1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማርኛ፤ ትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት በጀርመን

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2016

በአማርኛ፤ በትግርኛ፤ በኦሮምኛ እንዲሁም በስዋሂሊ ቋንቋ ወደ ጀርመን፤ ወደ ኔዘርላንድ ቋንቋ ደች ብሎም ወደ እንጊሊዘኛ ተተርጉሞ በስዕል ታጀቦ እና ግልጽ እና በቀላሉ ቋንቋን ለማስተማር የቀረቡት መጻህፍቶች፤ ተጠቃሚዎቹ ህጻናት ብቻ ሳይሆኑ፤ ጀርመንኛ እና ኢንጊሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አዋቂዎችም ቋንቋዉን ለመማር እንደሚጠቀሙበት ተነግራል።

https://p.dw.com/p/4cPmt
አማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት በጀርመን
አማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት በጀርመንምስል Habte Verlag

ፍፃሜ ተፈራ የአማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅ በጀርመን

የአፍሪቃ ቋንቋዎችን በማስተማር ዓለምአቀፍ አፍሪቃውያን ህጻናት እራሳቸዉን እንዲያገኙ ማስቻል በሚል መሪ ቃል በጀርመን ለሁለተኛ ትዉልድ አፍሪቃዉያን ህጻናት የሚሆን መጻሕፍ መታተም ከጀመረ ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በጀርመን መዲና በርሊን ነዋሪ የሆነችዉ ኢትዮጵያዊት ፍፃሜ ተፈራ አማርኛን ትግርኛን፤ ኦሮምኛን እንዲሁም በቅርቡ ስዋሂሊ ቋንቋዎችን መማር ለሚፈልጉ ህፃናት ከስዕል ጋር አወዳጅታ በማሳተም ላይ ባለችዉ መጽሐፍ ታዋቂነትን እያተረፈች ይገኛለች።

በአማርኛ፤ በትግርኛ፤ በኦሮምኛ እንዲሁም በስዋሂሊ ቋንቋ ወደ ጀርመን፤ ወደ ኔዘርላንድ ቋንቋ ደች ብሎም ወደ እንጊሊዘኛ ተተርጉሞ በስዕል ታጀቦ እና ግልጽ እና በቀላሉ ቋንቋን ለማስተማር የቀረቡት መጻህፍቶች፤ ተጠቃሚዎቹ ህጻናት ብቻ ሳይሆኑ፤ ጀርመንኛ እና ኢንጊሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አዋቂዎችም ቋንቋዉን ለመማር እንደሚጠቀሙበት ተነግራል። በሌላ በኩል አማርኛ ትግርኛ ኦሮምኛ ወይም ስዋሂሊ ቋንቋን የሚናገሩ ሰዎች፤ ጀርመንኛን እና እንጊሊዘኛን አልያም ደች ቋንቋን ለመማር ይጠቀሙበታል ተብሏል።

ከባለቤትዋ ጋር ወደ ጀርመን ከመጣች 10 ዓመት ገደማ እንደሆናት የምትናገረዉ ወጣትዋ ደራሲ ብሎም የህጻናት መብት ጉዳይ ምሁር ፍጻሜ ተፈራ፤ ሕጻናት በማኅበራዊ ኑሮ ዉስጥ ያላቸዉን መብት እና አያያዝ በተመለከተ በጀርመንዋ ፖስትዳም ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ የማስትሪት ዲግሪዋን አጠናቃለች። በምዕራቡ ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሕጻናት የቋንቋ መማርያ መጽሐፍትን ከማሳተም ሌላ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አፍሪቃ ሃገራት ላይ የህጻናትን መብት  ጉዳይ በተመለከተ እዚህ ጀርመን ዉስጥ በሚገኝ በአንድ ድርጅት ዉስጥ ተቀጥራም በማገልገል ላይ ትገኛለች። ለህጻናት ቋንቋ መማርያ እንዲያገለግል የምታቀርበዉን መጽሐፍ ለማሳተም የዛሬ ስድስት ዓመት ሃብቴ አሳታሚ ድርጅትን መስርቷንም ወጣትዋ ፍጻሜ ተፈራ ነግራናለች።

ፍፃሜ ተፈራ፤  የአማርኛ ትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅ በጀርመን
ፍፃሜ ተፈራ፤ የአማርኛ ትግርኛና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅ በጀርመን ምስል Habte Verlag

በምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ በብዛት በሚነገረዉ በስዋሂሊ እና ጀርመንኛ ብሎም በእንጊሊዘኛ የተተረጎመ መጽሐፍን ለተጠቃሚ ማቅረብ መጀመርዋን ፍፃሜ ተፈራ ተናግራለች።  ፍጻሜ ተፈራ፤  ለህጻናት የሚቀርቡ የታሪክ መጽሐፍቶች፤ ባለንበት ዘመን በፍጥነት በኢንተርኔት እና በማህበራዊ ሚዲያ እየተተኩ በመሆናቸዉ እነዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች የቀረቡት  መጽሐፎቿ ክፍተቱን ለመሙላት ይረዳሉ ስትል እንደምታምን ተናግራለች።

ለአማርኛ ትግርኛ ኦሮምኛ ጀማሪ ቋንቋ ተማሪዎች የሚሆነዉ እና በስዕል ከተደገፈዉ መማርያ መጽሐፍ በተጨማሪ ህጻናት በሚገጣጠም ስዕሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን፤ ለምሳሌ እንደ አክሱም ሃዉልት አይነት ቅርፆችን በመገጣጠም ታሪክን ለመማር የሚረዳ የመማርያ መሳርያዎችን፤ ብሎም ሌሎች ለሕጻናት መጫወቻ ግን ቋንቋና ቁጥርን ለመማር የሚረዳ መሳርያን ማዘጋጀትዋንም ወጣትዋ ፍጻሜ ተፈራ ገልፃለች።  

ፍፃሜ ተፈራ የአማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅ በጀርመን
ፍፃሜ ተፈራ የአማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅ በጀርመን ምስል Habte Verlag

መጽሐፉ በቋንቋ የሚደረግ የባህል ልውውጥ ዘርፍ መሆኑን የገለፀችዉ ፍጻሜ ተፈራ፤ መጻሕፍት እንደ የሰውነት ክፍሎች፣ እፅዋት እና እንስሳት ያሉ መሰረታዊ እውቀቶችን የያዙ እና አዲስ ቋንቋን በቀላሉ ለመማር  ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝም ታምናለች።

ፍፃሜ ወደ ጀርመን ከመምጣቷ በፊት ወደ 30 የህጻናት መማርያ መጽሐፍቶችን አሳትማለች። የህጻናትን ጉዳይ የሚከታተለዉ «ሴቭ ዘ ችልድረን» ከተባለዉ ድርጅት ጋር  ጨምሮ ከበርካታ የህፃናት ጉዳዮችን በሚሰሩ ተቋም  እና የስራ ፕሮጀክቶች ላይም ሰርታለች። በጀርመን የማስተርስ ዲግሪዋንም ያጠናቀቀችዉ በህጻናት መብት ላይ ጥናት በማድረግ ነዉ።

 አማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት በጀርመን
አማርኛ፤ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት በጀርመንምስል Habte Verlag

ፍፃሜ ተፈራ፤ በፍራንክፈርት ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ሕጻናትን አማርኛ ቋንቋን በማስተማር ልምድንም አካብታለች። ሕጻናቱን ቋንቋ ስታስተምር ከህፃናቱ ያገኘቻቸዉ ሃሳቦች ለስራዋ ብዙ ግብዓት እንደሆንዋትም ተናግራለች።

የልጆች እና የህጻናት መብት ጉዳዮች ላይ በበርሊን ፖትስ ዳም ዩንቨርስቲ ትምህርቷን ያጠናቀቀጥዉ ፍፃሜ ተፈራ፤ የልጆች እድገትን እና የልጆች መብቶችን በተመለከተ ለቋንቋ ተማሪዎች በምታቀርባቸዉ መጻሕፍቶችዋ ላይ ለማንፀባረቅ ፍላጎት አላት። በዚህም በመጻሕፍቶችዋ ከልጆች ተሳትፎ፤ ከልጆች አንደበት የምታገኛቸዉን ነገሮች ለሌሎች ማስተላለፍ ነዉ።  

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ