1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አልትራቪዮሌት ከፍተኛ የፀሐይ ጨረር በአዲስ አበባ ተከስቷልን?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2016

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሙቀት መጠን መጨመርን ተከትሎ ለአልትራቪዮሌት (ቆዳን ለሚጎዳ ከፍተኛ የፀሐይ ጨረር) መጋለጥ ሳይኖር አይቀርም የሚል መረጃ የማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎችን በእጅጉ አጨናንቆት ተስተውሏል ።

https://p.dw.com/p/4duMU
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ
የአዲስ አበባ ከተማ ከፊል ገጽታ ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

አደገኛ የፀሐይ ጨረር (አልትራቪዮሌት) አዲስ አበባ ተከስቷል?

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሙቀት መጠን መጨመርን ተከትሎ ለአልትራቪዮሌት (ቆዳን ለሚጎዳ ከፍተኛ የፀሐይ ጨረር) መጋለጥ ሳይኖር አይቀርም የሚል መረጃ የማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎችን በእጅጉ አጨናንቆት ተስተውሏል ። የዓለም ጤና ድርጅት ነው በሚል በተሰራጨው በዚህ መረጃ መሰረት ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የሚስተዋለው የሙቀት መጠን በተለይም ከረፋድ 5፡00 እስከ ከሰዓት 10፡00 ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው ። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ተቋም ግን ከወትሮው ወቅታዊ የአየር ጠባይ ሌላ የተፈጠረም ሆነ የሚፈጠር የተለየ ነገር አይኖርም ብሏል ። የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ተጨማሪ አለው ።

አልትራቪዮሌት የመከሰት እድል

አልትራቪዮሌት የተሰኘው በዓለም ሙቀት መጨመርና በላይኛው ከባቢ አየር ማለትም በኦዞን መሳሳት ይከሰታል የሚባለው ከፍተኛ የፀሐይ ጨረር  ከሰሞኑ በመዲናዋ አዲስ አበባ የመስተዋሉ መረጃ ከዳር እስከ ዳር ተስተጋብቷል ። ይሁንና ስለዚሁ ስጋት በዶቼ ቬለ የተጠየቁት በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው፦ ከተለመደው ወቅታዊው የአየር ጠባይ ውጪ የተፈጠረ ነገር የለም ባይ ናቸው፡፡

«ከጎርጎሳውያኑ መጋቢት 20 በኋላ ምን ጊዜም ጸሃይ ከደቡብ ወደ ሰሜን ንፍቀ ክብብ አቅጣጫዋን ትቀይራለች፡፡ ከዚህ የወቅት መቀያየር ውጪ የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ በመሳሪያዎቻችንም የተለየ የተመዘገበ ነገር አላየንም” ብለዋል፡፡ አልትራቪዮሌት  በብርቱ የፀሐይ ጨረር የሚከሰት በኦዞን መሳሳት የሚመጣ ነው የሚሉት ባለሞያው ከአከባቢው የአየር ጠባይ ጋር ወይም በአከባቢ አየር ውስጥ ኬሚካሎች ስከማቹ ሊከሰት እንደሚችል አንስተዋል፡፡

የፀሐይ መጠን መጨመር እና አልትራቪዮሌት የተለያዩ ናቸው ሲሉም አብራርተዋል ። በተለምዶ በበልግ ወቅት የሙቀት መጠኑ እንደሚጨምርም ገልጸው ይህን ከአልትራቪዮሌት ጋር የሚያገናኘው የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የፀሐይ ሙቀት መጨመር አነጋጋሪ ሆኗል
ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የፀሐይ ሙቀት መጨመር አነጋጋሪ ሆኗልምስል Seyoum Getu/DW

የአልትራቪዮሌት የጤና ጉዳት

ይሁንና አደገኛ የሆነው  የፀሐይ ጨረር (አልትራቪዮሌት)በሰው እና በእንስሳት ላይ ተፅዕኖ ሊያደርስ የሚችል ነው መሆኑን የሚገልጹት የቆዳ ህክምና ባለሙያዋ ዶ/ር ፍሬሰና እውነቱ ችግሩ የሚከሰት ከሆነ በመጀመሪያ ቆዳን በመጉዳት በሽታን የመከላከል አቅም ያሳንሳል፡፡ "የቆዳ ሴሎች እራሳቸውን እንዳይከላከሉ ያደርጋል፡፡ ሴሎች በራሳቸው እራሳቸውን የመጠገን አቅም ያሳጣል” ብለዋል፡፡ ይሁንና የችግሩ መፈጠርን በተመለከተ የበለጠ ጥናት ያሻዋል ነው ያሉት፡፡ ቆዳችን ላይ ጨረሩ ጥቃት ሲያደርስ ግን ቆዳችን ወደ ካንሰር ሴል በመለወጥ ለበሽታ ሊዳረግ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ እንደሚሉት ግን ከአየር ንብረት ጋር በተያየዘ የሚጠበቁ ለውጦች ሲኖሩ መስሪያ ቤታቸው ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ