አፄ ኃይለ ሥላሴ ከጀርመን ጋር የመሰረቱት ጥብቅ የወዳጅነት ግንኙነትና ፋይዳው
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016
የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳሚዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን የደርግ አባላት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓም ቤተ መንግሥታቸው ሄደው ከሥልጣን ካነሷቸው ግማሽ ምዕተ ዓመት ተቆጠረ። ደርግ ከሥልጣን ባስወገዳቸው በአስራ አንደኛው ወር በግፍ የተገደሉት አፄ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያን በመሩባቸው ዓመታት ባከናወኗቸው አዎንታዊም አሉታዊም በሚባሉ ስራዎቻቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በኃይል ከሥልጣን አንስቷቸው ያለፍርድም ታስረው ፣ የተገገደሉት አጼ ኃይለሥላሴ ፣ኢትዮጵያን 14 ዓመት በአልጋ ወራሽነት በንጉሠ ነገሥትነት ደግሞ ለ44 ዓመታት አስተዳድረዋል።አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ባለ «ራዕዩ» ንጉሥ
ወራሪውን ፋሺሽት ኢጣልያን በህዝባቸውና በወዳጅ አገራት ትብብር ድል አድርገው ወደ መጣበት ያባረሩት አጼ ኃይለሥላሴ ፣ከጦርነቱ በኋላም ሀገሪቱን በማዘመን ፣ትምሕርትን በማስፋፋት እና ምዕራባውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የውጭ መንግሥታት ጋር በመሰረቱት ጥብቅ የወዳጅነት ግንኙነት ሀገራቸውን ለዓለም በማስተዋወቅ ይወደሳሉ። ዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል ያነጋገራቸው የርሳቸው የቅርብ ዘመድና ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴም በብዛት የተሸጠ መጸሀፍ የጻፉት ልዑል ዶክተር አሥራተ ካሳ ይህን ከሚመሰክሩት ምሁራን አንዱ ናቸው።
ከፍተኛ ትምሕርት ለመከታተል በጎርጎሮሳዊው 1968 በመጡባት በጀርመን በስደት የሚኖሩት የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ ካሳ የአጼ ኃይለ ሥላሴን ከስልጣን መውረድም ሆነ በኋላም መገደል የሰሙት እዚሁ ጀርመን ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን የተነሱት በሀገሪቱ የተለያዩ ማሻሻያዎችን የማድረግ ስራ በተጀመረበትና እርሳቸውን ጨምሮ ህዝቡ ውጤቱን በተስፋ በሚጠባበቅበት ወቅት ነበር።የአፍሪቃ አባት- የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት
አጼ ምኒልክ ለጀመሩት ሥልጣኔን ወደ ኢትዮጵያ የማስገባት ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን ያስረዱት ልዑል ዶክተር አስፋወሰን በዚህም ከአጼ ምኒልክ ጋር ሀገሪቱን ወደ ላቀ ዘመን ለማሻገር የበቁ መሪም እንደነበሩ አስታውሰዋል። ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከጥቂት አገራት በስተቀር አብዛኛውን የዓለም ክፍል ተዘዋውረው በመጎብኘት ሀገራቸውን ያስተዋወቁ መሪ ናቸው። በዘመናቸው ካሳኳቸው የውጭ ሀገራት ግንኙነቶች ውስጥ ከጀርመን ጋር የመሰረቱት ጥብቅ ወዳጅነት አንዱ ነው። ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተ እንደሚሉት ይህ ወዳጅነት የተመሰረተው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ የተጣለባት ማዕቀብ መነሻ ሆኖ ነበር። ከዚያም ዓጼ ኃይለ ሥላሴ ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸንፋ በተቸገረችበት ወቅት ሀገሪቱን የጎበኙ የመጀመሪያው ንጉሠ ነገሥት ናቸው። በዚያ ክፉ ቀን ኃይለ ሥላሴ ከሌላው ዓለም ቀድመው ወደ ጀርመን የሄዱት ባዶ እጃቸውን አልነበረም። የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ፍፃሜ፣ የሪፐብሊኪቱ እጣ
አምባሳደር ተፈራ ሻውል በጎርጎሮሳዊው 1960ዎቹ በምዕራብ ጀርመን የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ኤምባሲ በሁለተኛ ፀሐፊነት የፕሬስ ጉዳይ ሠራተኛ በኋላም የዶቼቬለ የአማርኛውን ክፍል ያቋቋሙ ዲፕሎማትና ጋዜጠኛ ናቸው። የጀርመንና የኢትዮጵያን ግንኙነት ጥልቅና ሰፊ ሲሉ የሚገልጹት አምባሳደር ተፈራ መሠረቱ ከጎርጎሮሳዊው 1888 እስከ 1918 ጀርመንን ከመሩት ከመጨረሻው የጀርመን ንጉስ ፍሪድሪሽ ቪልሄልም 2ተኛ ዘመነ ሥልጣን አንስቶ መሆኑን ያስረዳሉ።ይህም እርሳቸው እንዳሉት በያኔው አጠራሩ የጀርመን ድምጽ ራድዮ የአማርኛ አገልግሎት እዲቋቋም ጭምር ምክንያት ሆኗል። ግርማዊነታቸው በ1954 በመጀመሪያው የምዕራብ ጀርመን መራኄ መንግሥት ግብዣ ጀርመን ከመጡ በኋላ ከጀርመን መንግሥት ጋር ስልጠናና ትምሕርትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ስምምነቶች ተፈጸሙ። በዚህ ስምምነት ጀርመን ለትምሕርት ከመጡት ኢትዮጵያውያን አንዱ አምባሰደር ተፈራ ነበሩ።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ