በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ
ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ቤይሩት ሊባኖስ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ የተባሉ 51 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዛሬ ማግሰኞ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት "እንደ ፈጣን እርምጃ ባለፈው ሳምንት ከዋናው መሥሪያ ቤት ሁለት ከፍተኛ አመራሮች ቀውስ የተከሰተበት ቦታ ሄደው እገዛ እያደረጉ ነው" ብለዋል።
አክለውም ይሄኛው ጊዜ የአደጋ ወቅት በመሆኑ "በምንም መልኩ ሰነድ አላቸው የላቸውም ሳይባል ቆንስላ ጽ/ቤቱ ማናቸውንም የኢትዮጵያ ዜጎች እንዲመዘገቡ" እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ቤይሩት ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ "ጦርነትን ስንሸሽ እየተከተለን እየተንከራተትን ነው ያለነው" ያለች አንድ አስተያየት ሰጪ ምዝገባ መመዝገባቸውን ገልፃ መንግሥት በፍጥነት እንዲደርስላቸው ተማፅናለች።
አንድ ዓመት የተሻገረው የእስራኤልና የሀማስ ጦርነት አድማሱ ሰፍቶ በሊባኖስ የሚገኘው ሄዝቦላህ ጭምር ገብቶበት፣ ኢራንም ታክላበት ግጭቱ ሊባኖስን የጦር ቀጣና እንድትሆን አድርጓል። ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አደጋ ላይ ወድቀዋል።
መንግሥት ከዚህ በፊት በተለያዩ አገራት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ያቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ቀዳሚ ትኩረቱን እዚህ ላይ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። በዚያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤትም ዜጎችን ከችግር ለማስወጣት ምዝገባ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ቤይሩት የምትኖር አንድ ሴት በምዝገባው መሳተፋን ለዶቼ ቬለ ገልፃለች። "እኛ ከኡንድ ሰፈር ወደ ሌላ ሰፈር ጦርነት እየተከተለን እኛ እየሸሸን ነው ያለነው"።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች አንፃራዊ ደህንነት ወዳለበት የሊባኖስ አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሕፃናት እና ሴቶችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው ብሏል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው
ይህንኑ ገልፀዋል።
"እንደ መጀመርያ ደረጃ እንቅስቃሴ ተመዝግበው ወደ አገር ቤት ለመምጣት ፍላጎት ያሳዩ 51 ኢትዮጵያዊያን በትናንትናው ዕለት ወደ ሀገራቸው ገብተዋል"።
ሌላኛዋ ከሕፃን ልጇ ጋር በቤይሩት በችግር ውስጥ የምትኖር ሴት እዚያ የሚደረግላቸው ድጋፍ እንዳይለያቸው ጭንቅ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሳ ጠይቃለች።
"በፊት የተመዘገቡት ሄደዋል፣ ወረቀት ያላቸው። እንደዛ ብላ ነው ያስረዳችኝ እዛ ውስጥ [ቆንስላ ጽ/ቤቱ] የምትሰራ ልጅ ያስረዳችኝ። በእውነት ነው የምልህ በጣም እየተጉላላ ነው ሕዝቡ"።
በቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት እያደረገ ያለው ምዝገባ ሰነድ አልባ ሆነው በሕገ ወጥ መልኩ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ያካትት እንደሆነ የጠየቅናቸው አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው "ሰነድ አላቸው የላቸውም ሳይል" እየመዘገበ መሆኑን በመግለጽ ዜጎች እየሄዱ እንዲመዘገቡ ጠይቀዋል።
"በምንም መልኩ ሰነድ አላቸው የላቸውም ሳይባል ቆንስላ ጽ/ቤቱ ማናቸውንም የኢትዮጵያ ዜጎች እንዲመዘገቡ እያደረገ ነው"።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሊባኖስን ቋንቋ የሚናገሩ ተጨማሪ ሠራተኞችን ቀጥሮ እያደረገ ያለው ሥራ እንዳለ ሆኖ የተመዘገቡትን በፍጥነት ወደ አገራቸው መመለሱ ላይ እንዲበረታ ኢትዮጵያዊያኑ እየጠየቁ ነው።
ሰለሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ