1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል የሕወሓትና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍጥጫ ቀጥሏል

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2017

የትግራይ ኃይሎች፦ በክልሉ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በሕዝብ ዘንድ መረባበሽ ፈጥረዋል አሉ ። በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሊቀመንበርነት የሚመራው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ያለው ፍጥጫ አልረገበም ።

https://p.dw.com/p/4lY1N
የህወሓት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጥጫ እንደቀጠለ ነው
የህወሓት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጥጫ እንደቀጠለ ነውምስል Million Hailesilassie/DW

ትግራይ ክልል ፍጥጫው ቀጥሏል

የትግራይ ኃይሎች፦ በክልሉ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በሕዝብ ዘንድ መረባበሽ ፈጥረዋል አሉ ። በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሊቀመንበርነት የሚመራው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ያለው ፍጥጫ አልረገበም ።  በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው መካረር እንዳሳሰባቸው የገለጡት የትግራይ ኃይሎች ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር እንደማይፈቅዱ ዐሳውቀዋል ። ሁኔታውንም በዝምታ አንመለከትም ሲሉም አቋማቸው ይፋ አድርገዋል ።   

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሊቀመንበርነት የሚመሩት የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቡድን ትላንት እንዳስታወቀው መስከረም 24 ካደረገው የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ ሕወሓትን ወክለው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያሉ ባለስልጣናት ከሓላፊነታቸው እንዲወርዱ መወሰኑ ይፋ አድርጓል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዳለው የገለፀው የሕወሓቱ ቡድኑ፥ ሕወሓትን ወክለው በግዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ፣ የዞን አስተዳደር እና ኤጀንሲዎችና ኮምሽኖች ያሉ ባለስልጣናት መቀየሩ ገልጿል።

አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 13 ባለስልጣናት ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስልጣናቸው ማንሳቱ የገለፁው ይህ የህወሓት ቡድን፥ በዚህ ጉዳይ ዙርያም ከፌደራሉ መንግስት ጋር ንግግር እንደሚያደርግ ማስታወቁ ይታወሳል። የሕወሓቱ መግለጫ ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባሰራጨው የጽሑፍ መግለጫ  ደግሞ፣ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓቱ ቡድን ከዚህ በፊት የተለያዩ ማደናገርያዎች እያሰራጨ መቆየቱ በማንሳት፥ አሁን ላይ ግን በግልፅ "መፈንቅለ ስልጣን እንዳደረገ አውጇል" ብሏል። ይህም "ስርዓት አልባነት እንዲሰፍን ያለው ፍላጎት ማሳያ" ተደርጎ የሚታይ ነው ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ጨምሮ ይገልፃል።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በዚህ "የጥፋት ኃይል" ብሎ የገለፀው አካል ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ያስታወቀ ሲሆን፥ ይህ ተከትሎ ለሚፈጠር ማንኛውም ጥፋት ደግሞ ተጠያቂው ይህ ቡድን እና አመራሩ ነው ትላንት አስታውቋል።

ትግራይ ክልል ውዝግቡ እንደቀጠለ ነው
ትግራይ ክልል ውዝግቡ እንደቀጠለ ነው ፤ መቀለ ከተማምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

የእነዚህ ሁለት አካላት ውዝግብ  ተከትሎ ደግሞ የትግራይ ሐይሎች ትላንት ማታ ባሰራጩት አጭር የፅሑፍ መልእክት፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ማስተካከል አስመልክቶ ሁለቱ አካላት ተፃራሪ መግለጫዎች መውጣታቸው በማንሳት፥ ይህም በህዝብ ዘንድ መረባበሽ ፈጥሯል ብሏል።

"የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች የትግራይ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ፣ እየወጡ ባሉ መግለጫዎች የሚፈጠር ስርዓት አልባነት ሊኖር እንደማይፈቅድ እና በዝምታ እንደማናይ ልናሳውቅ እንሻለን" ሲልም አቋሙ አስታውቋል።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ይሁን በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በጽሑፍ ከሰጡት መግለጫ ውጭ ተጨማሪ ማብራርያ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።

በህወሓት ሁለት ቡድኖች ስላለው ውዝግብ እና የፀጥታ ሐይሎቹ አቋም ዙርያ አስተያየታቸው ያጋሩን የሕግ ምሁሩ እና ፖለቲካዊ ሁኔታው በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ የሁለቱ አካላት አቋም ከሕግ አንፃር ያዩታል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ