1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዋሽ የነበሩ እሥረኞች አዲስ አበባ ተዛወሩ

ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016

የኢሕአፓን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በአዋሽ አርባ ታሥረው የነበሩ 17 ሰዎች፣ አርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ. ም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሠራቸው ተገለፅ።

https://p.dw.com/p/4gsE4
ፎቶ ማህደር፤ ማረምያ ቤት
ፎቶ ማህደር፤ ማረምያ ቤትምስል Amr Nabil/AP Photo/picture alliance

አዋሽ የነበሩ እሥረኞች አዲስ አበባ ተዛወሩ

አዋሽ የነበሩ እሥረኞች አዲስ አበባ ተዛወሩ 

የኢሕአፓን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በአዋሽ አርባ ታሥረው የነበሩ 17 ሰዎች፣ አርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ. ም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሠራቸው ተገለፅ። ሁለት ጋዜጠኞች ተነጥለው እዚያው በአዋሽ አርባ ይገኛሉ ሲሉ ለዶቼ ቬለ የገለፁ አንድ ፖለቲከኛ፣ የኢዜማ የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከአንድ ሳምንት እሥር በኋላ መለቀቃቸውን አረጋግጠዋል። 
ለአሥር ወራት ቆይቶ የተፈፃሚነት ጊዜው ባለፈው ሳምንት ያበቃውን የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ እስካሁን የቀረበላቸው ምንም ነገር አለመኖሩን የገለፁ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት "አሻሽሉ ተብሎ ለፓርላማ መቅረብ ነበረበት። ዝም ከተባለ ግን ተትቷል ማለት ነው" ብለዋል። 


አቶ የሽዋስ አሰፋ ከእሥር ተለቀቁ 
በአቶ የሽዋስ አሰፋ እና ሌሎች ፖለቲከኞች አስተባባሪነት "የእርስ በርስ ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይስፈን" የሚል ግብ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዳር ላይ ለማድረግ ታቅዶ በመንግሥት ከተከለከለ በኋላ አስተባባሪዎች በተለያየ ጊዜ ታሥረዋል። ከቀም ብሎ ታሥረው ከትለቀቁት የሰለፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፤ አርብ እለት ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩት እሥረኞች "ጨለማ ቤት ውስጥ" መታሰራቸውን ፓርቲያቸው ማረጋገጡን ገልፀዋል።


"እዛ [አዋሽ አርባ] ካመጧቸው በኋላ ቀጥታ የከተቷቸው ጨለማ ቤት ነው። በአሁኑ ሰዓት ከእሥረኛም፣ ከቤተሰቦቻቸውም ነጥለው ቤተሰብ ምግብ ብቻ ነው እያቀረበ ያለው። ይህንን ኢሕአፓ አረጋግጧል" አቶ የሽዋስ አሰፋ በምግብ ብክለት ምክንያት ሆስፒታል ገብተው እንደነበር እንደግለፁላቸው ያስታወቁት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ያልተለቀቁትን ሰዎች በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በማብቃቱ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ወደመመስረት እንደሚያመሩ ገልፀዋል። "ኹከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ተጠርጥረኻል የሚል ነበር። እሱም ያንን እንዳልፈፀመ ተናግሮ ከዚያም በኋላ ወደ ቤቱ ነው ለብርበራ የሄዱት" 
ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራ የሲቪክ ድርጅቶች ጥሪ

Äthiopien | EZEMA Pressekonferenz
ፎቶ ማህደር፤ ኢዜማ ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ በ 2014 ዓ.ምምስል Solomon Muchie/DW


በሌላ በኩል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ የፖለቲከኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች ተጽእኖ ፈጣሪዎች የዘፈቀደ እሥር አሳስቦኛል ሲል ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባለ ሀገር በቀል የመብት ድርጅት ገልጿል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት አሊ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶችን የማፈን አዝማሚያን መስተዋሉን ገልፀዋል። በመሆኑም ሀሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ ብቻ የታሠሩ ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል ድርጅቱ ጥሪ አድርጓል።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉዳይ 
ለብዙዎች መታሰር ምክንያት የሆነው በአማራ ክልል ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈጻሚነቱ ጊዜ የተጠናቀቀ ቢሆንም ስለ አዋጁ ማብቃትም ሆነ መራዘም ከመንግሥት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። በጉዳዩ ላይ ካነጋገርናቸው ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል አንደኛው "አሻሽሉ ተብሎ ለፓርላማ መቅረብ ነበረበት። ዝም ከተባለ ግን ተትቷል ማለት ነው" ብለዋል። አክለውም የአዋጁ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ሪፓርት ለምክር ቤቱ ይቅረብ አይቅረብ የሚለው በምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ የሚወሰን መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን ግን በዚህ መልኩ ሪፓርት ቀርቦ ለውይይት ክፍት የሆነበት ጊዜ እንደሌለ ገልፀዋል። 


ስለ አዋጁ ጊዜ ማብቃትም ሆነ መራዘም ከመንግሥት እስካሁን ምንም ባይባልም ብሔራዊው የመብት ተቋም - የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የአዋጁ የማስፈፀሚያ ጊዜ ማብቃቱን በማስታወስ መንግሥት "በእስር የቆዩ ሰዎችን የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥል" አሳስቧል። ኮሚሽኑ ወደ መደበኛው የሕግ አተገባበር ሂደት መመለስን ጨምሮ በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ እና ሌሎች ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችም እንዲመለሱ ሰሞኑን ጥሪ አቅርቧል። ፓርላማው ይህንኑ ድንጋጌ "ለተጨማሪ ጊዜ እንዳያራዝመው" ባለፈው አርብ የጠየቀው ኢሰመጉ አዋጁ ተፈጻሚነቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም "አሁንም ድረስ በተግባር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ይፈጸሙ የነበሩ" ያላቸው ድርጊቶች "ያለምንም የሕግ መሠረት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ" ሲል አስታውቋል። በዋና ዋና የአማራ ክልል ከተሞች ባደረግነው ማጣራት የኢንተርኔት እና የሰዓት እላፊ ገደቦች አሁንም እንዳልተነሱ ተገንዝበናል።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ