አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል እየተፈፀመ ያለው የዘፈቀደ እሥር እንዲቆም ጠየቀ
ረቡዕ፣ መስከረም 22 2017ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፦ በአማራ ክልል ሰሞኑን እየተፈፀመ ነው ያለው «የዘፈቀደ የጅምላ እሥር» በአስቸካይ እንዲቆም ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠየቀ ። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትቱ ከመስከረም 18 ቀን፣ ጀምሮ በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች የፀጥታ ኃይሎች በዘመቻ መልክ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያሠሩ ስለመሆኑ ገልጿል ። ታሳሪዎች ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ ቤተሰብም ሊያነጋግር እንደማይችል ከክልሉ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ።
ዓለም አቀፉ የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት አመነስቲ ኢንተርናሽናል ካለፈው ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን፣ ጀምሮ በአማራ ክልል የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ በዋና ዋና የክልሉ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጅምላ የዘፈቀደ እሥር እየተፈፀመባቸው መሆኑን፣ መንግሥትም ይህንን ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል።
ድርጅቱ የዐይን እማኞች ነገሩኝ ሲል ባሰፈረው የመግለጫው ዝርዝር የክልሉ ባለሥልጣናት የሚታሠሩ ሰዎችን ስም ዝርዝር እንደሚያቀርቡ እና ለዚህ ድርጊት የፍርድ ቤት የእሥር ትዕዛዝም ሆነ የመያዣ ፈቃድ የማያቀረቡ መሆኑን አትቷል። አመነስቲ ኢንተርናሽናል ይህንን ድርጊት የፖሊስ አባላት እና የመከላከያ ሠራዊት መፈፀማቸውን ደምድሞ ጠቅሷል።
በተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ አከባቢ ዋና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ በክልሉ "የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አባላት በአማራ ክልል እያካሄዱት ያለው የዘፈቀደ የጅምላ እሥራት መንግሥት ለሕግ የበላይነት ደንታ ቢስ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው"። በሚል ስለመግለፃቸው ተጠቅሷል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ አስተያየት ሰጪ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ያለው የእሥር ሁኔታ ሰዎችን ወደተዘጋጁ ማሠሪያ ሥፍራዎች እንዲወሰዱ የሚያስገድድ መሆኑን፣ ቤተሰብ የታሠሩትን መጠየቅ እንደማይችል እና ታሳሪዎች ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ የተስተዋለበት ነው ብለዋል።
የአመነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ አከባቢ የሥራ ኃላፉው አክለው እንዳሉት "የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የዘፈቀደ እሥራቶችን በአፋጣኝ ማቆም አለባቸው"። የታሠሩት ሰዎች ሕግን በተከተለ ሁኔታ አለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ወንጀሎች ክስ ሊመሰረትባቸው ወይንም ያለምንም መዘግየት ሊፈቱ እንደሚገባ ተናግረዋል። ባለሥልጣናቱ የዘፈቀደ እሥርን እንደ መጨቆኛ መሣሪያ መጠቀምን የሚያቆሙበት ጊዜ አሁን መሆኑን ገልፀዋል።
በጉዳዩ ላይ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራሪያ ለመጠየቅ ብንሞክርም የእጅ ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም። የአማራ ክልል መንግሥት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ትናንት በሰጡት እና በሕዝብ መገናኛ ብዙኃኖች በተላለፈ የጋራ መግለጫቸው ግን በክልሉ እየተወሰደ ያለው ሰሞነኛ እርምጃ ሕግ የማስከበር ተግባር መሆኑን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል። የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፉ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጽንፈኛ ያሉትን ኃይል "በመረጠው ቋንቋ" በኃይል ማነጋገር ተገቢ ነው ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው "ስምሪት በሚሰጡ መሪዎች ላይ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት ታምኖበታል፣ እርምጃውም ተጠናክሮ ይቀጥላል"፣ በክልሉ በተለያየ መንገድ በመንግሥት መዋቅር፣ በንግድ የተሰማሩ የመረጃ እና የሀብት ምንጮች እንዲሁም የእገታ አስተባባሪ የሆኑ የተባሉ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል" ሲሉም የቀጣይ ሂደቶችን መልክ ምን መሳይነት አመልክተዋል። አንድ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ እንደሚለው እዚያ መኖር ከባድ አደጋ እንደተጋረጠበት በምሬት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያደረገውን የምርመራ ውጤት ባለፈው ሳምንት ይፋ ሲያደርግ እንዳለው የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እሥራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር እና እገታ በአሳሳቢነት መቀጠላቸውን፤ "አስገድዶ መሰወርንና ሰዎች ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየትን" በሚመለከት ራሱን የቻለ ዝርዝር መግለጫ ወደፊት ይፋ የሚያደርግ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
በአማራ ክልል ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ ችግር መፈጠሩ ተገልፆ የፌዴራሉም መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ፣ ተጥሎ የከረመውና ተደጋግሞ ተራዝሞ የነበረው የአስቸኳይ ጌዜ አዋጅም ቢነሳም የፀጥታ ችግሩ ለ አንድ ዓመት ከአራት ወራት በትጥቅ ግጭት ጭምር ታግዞ አሁንም ሁነኛ፣ ብሎም ዘላቂ ሰላም ሊገኝለት ሳይችል ቀጥሏል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ