1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ አበባ የታሰረው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ የቀረበበት ክስና ዲፕሎማሲ

ረቡዕ፣ የካቲት 20 2016

አዲስ አበባ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች የተያዘው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ አሁንም በምርመራ ላይ እንደሚገኝ የሚሠራበት የዜና ተቋም ከፓሪስ ለዶቼ ቬለ አስታወቀ። አፍሪካን ኢንተለጀንስ የተሰኘው ድረ ገጽ ዘጋቢ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንትዋን ጋራንዶ ባለፈው ሳምንት በሥራ ላይ እንዳለ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉ ነው የተገለጸው።

https://p.dw.com/p/4cz7n
Türkei Protest Pressefreiheit
ምስል Getty Images/C. McGrath

የታሰረው ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ

የሥራ ባልደረቦቹ ለዶቼ ቬለ እንተናገሩት ጉዳዩንም የፈረንሳይ መንግሥት ጣልቃ በመግባት እየተከታተለው ነው። በተመሳሳይም ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋለው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ባስቸኳይ በነጻ እንዲለቀቅ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

አንትዋን ጋራንዶ የተባለው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ የተዘገበው ባለፈው ሐሙስ የካቲት 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ነው ። ጋዜጠኛው «ረብሻ ለመቀስቀስ » ሞክረሃል መባሉንም ቀጣሪው ድርጅት ዐስታውቋል። አንቷን ጋሊንዶ በቅርቡ የተካሄደውን የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን አፍሪቃ ኢንተለጀንስ ለተሰኘ ልዩ ኅትመት ለመዘገብ ነበር አዲስ አበባ መገኘቱ የተገለጸው።  መቀመጫውን ፓርስ ፈረንሳይ ያደረገው አፍሪካን ኢንተለጀንስ የተሰኘው ድረ ገጽ ዘጋቢ አንትዋን ጋራንዶ ባለፈው ሐሙስ በደህንነት ኃይሎች መታሰሩን ነው የተለያዩ የመረጃዎች ምንጮች ይፋ ያደረጉት። የሚሠራበት ተቋም አፍሪካን ኢንተለጀንስም በገለጸው መሰረት በያዝነው ወር መጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ያቀናዉ ፈረንሳዊዉ ጋዜጠኛ አንትዋን ጋሊንዶ የአፍሪቃ ሕብረት ዓመታዊ ጉባዔን ለመዘገብ እና በጋዜጠኝነት ለመሥራትም ፈቃድ ጠይቋል።

Logo des Commitee to protect Journalists / CPJ

ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ በደህንነተት መኮንኖች የተያዘዉ በአዲስ አበባ ኢትዮ ስካይላይት ሆቴል ውስጥ የመንግሥት ተቃዋሚ ከሆኑት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ ባቴ ኡርጌሳ ጋር ቃለመጠይቅ ሲያደርግ እንደ ነበር ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረዉ ዓለም አቀፉ ድርጅት CPJ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቃለ ምልልስ ሲደረግላቸው የነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ ባቴ ኡርጌሳም መታሰራቸውንም አክሏል። 
ጋዜጠኛው ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን፣ 2016 ፍርድ ቤት መቅረቡን የገለጸው አፍሪካን ኢንተለጀንስ እስከ ፊታችን አርብ የካቲት 22 ቀን፣ 2016 ዓ/ም ድረስ እስሩ እንደተራዘመ ማረጋገጡን አስታውቋል። ጋዜጠኛው «ያለምክንያት መታሰሩን » እንደሚቃወምም  ገልጻል።  
የአፍሪቃ ኢንተለጀንስ ኅትመት የምሥራቅ አፍሪቃ ክፍልን በኃላፊነት የሚመራው የ36 ዓመቱ ጋዜጠኛ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2013 እስከ 2017 ኢትዮጵያ የኖረ እና «በኢትዮጵያ የመገናኛ አውታር ባለሥልጣናት»ም የሚታወቅ ነው ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አክሎ ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምላሽ አለመስጠታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። 
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት መካከል ጋዘጠኞችን በብዛት በማሰር ሁለተኛዉ ሀገር መሆንዋን የገለፀዉ ዓለም አቀፉ የጋዘጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት፤ ፈረንሳዊዉ ጋዜጠኛ አንትዋን ጋሊንዶ በአፋጣኝ እንዲለቀቅ ሲል ጥሪውን አቅርቧል። እንደ CPJ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ስምንት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም በመንግሥት ኃይላት ታስረው ይገኛሉ። 

ሃይማኖት ጥሩነህ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ