1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሰመኮ መግለጫ እና የኦሮሚያ ክልል ማስተባበያ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ በተላላፊ በሽታ ምክንያት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሰዎች ማቆያ ስፍራ አለመኖሩን ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/4Wb36
ፎቶ ከማኅደር፤ የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ በተላላፊ በሽታ ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚያመለክት መግለጫ ይፋ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ የኢሰመኮ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ምስል Solomon Muche/DW

የኢሰመኮ መግለጫ እና የኦሮሚያ ክልል ማስተባበያ

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ስፍራ በተላላፊ በሽታ ምክንያት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትናንት ባወጣው መግለጫ ገለፀ። በማቆያ ቦታው ከነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል 190 ሰዎች በሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ያገኙ መሆኑን እና ክትትሉ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ሕክምና እያገኙ እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል። ስለ ጉዳዩ ዛሬ ከዶቼ ቬለ ጥያቄ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ «አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ በክልሉ በሸገር ከተማም ሆነ በፍቼ ከተማ ምንም ዓይነት የማቆያ ስፍራ አለመኖሩን ማረጋገጥ እንወዳለን» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ግን በገላን ከተማ የማደሪያ ቁሳቁስ ፣ በቂ አየር እና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ እና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለበት ማቆያ ቦታ መኖሩን፤ ሌሎች ምርመራ እያደረገባቸው ያሉ ማቆያ ማዕከላት መኖራቸውንም ዐስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የክትትል ግኝት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ  በአብዛኛው ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ በተለምዶ የጎዳና ተዳዳሪዎች በመባል የሚታወቁ ሰዎች ከጎዳና ላይ ተነስተው እንዲቆዩ የሚደረግበት በሸገር ከተማ፣ ሲዳ አዋሽ ወረዳ የሚገኘውን ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ጨምሮ በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ቢሮ ሥር የሚተዳደሩ ማዕከላትን ነሐሴ 24 ቀን፣ እንዲሁም በጳጉሜን 2 እና 3 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. በስፍራ በመገኘት በማቆያ ማእከሉ የሚገኙ ሰዎችን እና የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮን ጨምሮ የሚመለከታቸውን የመንግሥት የፀጥታ አካላት በማነጋገር ክትትል ማካሄዱን ገልጿል። ኮሚሽኑ የማቆያ ማእከሉ አስተባባሪዎችን እና ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን፣ በቦታው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሞያዎችን እና ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኝ የነበረውን የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ኃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በማነጋገር ስለጉዳዩ አስፈላጊ መረጃና ማስረጃዎች ማሰባሰቡንም ገልጿል። በዚሁ ስፍራ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል የሞቱ ፣ ጽኑ ሕክምና ውስጥ የሚገኙ መኖራቸውን የኮሚሽኑ የክትትል ዘገባ ያሳያል። በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ «ይሄ ሂደት ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ [ በአማራ ክልል የታወጀው] በፊትም በኋላም የቀጠለ ነው» ብለዋል።
 

ፎቶ ከማኅደር፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሸገር ከተማ አስተዳደር
«ገላን ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ የሰዎች ማቆያ ቦታ 3 ሰዎች በበሽታ ሞተዋል» ኢሰመኮ፤«በክልሉ ውስጥ ምንም ዐይነት የሰዎች ማቆያ ስፍራ የለም» የኦሮሚያ ክልል ።ፎቶ ከማኅደር፤ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሸገር ከተማ አስተዳደርምስል Seyoum Getu /DW

የኦሮሚያ ክልል የሰጠው ምላሽ


«በማቆያ ማዕከሉ የሚገኙት ሰዎች ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች ሲሆኑ፤ አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችም ይገኙበታል» ያለው ኢሰመኮ በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች በማቆያ ማዕከሉ ውስጥ ይገኙ እንደነበርና ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገበት ወቅት ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች መኖራቸውን ለመረዳት ተችሏል ብሏል። 
በአንጻሩ በክልሉ ምንም የማቆያ ስፍራ የለም ያሉት የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ «ያልተረጋገጠ ሀሰት የሆነ መረጃ በማኅበራዊ መገናኛ ዐውታሮች ሲዘዋወር አይተናል» አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ በክልሉ በሸገር ከተማም ሆነ በፌቼ ከተማ ምንም ዐይነት የማቆያ ስፍራ አለመኖሩን ማረጋገጥ እንወዳለን ብለዋል። 

ኢሰመኮ የተመለከተው ማቆያ ቦታ ምን ይመስላል ?


ኢሰመኮ በገላን ተመለከትኩት ያለው ማቆያ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ምግብ በቀን ሦስት ጊዜ እና የመጠጥ ውኃ የሚቀርብ መሆኑን፣ በአንጻሩ ይህ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ለሰዎች መጠለያ ወይም ማቆያ ተብሎ የተዘጋጀና የተደራጀ እንዳልሆነና ይልቁንም ለኢንዱስትሪ ዕቃዎች ማከማቻ ተዘጋጅቶ የነበረ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል። ስፍራው ለግል ንጽሕና መጠበቂያ የሚሆን የውኃ እና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት፣ የመኝታ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት የሌለው፣ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ መሆኑ እና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለበት መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማይ፦ «በገላን ከተማ ይህ አንድ የማቆያ ቦታ ነው። በገላን ከተማ ውስጥ ደግሞ ሌሎች የተለያዩ የማቆያ ቦታዎች ክትትል የምናደርግባቸው ቦታዎች አሉ» ብለዋል።
 

ፎቶ ከማኅደር፤ በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማ
ኢሰመኮ በገላን ተመለከትኩት ያለው ማቆያ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ምግብ በቀን ሦስት ጊዜ እና የመጠጥ ውኃ የሚቀርብ መሆኑን፣ በአንጻሩ ይህ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ለሰዎች መጠለያ ወይም ማቆያ ተብሎ የተዘጋጀና የተደራጀ እንዳልሆነ አስታውቋል። ፎቶ ከማኅደር፤ በኦሮሚያ ክልል ወሊሶ ከተማምስል Tamirat Dinsa/DW

ኢሰመኮ ያቀረበው ምክረ ሀሳብ እና የጠየቀው የእርምት ርምጃ


በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም በመዲናዋ የሚደረጉ ዓለም አቀፋና አህጉራዊ ጉባኤዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ በርካታ በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በኃይል ከጎዳና ላይ እንዲነሱ በማድረግ በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ  የሚደረግበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። አያይዞም «ሰዎችን በግዳጅ ወደ አንድ ማቆያ ማዕከል ወይም ቦታ ማስገባት ወይም ለኑሮ ከመረጡት ቦታ ወደማይፈልጉበት አካባቢ እንዲሄዱ ማስገደድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያስከትል በመሆኑ፤ ይህ አስገዳጅ አሠራር በአስቸኳይ እንዲቆም» ሲል ኢሰምኮ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ