዕድር-ሰንበቴ መሪዎች፣የየአብያተ-ክርስቲያን-መሳጂድ አስተዳዳሪዎች ወይም ሽማግሌዎች መሪ አልባዉን ሕዝብ ማስተባበራቸዉ-ሁለት።

ለዝንተ-ዓለም የፀናዉ የመተዛዘን-መደጋገፍ ስነ-ልቡና ሰላሳ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ያልነበር ያክል መጥፋቱ እንደ ሰዉ ለሚያስብ ኢትዮጵያዊ በርግጥ ያሳዝናል።የከፋዉን አጥቀስም። ግን ሰሞኑን እንዳታዘብነዉ ኢትዮጵያ ወጣቶች-አዛዉንቶችን የሚገድሉባት፣ ባል እሚስት ፊት የሚሰይፍባት፣ ሕፃናት የሚበተኑባት፣ በ50-60 ዓመት ድካም የተጠራቀመ ጥሪት የሚጋይባት ሐገር መሆንዋ አያስዝንም።ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል፣ ይሰቀጥጣል እንጂ።የስብስብ ለኢትዮጵያ ሰባዊ መብቶች የበላይ ሐላፊ ያሬድ ኃይለ ማርያም እንደሚሉት የግጭት ግድያዉን ሁኔታ፣ ለማየት አይደለም ለመስማትም ይዘገንናል።

Äthiopien Religiöse Führer
ምስል DW/S. Muchie

ጭናቅሰን፣ ቡራዩ፣ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ቅማንት ብቻ አይደለም፣ባሕርዳር፣ ሐዋሳ፣ ጉሙዝ ምዕራብ ወለጋ ብቻ አይደለም።አዳማ፣ ዶዶላ፣ድሬዳዋ ብቻ አይደለም።ሁሉምጋ። ሐቻምና፣አምና ብቻ አይደለም-ዘንድሮም እንጂ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዕለት ጉርሱ እየሸረፈ የሚከፍለዉ ግብር በሚከፍለዉ ልክ ጤና፣እዉቀት፣ መሰረተ ልማቱን ለማስፋፋት አለመዋሉ ካንዴ በላሕ ሕዝብን አሳምፆ ሥርዓት አስለዉጧል።

ከሕዝብ ከተሰበሰበ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የሚፈስለት የፖሊስ፣ የመረጃ፣የአስተዳደርና የመከላከያ ጦር የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት ካላስከበረ ሥራ-ኃላፊነቱ ዛሬ በርግጥ ሊያጠያይቅ ይገባል።የሕግ ባለሙያ ተማም አባቡልጎ እንደሚያምኑት አጠያያቂዉ ነገር የፀጥታ አስከባሪዉ ብቃት ወይም ኃላፊነት ብቻ አይደለም። አጠቃላይ የመንግስት ብቃትና ፍላጎት ጭምር-እንጂ።

አቶ ያሬድ ደግሞ መንግስት ሕግና ስርዓት ለማስከበር አቅምና ተቋማት አላጣም ባይ ናቸዉ።ግን «ዳተኛ» ነዉ።

ሶማሊያ ስትፈርስ ሶማሌዎችን እንዳቅሟ ረድታለች።ላይቤሪያ ድረስ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት አዝምታለች።ሩዋንዳ፣ የጎሳ ዛር ባሳበዳቸዉ ፖለቲከኞዋ ወደ አስከሬን መከመሪያነት ስትቀየር ቀድመዉ ከደረሱ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ሱዳኖችን የመሸገላቸዉ ስኬት-ሲዘገብ የሚመሩትን ሕዝብ የሚያፋጀዉን የዘር፣የሕይማኖት ወይም የቦታ ይዞታ ጠብን ለማቃለል አይገዳቸዉም የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር።ተስፋዉ በርግጥ በንኗል።ጠቅላይ ሚንስትሩ የተወሳሰበዉን የጠብ መነሻ ቀርቶ የአፋርና የኢሳ (ሶማሌን) ግጭት ለማቃለል እንኳ እስካሁን የፈየዱት ነገር የለም።አቶ ተማም እንደሚሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መንግስታቸዉም ሆነ ፀጥታ አስከባሪዉ የቀድሞዉ ሥርዓት ዉርስ በመሆናቸዉ ሕግና ሥርዓትን በሚፈለገዉ ደረጃ እንዲያስከብሩ መጠበቅ ስሕተት ነዉ።                                    

አቶ ያሬድ በበኩላቸዉ መንግስትና ባለስልጣናቱ የተለያዩ ሰበቦች እየሰጡ ከችግሩ እየሸሹ ነዉ ባይ ናቸዉ።

86 ኢትዮጵያዉያንን የገደለዉ ግጭትና ጥፋት ከተጀመረ የፊታችን ሮብ ሁለተኛ ሳምንቱ።የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ቃል አቀባይ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ በግጭት ቀስቃሽ፣ ገዳይ አስገዳይነት የተጠረጠሩ ከ400 በላይ ሰዎች መያዛቸዉን አስታዉቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት በመገናኛ ዘዴ ባሰራጩት መልዕክት የሟቾችን ዘርና ኃይማኖት ከመዘርዘር ባለፍ በተጠርጣሪዎች ላይ ስለሚወሰደዉ ሕጋዊ እርምጃ ያሉት ነገር የለም።በግጭቱ በርካታ ሰዉ የተገደሉባቸዉን አካባቢዎች እስከዛሬ አልጎበኙም።መንግሥታቸዉ ለሟች ቤተሰቦች፣ለቁስለኞች፣  ለተፈናቃዮች፣ ሐብት ንብረት ለጠፋባቸዉ ዜጎች ካሳ ለመስጠት ስለመዘጋጀት አለመዘጋጀቱ ያሉት ነገር የለም።ግጭቱን የቀሰቀሱ፣ ያባባሱ፣ለሌላ ግጭት የሚዝቱ ባለስልጣናትና ሌሎች ኃይላት በሕግ ስለመጠየቅ አለመጠየቃቸዉ ከጠቅላይ ሚንስትሩ የሰማነዉ ነገር የለም።

ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሐብት ንብረታቸዉ ሲጠፋ ጠመንጃዉን ታቅፎ በየስፍራዉ ተወሽቆ የነበረዉን ፖሊስ፣ አዛዦቹንና የአካባቢ ባለስልጣናትን መንግሥት መቅጣት አለመቅጣቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ አልነገሩንም።የሰባዊ መብት ተሟጋቹ የጠቅላይ ሚንስትሩን መግለጫ «ገለባ» ብለዉታል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office Of The Prime Minister

 ሐቻምና ጂጂጋ፣ ጭናቅሰን፣ሚኤይሶ፣ ሞያሌ ነበር።አምና ቡራዩ፣ጌድኦ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ጉሙዝ፣ቅማንት፣ ሲዳማ እያለ ቀጠለ።ዘንድሮ ከአዳማ እስከ ዶዶላ ሕዝብ በተወዳጅ-ልጅ-ዉላጁ፣ ዘመድ-አዝማዱ ሞት ልቡ ተሰበረ።ለከርሞስ መቆሚያ ይበጅለት ይሆን? አቶ ተማም ለየትያለ ቅደመ ሁኔታ ሊኖር ይገባል ባይ ናቸዉ።ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት መመስረት።ይሆን ይሆን!? ወይስ? ብቻ እስኪ እንደገና ቸር ያሰማን እንበል።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ