1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“አፍሪካ የበለጠ በፍትኃዊነት መወከል አለባት” የአይኤምኤፍ ኃላፊ ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 2 2017

ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የሚኖራቸው ሦስተኛ ተወካይ ጥቅምት 22 ይፋ እንደሚሆን የአበዳሪው ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በተቋሙ ለአፍሪካ አንድ ውክልና ሲጨመር የአይኤምኤፍ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የመቀመጫዎች ቁጥር ወደ 25 ከፍ ይላል።

https://p.dw.com/p/4liZC
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ “አፍሪካ የበለጠ በፍትኃዊነት መወከል አለባት” የሚል አቋም እንዳላቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Hamad I Mohammed/REUTERS

“አፍሪካ የበለጠ በፍትኃዊነት መወከል አለባት” የአይኤምኤፍ ኃላፊ ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ሦስተኛ ተወካይ በመጪው ጥቅምት 22 ቀን 2017 ይታወቃል። ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ ሁለት መቀመጫዎች አሏቸው። ለአፍሪካ አንድ ሲጨመር የአበዳሪውን ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የመቀመጫዎች ቁጥር ወደ 25 ከፍ ያደርገዋል።

ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገውን አበዳሪ ተቋም የለት ተለት ሥራዎች የሚያከናውን ነው።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ አበዳሪ ሀገሮች ያላቸው ድምጽ እጅግ ከፍተኛ ነው። አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ቻይና እና አውሮፓ እንደ ቅደም ተከተላቸው በሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው ናቸው። ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ የሚበደሩ እና በባለጸጎቹ “በማደግ ላይ የሚገኙ” የሚባሉ ሀገራት በአንጻሩ ዝቅተኛ ድምጽ አላቸው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ  በመጪው ጥቅምት 22 ቀን 2017 “ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አንድ ተጨማሪ የቦርድ አባል ወደ አስተዳዳሪው እና የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ ይጨምራል” ሲሉ ተናግረዋል።  

ጂዮርጂየቫ “ይኸን እያደረግን ያለንው አፍሪካ የበለጠ በፍትኃዊነት መወከል አለባት ብለን ስለምናምን ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሁለት መቀመጫዎች አሏቸው። ሀገራቱ በሁለቱ ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን የተለያዩ ተወካዮች አሏቸው። 

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ለኢትዮጵያ የብድር አከፋፈል ሽግሽግ አንዱ ቅድመ-ሁኔታ የነበረው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፕሮግራም ጸድቆ ተግባራዊ መሆን ስለ ጀመረ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ በቅርቡ አንዳች ምላሽ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።ምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 23 የአፍሪካ ሀገሮች የሚገኙ ሲሆን በተያዘው የጎርጎሮሳዊው 2024 ሀገራቱ በኤኮኖሚ ባለሙያው ዊሊ ናኩንያዳ ይወከላሉ። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በዚሁ ምድብ የሚገኙ ናቸው።

ሁለተኛው ምድብ በሬጊስ ኦሊቨር ን'ሶንዴ የሚወከል ሲሆን ጅቡቲ፣ ርዋንዳ እና ሴኔጋልን ጨምሮ 24 የአፍሪካ ሀገሮች የተካተቱበት ነው። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ እንዳሉት አሁን በሁለት ምድብ የተካተቱት የአፍሪካ ሀገሮች ሦስተኛ ወንበር ሲጨመር ሦስት ቦታ ይከፋፈላሉ።

ዋና ዳይሬክተሯ “ውጤቱን የድምጽ አሰጣጡ ከተጠናቀቀ በኋላ እናሳውቃለን” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የብድር ጫና ላጎበጣቸው ሀገሮች ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ዕገዛ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ተበዳሪዎች የዕዳ ጫናቸው ዘላቂ እንደማይሆን ሲረጋገጥ የቡድን 20 ሀገራት የጋራ ማዕቀፍን ጨምሮ የአከፋፈል ማሻሻያ የሚያደርጉት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በሚደረግ ውይይት ነው።

ቻድ፣ ጋና እና ዛምቢያ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። ኢትዮጵያ እንደ ሦስቱ ሀገራት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ ጥያቄ ካቀረበች ረዥም ጊዜ ተቆጥሯል። ለብድር አከፋፈል ሽግሽግ አንዱ ቅድመ-ሁኔታ የነበረው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፕሮግራም ጸድቆ ተግባራዊ መሆን ስለ ጀመረ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ በቅርቡ አንዳች ምላሽ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ተግባራዊ በመሆን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር መንግሥትን ወጥሮ ለያዘው የውጪ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ ቢሰጥም በገበያው ኃይለኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የኬንያ ተቃዋሚዎች
የፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተፈራረመው ሥምምነት መሠረት የታክስ ጭማሪ ለማድረግ ያቀደበት የ2024 የበጀት አዋጅ በኬንያውያን በተለይ በወጣቶች ዘንድ ኃይለኛ ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር ምስል James Wakibia/ZUMA PRESS/picture alliance

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬንያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተፈራረመችው የብድር ሥምምነት ተግባራዊ የምታደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን መንግሥት ለኃይለኛ ተቃውሞ ዳርጎታል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለደሀ ሀገሮች ብድር ሲሰጥ የሚያበጀው መርሐ-ግብር ተበዳሪ ሀገራት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ እንዲከተሉ ግፊት የሚያሳድር ነው። የተቋሙ አካሔድ መሠረተ-ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፋት የሚሹ መንግሥታት እጅ እንዲያጥራቸው ያደርጋል። በኬንያ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መሠረት የሚሰበስበውን ቀረጥ ለመጨመር በተነሳበት ወቅት ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ሀገራት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ እንዲከተሉ ግፊት ሲያደርግ ከዕድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የድህነት ቅነሳ ፍላጎቶቻቸው መጣጣሙን እንዴት ያረጋግጣል? ተብለው የተጠየቁት ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ግን “ለአባል ሀገሮቻችን የፊስካል ሁኔታ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን” የሚል አቋም አላቸው።

“የፊስካል እና የፋይናንስ መረጋጋት የሀገራት ኤኮኖሚ ጥሩ እንዲሆን አስፈላጊ ነገር ነው። ይኸንን ስናደርግ ሁልጊዜም በዛሬውን አንገብጋቢ ፍላጎት እና በመካከለኛ ጊዜ የበጀት ተግዳሮቶች እንዲሁም የፊስካል መረጋጋት መካከል ትክክለኛውን ሚዛን እየፈለግን ነው” በማለት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአባል ሀገራቱን ነባራዊ ሁኔታ በጥንቃቄ እንደሚመለከት አስረድተዋል።

አንድ የአፍሪካ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር “ዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ግትር ፖሊስ አድርገን እንቆጥረው ነበር። አሁን አይኤምኤፍን የምንወስደው እንደ አጋር ነው” ሲሉ በመስማታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ “በጋራ የበለጠ ዘላቂ ለሆነ ልማት መንገድ መፍጠር እንችላለን። ዋንኛ ትኩረታችን መረጋጋት ለዕድገት እና ለልማት የሚያስፈልገውን መረጋጋት መፍጠር ነው” ሲሉ ከዶይቼ ቬለዋ ጆሴፊን ማሐቺ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ