1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ኢትዮጵያውያን ቲክቶከሮች ስለቲክ ቶክ መታገድ ምን ይላሉ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ቲክ ቶክ ከቻይናው ኩባንያ ባይትዳንስ እጅ እስካልወጣ ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ እገዳ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ህግ ያለፈው ቅዳሜ አጽድቋል።ያ ለመሆኑ ቲክ ቶክ ቢታገድ በይዘት ፈጣሪዎች እና በተጠቃሚዎች ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል?

https://p.dw.com/p/4fM0x
Symbolbild TikTok USA
ምስል Olivier Douliery/AFP

ቲክ ቶክ ቢታገድ በይዘት ፈጣሪዎች ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል?

የአሜሪካ ህግ አውጭዎች  ታዋቂው የቪዲዮ ማጋሪያ ቲክ ቶክ አሜሪካ  ውስጥ ለመስራት ከቻይና  ኩባንያ ባይትዳንስ እንዲነጠል ይፈልጋሉ።ያ ካልሆነ ግን  መተግበሪያውን በሀገሪቱ እንደሚያግዱ እየገለጹ ነው ።ለመሆኑ ቲክ ቶክ ቢታገድ በይዘት ፈጣሪዎች እና በተጠቃሚዎች ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል?  
የዩኤስ አሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ቲክ ቶክ ከቻይናው  ኩባንያ  ባይትዳንስ/ByteDance./ እጅ እስካልወጣ ድረስ በሀገሪቱ ውስጥ እገዳ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ህግ ያለፈው ቅዳሜ አጽድቋል። ታዋቂውን የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያን ለማገድ የሚያስችለው ረቂቅ ህግ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ህጉ እሳቸው ዘንድ የሚደርስ ከሆነ ያለማወላወል እንደሚያፀድቁት ቃል ገብተዋል።ቲክ ቶክ በበኩሉ ይህ ህግ  ስራ ላይ ከዋለ  የ170 ሚሊዮን አሜሪካውያንን የመናገር መብት ይጥሳል፣ የ7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የንግድ እንቅስቃሴንም ይጎዳል ሲል አስጠንቅቋል። ይህም ቲክ ቶክ ለአሜሪካ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያደርገውን የ24 ቢሊዮን ዶላር (22.5 ቢሊዮን ዩሮ) መድረክ ይዘጋል ብሏል።  
በቲክ ቶክ ዕገዳ ኢትዮጵያውያን የይዘት ፈጣሪዎች ምን ይላሉ?

ለመሆኑ ቲክ ቶክ ቢታገድ በይዘት ፈጣሪዎች ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል? ዶቼ ቤለ ያነጋገረው፤ ኤልሻዳይ ውበቱ 700 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት «የሸገር ገበታ» የሚል ምግብ ቤቶችን የሚያስተዋውቅ የቲክ ቶክ ገጽ አለው።  ወደ 30 በመቶ የሚሆኑት ተከታዮቹ በአሜሪካ የሚገኙ መሆናቸውን የሚገልፀው ኤልሻዳይ  በአንድ ቪዲዮ አነሰ ከተባለ እስከ ሁለት መቶ ሺህ በዛ ከተባለ እስከ አምስት መቶ ሺህ ዕይታ ያገኛል። ስለሆነም የቲክ ቶክ መታገድ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ እንዳለው ይገልፃል። 

ኤልሻዳይ ውበቱ 700 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት «የሸገር ገበታ» የሚል የኢትዮጵያ ምግብ እና ምግብ ቤቶችን የሚያስተዋውቅ የቲክ ቶክ ገጽ አለው። 
ኤልሻዳይ ውበቱ 700 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት «የሸገር ገበታ» የሚል የኢትዮጵያ ምግብ እና ምግብ ቤቶችን የሚያስተዋውቅ የቲክ ቶክ ገጽ አለው። ምስል Privat

ኤልሻዳይ እንደሚለው  ቲክ ቶክ ምንም እንኳ በግሉ ነፃነት ቢያሳጣውም፤ ራሱን በማስተዋወቅ  ለብዙ የስራ ዕድሎች በር ከፈቶለታል። ከእርሱ የግል ህይወት ባሻገርም ቲክ ቶክ በመዝናኛው ዘርፍ በተለይ በሙዚቃ ስራ ላይም  አስተዋፅኦው ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳል። 
ሌላው ዶቼ ቬለ ያነጋገረው የቲክ ቶክ ይዘት ፈጣሪ ወንድማገኝ ተስፋዬ በቲክ ቶክ ስሙ ራቼ፤ አዝናኝ እና አስቂኝ በሆነ መልኩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን/Satire comedy/ በቲክ ቶክ ያቀርባል። ራቼ በሚለው የቤት ስሙ በከፈተው  የቲክ ቶክ ገፅ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤ የቲክ ቶክ መዘጋት ታዲያ በቀላሉ መድረክ አግኝተው ተሰጧቸውን ማውጣት የቻሉ እንደ እርሱ አይነት ወጣቶችን ዕድል እንደሚነፍግ ይናገራል። 

«አሁን ከዚህ በፊት «ታለንት» የነበረው ሰው «ታለንት» ስላለው ብቻ የመውጣት ዕድሉ «ሬር»ነበር። ቲክ ቶክ ግን ምን አይነት ዕድል ይዞ መጣ አቅም ያለው ሰው «ታለንት» ላለው ለዚያ ሰው መድረክ ነው የፈጠረለት።እና በጣም ቆንጆ «ፕላት ፎርም» ነው።እንደኛ ደግሞ ከቲክ ቶክ በፊት ምንም የነበሩ ግን ይህንን «ሶሻል ሚዲያ» ተጠቅመው የሆነ ሰው መሆን የቻሉ በሰው ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ አንድ ሚሊዮን ተከታይ ማፍራት ለቻሉ ሰዎች ቲክ ቶክ ተዘጋ ማለት ያው የሰዎችን ስራ እና እንጀራ እንደማቋረጥ ነውና ተፅዕኖው ቀላል አይለም።»በማለት የዚህ ዲጅታል መድረክ መዘጋት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አብራርቷል።

ወንድማገኝ ተስፋዬ በቲክ ቶክ ስሙ ራቼ ተስፋዬ፤በቲክ ቶክ ገፁ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤የቲክ ቶክ መዘጋት እንደ እርሱ አይነት ወጣቶች ተስጧቸውን እንዳያወጡ ዕድል ይነፍጋል ይላል።
ወንድማገኝ ተስፋዬ በቲክ ቶክ ስሙ ራቼ ተስፋዬ፤በቲክ ቶክ ገፁ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤የቲክ ቶክ መዘጋት እንደ እርሱ አይነት ወጣቶች ተስጧቸውን እንዳያወጡ ዕድል ይነፍጋል ይላል።ምስል Privat

በቲክቶክ የሚደረጉ የቀጥታ ስርጭቶች  ክፍያ እና ገቢ ከተመልካቾች  በሚገኙ ምዕናባዊ ሽልማቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ይህ መተግበሪያ በአሜሪካ የሚዘጋ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ይዘት ፈጣሪዎች ትልቅ ጉዳት እንዳለውም ይገልፃል።በመላው ዓለም በቀጥታ የሚደረጉ የቲክ ቶክ የጨዋታዎችም ያለ አሜሪካ ታዳሚዎች የሚሆን አይለም ይላል።

የቲክ ቶክ ስለተቀመር ለተወዳጅነቱ አስተዋጽኦ አለው

ቲክ ቶክ በዓለም ላይ 2 5 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በአሜሪካ 170 ሚሊዮን በአውሮፓ ደግሞ 134 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።ይህ ዲጅታል መድረክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እያደገ መሆኑ ይነገራል።በዚህ ሁኔታ ቲክ ቶክ በዓለም ላይ በተለይ በወጣቶች ዘንድ በአጭር ጊዜ ተወዳጅነት ያገኘ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ሲሆን፤ ለዚህም በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ እና ለአጠቃቀም ቀላል መሆኑ የቲክ ቶክን ስልተ ቀመር/Algorithm/ከሌሎች ዲጅታል መድረኮች የተለዬ አድርጎታል። 

ኤልሻዳይም ይሁን ራቼ ቲክ ቶክ አይታገድም የሚል ግምት አላቸው።ያም ሆኖ ቲክ ቶክ የሰዎችን ጊዜ እና ትኩረት በመሻማት ረገድ  የራሱ ደካማ ጎኖቹ እንዳሉት አልሸሸጉም።ቲክ ቶክ ለመረዳዳት የሚውለውን ያህልም የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ማስፋፋቱም ሌላው ስጋት ነው።

ቲክ ቶክ በዓለም ላይ 2 5 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በአሜሪካ 170 ሚሊዮን በአውሮፓ ደግሞ 134 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።
ቲክ ቶክ በዓለም ላይ 2 5 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በአሜሪካ 170 ሚሊዮን በአውሮፓ ደግሞ 134 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።ምስል dpa/picture-alliance

ቲክቶክ በአሜሪካ ለምን ተቃውሞ ገጠመው?

የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት የመተግበሪያው በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነት እየጨመረ በመምጣቱ ቤጂንግ በሀገሪቱ ውስጥ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን እንድትሰልል መንገድ ይከፍታል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።ቲክ ቶክ በባለሥልጣናት ዘንድ ለምን ስጋት አሳደረ?
ለዚህም በምክንያትነት የሚያቀርቡት  በርካታ የቻይና ብሄራዊ ደህንነት ህጎች፤የቻይና ድርጅቶች መረጃ በመሰብሰብ በስለላ እንዲያግዙ መገደዳቸውን ነው። 
የቲክ ቶክ ሀላፊዎች ግን፤ መተግበሪያው ለቻይና መንግስት መሳሪያነት ሊያገለግል ይችላል ወይም የአሜሪካን የተጠቃሚዎች መረጃ ለቻይና ባለስልጣናት ያጋራል የሚለውን ስጋት  ተጨባጭነት የለውም ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።
የሶፍትዌር መሀዲስ የሆኑት አቶ ይግረማቸው እሸቴም የጅኦ ፖለቲካዊ ጉዳይ ካልሆነ ቲክ ቲክ ከሌሎቹ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለዬ ስጋት የለውም ባይ ናቸው። ያም ሆኖ ቲክ ቶክ በኢንተርኔት እንደሚሰራ አንድ መተግበሪያ በግል መረጃ ደህንነት ላይ ስጋት የለውም ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል።ከዚህ አንፃር የአጠቃቀም ህግ እና መመሪያ ማውጣት ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

ህጉ ምን ይደነግጋል?

የአሁኑ ረቂቅ ህግ ባለፈው መጋቢት ወር በምክር ቤቱ የፀደቀውን ለመከለስ የወጣ ሲሆን፤ ረቂቅ ህጉ ለቻይና ባለቤት ባይትዳንስ መተግበሪያውን ለመሸጥ ዘጠኝ ወራት ይሰጣል፣  ሽያጭ የሚያካሄድ ከሆነ ደግሞ የሶስት ወር ማራዘሚያ ሊኖር ይችላል።ከዚያም  የቻይናው ኩባንያ ባይትዳንስ  ተጠቃሚዎችን በፍላጎታቸው መሰረት ቪዲዮዎችን የሚመግብውን የቲክ ቶክ ስልተቀመርን ወይም አልጎሪዝምን ከመቆጣጠር ይታገዳል።

ዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ቲክ ቲክ  በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ቤጂንግ በሀገሪቱ ውስጥ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን እንድትሰልል መንገድ ይከፍታል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ቲክ ቲክ በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ቤጂንግ በሀገሪቱ ውስጥ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን እንድትሰልል መንገድ ይከፍታል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።ምስል The Canadian Press/AP/dpa/picture alliance

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን የአሜሪካ ግምጃ ቤት ፀሀፊ ሆነው ያገለገሉት ስቲቨን ምኑቺን መተግበሪያውን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል። የቻይናው ኩባንያ ባይትዳንስ ቀደም ሲል እንደገለፀው ለአሜሪካ ኩባንያዎች የማይሸጥ ከሆነ ግን፤ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አሁን በፀደቀው ረቂቅ አዋጅ መሰረት ቲክቶክን ሊያግድ ይችላል።

የቲክቶክ እገዳ ተቃውሞ እና ድጋፍ 

የአሜሪካ ህግ አውጪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ቲክቶክን ለማገድ  ተቃርበዋል።ያም ሆኖ ህጉ ተቃውሞ እና ድጋፍ ገጥሞታል።
የህጉ ደጋፊዎች ቤጂንግ በተለያዩ መንገዶች ከአሜሪካ ዜጎች ላይ መረጃ በቀላሉ ማግኘት ያስችላታል፣ ይህም የግል መረጃን በሚሸጡ ወይም በሚከራዩ የንግድ መረጃ ደላሎች እጅ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ።የቲክ ቶክ ዕገዳ አሜሪካውያንን እያወዛገበ ነው
በሌላ በኩል፤ ከህጉ ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የሆነው የቀደሞው ትዊተር አሁኑ X ባለቤት ቢሊየነሩ ኤሎን ማስክ «ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ እገዳ የ X መድረክን ሊጠቅም ቢችልም፤ቲክ ቶክ በአሜሪካ ውስጥ መታገድ የለበትም» ይላል። ኤሎን ማስክ እንደሚለው ይህንን ማድረግ የመናገር እና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚጻረር ነው።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ