አሸባሪነትና የአፍሪቃ መሪዎች ምክክር፤ | አፍሪቃ | DW | 03.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አሸባሪነትና የአፍሪቃ መሪዎች ምክክር፤

የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራት ጥቂት ርእሳነ ብሔርና የ 15 አገሮች ፤ የሕብረቱ የሰላምና ፀጥታ ም/ቤት ከፍተኛ ተወካዮች በኬንያ መዲና በናይሮቢ ፤ ትንናት የአንድ ቀን ጉባዔ በማካሄድ በክፍለ ዓለሙ፣አሳሳቢ ሆኖ ስለተገኘው አሸባሪነት መክረዋል።

በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ፣ በተለይም ፤ በምዕራብና በምሥራቅ እንዲሁም የአፍሪቃው ቀንድ በመባል በሚታወቀው ክፍል አሸባሪነት ራስ ምታት ሆኗል። የትናንቱ የናይሮቢ ጉባዔ የተካሄደው፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሶማልያ ውስጥ ከኧል ቃኢዳ ጋር ጥምረት እንዳለው

የሚነገረልትን የአሸባብ ስልታዊ ቦታ በአብራሪ የለሽ አይሮፕላን መትታ፣ የአሸባሪው ቡድን ዋና ዋና አባላት ሳይገደሉ እንዳልቀረ ከተነገረ በኋላ ነበር። በአፍሪቃ አሳሳቢ ስለሆነው የአሸባሪ ኃይሎች እንቅሥቃሴና አስፈላጊንቱ ጎልቶ ስለሚነገርለት የመንግሥታት ትብብር የተከታዩ ዘገባ ትኩረት ነው።

በናይሮቢው ያንድ ቀን ጉባዔ ፤ ከአስተናጋጅ ሀገር ፣ ኬንያ፣ ፕሬዚዳንት ዑሁሩ ኬንያታ ሌላ፣ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ የሶማልያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እንዲሁም የወቅቱ የአፍሪቃ የሰላምና ፀጥታ ም/ቤት ሊቀመንበር የቻዱ ርእሰ ብሔር ኢድሪስ ደቢ ተገኝተዋል። በጉባዔው መክፈቻ ኢድሪስ ደቢ ባሰሙት ንግግር ላይ ፤ «የአፍሪቃው ክፍለ ዓለም ሰላምና መረጋጋት የሚያሳስበን ጉዳይ ነው። በሳሔል አካባቢ፤ ቦኮ ሐራም በተለይ በናይጀሪያና በአንዳንድ የምዕራብ አፍሪቃ ክፍሎች የሠነዘራቸው ጥቃቶች፤ ይህን ሰው ሠራሽ መቅሰፍት ይበልጥ ተጠናክረን እንድንታገል የሚያነሳሳን ይሆናል ማለታቸው ነው የተጠቀሰው።

አሸባሪነትን ተጠናክሮ ለመታገል ምንድን ናቸው የሚያስፈልጉት ዐበይት ጉዳዮች?በአፍሪቃ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ም/ቤት የተጠቀሰው ጉዳይ ተመራማሪ ባለሙያ ጆን ባፕቲስቴ ምዋንጄ እንዲህ ይላሉ።

«አሸባሪነትን ለመታገል በሰፊው የመረጃ ልውውጥን ይጠይቃል። ይህ ነው ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ! ቀጥሎም፤ አካባቢዎች የተባበረ ርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ሁለቱን መሠረታዊ ጉዳዮች አጣምረን እርምጃ ከወሰድን በትክክለኛው ሽብር ላይ ዘመትን ማለት ነው። እናም ማሸነፍ እንችላለን።»

ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ፤ ባለፈው መስከረም ናይሮቢ ውስጥ የአሸባብ ታጣቂዎች በአንድ የገበያ አዳራሽ 67 ሰዎችን መግደላቸውን በማስታወስ ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዑሑሩ ኬንያታ ፣ »ማንም መንግሥት ብቻውን ይህን አሥጊ ሁኔታ ሊያስወግድ አይችልም። አፍሪቃ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚያስጨንቀው፤ የአሸባሪ ድርጅቶች ተዋጊዎች ቁጥር መጨመርና አደጋ የመጣል ችሎታቸውንም ሚeበልጥ ማጠናከራቸው ነው» ብለዋል።

በዛ ያሉ የአፍሪቃ አገሮች ፤ ኬንያና ናይጀሪያ ጭምር እስላማዊ አክራሪና አሸባሪ ኃይሎችን በመውጋት ረገድ የምዕራባውያን መንግሥታት ተባባሪዎች ናቸው። የጸጥታ ኃይሎቻቸውም ተጨማሪ ሥልጠና ምግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ከብሪታንና ከሌሎችም እርዳታ ለጋሽ መንግሥታት ድጎማ ያገኛሉ። አንዳንድ የአውሮፓ ሃገራት ተወካዮችም በናይሮቢው ጉባዔ የተገኙ ሲሆን፤ ይህም የአፍሪቃው ክፍለ ዓለም አሸባሪነትን ለማስወገድ በሚያደርገው ትግል የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ እንደማይለየው የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው የተመለከተው። በናይሮቢው ጉባዔ ከተገኙት መካከል አንዱ በኬንያ የፈረንሳይ ምክትል አምባሳደር ኢማኑኤል ሬኖ ናቸው።

«እንደሚመስለኝ የኛ በዚህ ጉባዔ መገኘት የሚያሳየው፤ ጉዳዩ በጥልቅ እንደሚመለከተን ፤ የአካባቢው አገሮች የሚያደርጉትን ጥረት በተለይ የኬንያና የሶማሊያ መንግሥታት ፤ አሸባሪነትን ለመታገል የሚያደርጉትን ጥረት እንደምንደግፍ ለማረጋገጥ ነው። ለዚህም ነው ለ AMISOM ሥምሪት በያመቱ የ 100 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ የምንሰጠው።»

ለምዕራባውያኑ ድጋፍ አንዱ ምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሌው አሸባብ ላይ አልፎ አልፎ በአብራሪ -የለሽ አይሮፕላን የምትሰነዝረው ጥቃት ነው። በትናንትናው ዕለትም የናይሮቢው ጉባዔ ከመከፈቱ ጥቂት ቀደም የአሸባብን የጦር መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔን ለመግደል ያነጣጠረ ርምጃ መውሰዷ ተነግሯል።ይሁንና ጎዳኔ ይሙቱ ፤ ይቁሰሉ ወይም ከተቃጣው አደጋ ያምልጡ የታወቀ ነገር የለም።

ጎዳኔ ቢገደሉም እንኳ፤ በበርሊን የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም ባልደረባ የሆኑት የአፍሪቃ ጉዳዮች ተከታታይ ባለሙያ አኔተ ቬበር እንደሚሉት አሸባብን እንዲጠፋ የሚያደርግ ርምጃ ሆኖ ሊታይ አይችልም።

አሸባብ ተለዋዋጭ ነው። አሸባብ በደቡብ ሶማልያ ከመቶ ምናልባትም ከሺ የሚበልጡ ተዋጊዎች እንዳሉት ነው የሚታሰበው።ወታደራዊ ስልታቸውን በመለወጥ፣ በመቅዲሹ ፤ ከከተማ ሽምቅ ውጊያ

ወደ ገጠር በመግባት ሰፊ ግዛት መቆጣጠርና የደፈጣ ውጊያ ማካሄድ ይህ ሁሉ የቻሉበት ጉዳይ ነው።»

የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኝና የሶማልያን ይዞታ ጠንቅቀው የሚያውቁት አሁን በናይሮቢ የሚገኙት ባለሙያ ራሺድ አብዲ ፤ አሸባብ በደፈጣ ውጊያ ወይም ቦታዎችን በመቆጣጠር ብቻ የሚመካ ድርጅት አይደለም ይላሉ።

«ቦታ መቆጣጠር ብቻ በቂ አይደለም። አሸባብ፤ በሰፊውና በጥልቀት ከሶማልያ ማሽበረሰብ ጋር የተቆራኘ ድርጅት ነው። በዚህ ድርጅት ላይ ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘሩ፤ ምናልባት የድርጅቱን የማጥቃት አቅም ሊያዳክም ይችላል፤ ነገር ግን ፤ በሚደርስበት ከባድ ወታደራዊ ጥቃትና መፈናፈኛ ማጣት ይበልጥ ተጠናክሮ የሚገኝበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic