1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ፤ ፆታዊ ጥቃቶች ላይ ተገቢ ምላሽ እየተሰጠ አይደለም ተባለ

ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2016

በትግራይ እየተፈፀሙ ላሉ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የአስተዳደሩ የፀጥታ እና ፍትህ ተቋማት ተገቢው ምላሽ እየሰጡ አይደለም በማለት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት ተቹ። እነዚህ በተለይም በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት በጋራ በሰጡት መግለጫ በትግራይ አሳሳቢ የሆነው ፆታ መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4i0y2
ከሃያ አምስት በላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በሴት ላይ በደል ይቁም ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጡ
ከሃያ አምስት በላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በሴት ላይ በደል ይቁም ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጡ ምስል Million Hailesilassie/DW

በትግራይ በሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች ላይ ተገቢ ምላሽ እየተሰጠ አይደለም ተባለ

በትግራይ እየተፈፀሙ ላሉ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የአስተዳደሩ የፀጥታ እና ፍትህ ተቋማት ተገቢው ምላሽ እየሰጡ አይደለም በማለት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት ተቹ። እነዚህ በተለይም በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት በጋራ በሰጡት መግለጫ በትግራይ አሳሳቢ የሆነው ፆታ መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የመቐለ ከተማ ፖሊስ ፅሕፈት ቤት ያወጣው ያለፉት 11 ወራት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፥ በመቐለ ብቻ ባለፉት ወራት በ12 ሴቶች ላይ ግድያ የተፈፀመ ሲሆን 80 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መመዝገቡ ይገልፃል። 10 የእገታ ተግባራት፣ 178 የግድያ ሙከራ ወንጀሎች በመቐለ ባለፉት 11 ወራት መፈፀማቸው የመቐለ ፖሊስ ፅሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። በመቐለ ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታ መሰረት ያደረጉ ወንጀሎች መበራከታቸው በተለያዩ አካላት ይገለፃል። በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈፀሙ ያሉ በሴቶች የሚደርሱ ጥቃቶች በማውገዝ ከሃያ አምስት በላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በጋራ በሰጡት መግለጫ፥ ከጦርነቱ በኃላ ጭምር በትግራይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ግፎች፣ ዓመፅ፣ ማገት እና መግደል በስፋት መቀጠላቸው አስታውቀዋል። ሲቪል ተቋማቱ በትግራይ ያሉ የፍትህ እና ፀጥታ ተቋማት በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በመከላከል እና ተጠያቂነት በማረጋገጥ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሐላፊነት እየተወጡ አይደለም በማለትም ወቅሰዋል።

የሲቪል ተቋማቱ በመወከል መግለጫው ያቀረቡት የራይዝ ኤንድ ሻይን የሴቶች ማብቅያ ማእከል ሐላፊ ሰላማዊት ግደይ፥ ወንጀሎቹ ሴቶች በአጠቃላይ ሕብረተሰቡ ለአደጋ ያጋለጡ ብለዋቸዋል። ሰላማዊት "እነዚህ ፆታ መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የወንጀሎች ዓይነት እና መጠን ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከቱ መሆኑ የሚያመለክቱ ከመሆናቸው በተጨማሪ የአፈፃፀማቸው ሁኔታ ደግሞ በጣም አስነዋሪ፣ ጭካኔ የተሞላበት፣ የሕብረተሰባችን ሞራል እና ክብር የሚነካ አሰቃቂ ተግባርነው" ብለዋል። 

ከሃያ አምስት በላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በሴት ላይ በደል ይቁም ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጡ
ከሃያ አምስት በላይ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በሴት ላይ በደል ይቁም ሲሉ በጋራ መግለጫ ሰጡ ምስል Million Hailesilassie/DW

ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በተደጋጋሚ በትግራይ እየታዩ ያሉ ወንጀሎች የትግራዩ ጦርነት ቢቆምም፥ ሴቶች አጠቃላይ ሕብረተሰቡ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንዳይመለስ ዕንቅፋት ሆነው ያሉ ናቸው ብለዋቸዋል። "በአጠቃላይ እነዚህ ተግባራት፥ ዓለምአቀፍ ወንጀሎች እንደተፈፀሙበት በተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎች የተረጋገጠው የትግራይ ጦርነት ቢያልቅም፥ ህዝባችን ቀጣይነት ካለው ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይወጣ የሚያደርጉ እና ዓለምአቀፍዊ፣ አህጉራዊ እና ሃገራዊ ሰብአዊ ሕግችና ቃልኪዳኖች የሚፃረሩ ናቸው" ብለዋል።

መንግስት ወንጀሎቹ በመከላከል እና ፍትህ በማረጋገጥ በኩል የሚጠበቅበት ተግባር እየፈፀመ እንዳሎሆነም ሲቪል ተቋማቱ አንስተዋል።"በተለይም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የፍትህ እና የፀጥታ ተቋማት የእነዚህ ወንጀሎች እና ክስተቶች ቀጣይ አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት በቅንነት፣ በገለልተኛነት እንዲሁም ተጠያቂነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ በአፋጣኝ ሕግ የማስከበር ሐላፊነታቸው ሊወጣ ይገባል። ይሁንና እስካሁን ያሉ አካሄዶች ስንገነዘብ የችግሩ ስፋት እና አደጋ ግምት ውስጥ ያላስገባ፥ በተለይም ደግሞ ሰፊ የተጠያቂነት ክፍተት የታዘብንበት ነው የሚል እምነት አለን" ሲቪል ተቋማቱ ይላሉ።

በትግራይ የተበራከቱ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በመቃወም በቅርቡ በመቐለ ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል። የክልሉ አስተዳደር ችግሩ እንደሚገነዘብ እና ይህ ለመፍታት እየሰራ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይገልፃል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
አዜብ ታደሰ 
ፀሃይ ጫኔ