1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ የኢንዱስትሪዎች ሥራ እንቅስቃሴ መስተጓጎልና ሥራ አጥነት

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2016

በትግራይ ክልል የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ተከትሎ ሥራ አጥነት መበራከቱ ተገለፀ። በክልሉ ከጦርነቱ በፊት ሥራ ላይ ከነበሩ ከስድስት ሺህ በላይ አምራች ተቋማት አብዛኞቹ አሁንም ወደ ሥራ አልተመለሱም።

https://p.dw.com/p/4hK32
ትግራይ ኢንዱስትሪ
በትግራይ ክልል በጦርነት ከተጎዱ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ምስል Million H. Silasse/DW

በትግራይ የኢንዱስትሪዎች ሥራ እንቅስቃሴ መስተጓጎልና ሥራ አጥነት

በትግራይ ክልል የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ተከትሎ ሥራ አጥነት መበራከቱ ተገለፀ። በክልሉ ከጦርነቱ በፊት ሥራ ላይ ከነበሩ ከስድስት ሺህ በላይ አምራች ተቋማት አብዛኞቹ አሁንም ወደ ሥራ አልተመለሱም። ውድመት፣ የመንቀሳቀሻ ሀብት እና ግብአት እጦት እንዲሁም ተደራራቢ ዕዳ እና የብድር ወለድ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ፈተና እንደሆኑ ነው የተነገረው።

የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ከጦርነቱ በፊት 6,400 አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ አምራች የኢንዱስትሪ ተቋማት የነበሩ ሲሆን፥ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረ ውድመት፣ ዝርፍያ እና ሌላ ዓይነት ጉዳት አብዛኞቹ ከሥራ ውጭ እንደሆኑ እና እስካሁንም ወደ ሥራ የተመለሱት 227 ተቋማት ብቻ መሆናቸው ተገልጿል። ይህ በትግራይ ክልል በሚልዮን የሚቆጠር የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረ የማምረቻ ዘርፍ በደረሰበት ጉዳት ወደ ሥራ ባለመመለሱ ሥራ አጥነት ተበራክቷል፣ ምርት ቀንሷል፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል።

ትግራይ ክልል
ትግራይ ክልል ምስል Million H. Silasse/DW

በትግራይ የሚገኙ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች /ኢንቨስተሮች/ እና የተቋማት አንቀሳቃሾች ከጦርነቱ በኋላ ወደ ሥራ እንዳይመለሱ በርካታ ፈተናዎች እየገጠምዋቸው መሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፥ ባንኮች ከጦርነቱ በፊት የወሰዱትን ብድር ከጦርነት ግዜው ወለዱ ጋር ጨምረው እንዲመልሱ መጠየቃቸው፣ የሥራ ማስኬጃ ማጣታቸው፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈተናቸው እና የጥሬ ግብአት አቅርቦት ውስንነት እንደገጠማቸው በአንቀሳቃሾች ይገልፃል። ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅት የወደሙ ተቋማት ካሣ ከመንግሥት እንደሚጠብቁት ይገለፃል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በትግራይ የተቀዛቀዘው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ሰሞኑን በመቐለ ውይይት እና የሥራ ጉብኝት አድርጓል። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ በትግራይ የተቀዛቀዘው እንቅስቃሴ ለመመለስ በፌደራሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ