1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎችን ግጭት ውስጥ ያስገባ ውዝግብ

ቅዳሜ፣ የካቲት 9 2016

አማራና ትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣና ወፍላ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ወረራ ፈፀሙብን ሲሉ የየአካባቢዎቹ አስተዳደርና ነዋሪዎች ተናገሩ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ወረራ የፈፀሙት የአማራ ሚሊሺያዎች ናቸው ሲል መልስ ሰጥቷል። “ውዝግቦቹም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት» ነው የሚፈቱት ብሏል።

https://p.dw.com/p/4cWgN
Äthiopien Southern Tigray, Alamata
ምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት

አማራና ትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣና ወፍላ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ፈፀሙብን ሲሉ የየአካባቢዎቹ አስተዳደርና ነዋሪዎች ተናገሩ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ጥቃት የፈፀሙት የአማራ ሚሊሺያዎች ናቸው ሲል መልስ ሰጥቷል፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አክሎም “ውዝግቦቹም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንጂ በጦርነት አይፈቱም” ብሏል፡፡

ቀደም ሲል በትግራይ ክልል አስተዳደር በነበሩና አሁን የአማራ ክልል በሚያስተዳድራቸው ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎች ሰሞኑን የታጠቁ የትግራይ ኃይሎች በአንዳንዶቹ ቀበሌዎች ጥቃት እንደፈፀመና በነዋሪዎች ላይ ወከባና እንግልት አድርሰዋል ሲሉ የአላማጣና ኮረም አካባቢ ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡

የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ባለፈው ረቡዕ አሁን የአማራ ክልል መንግስት ከሚያስተዳድራቸው ቀበሌዎች መካከል በራያ ባላ “ማሩ”በሚባል ቀበሌ የትግራይ ተዋጊዎች ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈፅመዋል ብለዋል፣ አሁንም በአካባቢው ስጋት እንዳለ አመልክተዋል፡፡

Karte Äthiopien Region Tigray DE

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ እንደገለጡት ታጣቂ ኃይሉ በራያ አላማጣ ወደሚኖሩበት “ተክላይ በር” ቀበሌ በመግባት ህብረተሰቡን አዋክበዋል፣ አንገላትተዋል ብለዋል፣ የመከላከያ ሰራዊት ከገባ በኋላ ለጊዜው ግጭቱ መቆሙን አስረድተዋል፣ ሆኖም አሁንም የአቀበሌው ነዋሪዎች “እንወረራለን” የሚል ስጋት አድሮባቸዋል ነው ያሉት፡፡

አሸንጌ በተባለው የወረዳው አካባቢ ሰሞኑን ከትግራ ኃይሎች “ትንኮሳ” ደርሶብናል የሚሉት አንድ ኮረም ከተማ አካባቢ ያሉ የወፍላ ወረዳ ነዋሪ አሁንም ውጥረቱ እንዳለ ነው ብለዋል፣ ዛሬም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፅእንደሚሰማ ነው ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ጉዳይ

“ለጥቃት ተንቀሳቅሷል” ያሉት ታጣቂ ኃይል የተሟላ ትጥቅ ያለውና ከሚሊሺያ አደረጃጀት የላቀ እንደሆነ የገለጡልን ደግሞ ሌላ የአላማጣ ነዋሪ ናቸው፡፡

“ለውጊያ የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ ይዘው ነው የመጡት፣ ከሚሊሺ ከፍ ያለ፣ ዲሽቃ አለ፣ ስናይፐር አለ፣ የቡድንና የግል መሳሪያ አለ፣ በሰው ኃይል በደንብ የጠነከረ በትግራይ የሽግግር መንግስት የሚመራ ተዋጊ ኃይል ነው የመጣው” ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሀለፎም ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ምላሽ  ጥቃት የፈፀመው የአማራ ታጣቂ ሚሊሺያ ነው ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ረዳኢ የአማራ ኃይሎች በትግራይ መሬት ላይ ሆነው ሌላ ጥቃት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ ነው በሚልም ይከስሳሉ፡፡

Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

“ወረራ ፈፅመውብናል የሚል ተረት ቢያቆሙት ነው የሚሻለው፣ ጥቅም የለውም፣ እነርሱ ወርረው ከያዙት አካባቢ ቢወጡ ነው ለሰላም ጥቅም የሚሆነው፣ የተጠቃቀሱት ቦታዎች በሙሉ የትግራይ ራያ አካባቢዎች ናቸው እንጂ የአማራ አካባቢዎች አይደሉም፣ ሁለተኛው ባለፉት ቀናት የተፈፀሙት የተባለው በራያ ጨርጨር አካባቢ ነው፣ በራያ ጨርጨር ካሉ ቀበሌዎች አራቱ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነው ያሉት፣ አሁን ጥቃቱ የተፈፀመው የአማራ ኃይሎች መጥተው በእኛ ሚሊሺያዎች ላይ ነው ተኩስ የከፈቱት፣ ወርረው በያዙት መሬት እንኳ ቢሆን ወደዚያ የእኛ ኃይሎች ወይም ሚሊሺያዎች ተንቀሳቅሰው ቢሆን አንድ ነር ይባል ነበር፣ ያ ሳይሆን እነሱ በወረራ ባልያዙት አካባቢ መጥተው ነው ጥቃት የፈፀሙት፣ በራያ ጨርጨር ላይ፤ እነርሱ ጥቃት ፈፅመው መልሰው እነርሱ ጯሂ ሆነው እየሰማኋቸው ነው፣ ሰሞኑንም እንደዚያ እየታዘብናቸው ነው፡፡ ጥፋት የፈፀሙ፣ ጉዳት የፈፀሙ እነርሱ ናቸው፣ ሲጀመር ደግሞ ጥፋት እየፈፀሙ ያሉ በእኛ በትግራይ መሬት ላይ ተቀምጠው እያሉ መልሰው መጮሁ ጥቅም ያለው ኤመስለኝም ” ሲሉ ነው አቶ ረዳኢ የገለፁት፡፡የትግራይ ክልል ሮሮ ስለ ፕሪቶርያው ውል አተገባበር

ችግሮቹ የሚፈቱት  በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንጂ በጦርነት አይደለም ያሉት አቶ ረዳኢ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም ውዝግቦች በጦርነት ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ