1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል ሥራ ያላቸዉ ወጣቶች ከ20 በመቶ ያነሱ ናቸዉ-ጥናት

ረቡዕ፣ ሰኔ 5 2016

ከጦርነቱ በፊት በትግራይ የስራ አጥ ወጣቶች መጠን 30 ከመቶ እንደነበረ የሚገለፅ ሲሆን፥ የደረሰው ውድመት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው አሁን ላይ በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 81 ከመቶዎቹ ስራ አጥ ሆነው እንዳለ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክት የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ይገልፃል።

https://p.dw.com/p/4gvFD
ከጦርነቱ በኋላ የትግራይ ወጣቶች ለሠላም እንዲጥሩ የሚደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም ወጣቱ በቂ ሥራ የለዉም
በቅርቡ የትግራይ ወጣቶች ለሠላም በሚል ዐባይ መርሕ ላይ የመከረዉ ጉባኤ መቀሌ ዉስጥ ሲደረግ ምስል Million Haileyessus/DW

ትግራይ ክልል ሥራ ያላቸዉ ወጣቶች ከ20 በመቶ ያነሱ ናቸዉ-ጥናት

በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 81 ከመቶዎቹ ስራአጥ መሆናቸውና 40 ከመቶዎቹ መሰደድ እንደሚፈልጉ አንድ ጥናት አረጋገጠ። የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በክልሉ ለሁለት ዓመት ከተደረገዉ ጦርነት በኋላ ያለዉ ሁኔታ ለወጣቶች ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።

ከጦርነቱ በፊት በትግራይ የስራ አጥ ወጣቶች መጠን 30 ከመቶ እንደነበረ የሚገለፅ ሲሆን፥ የደረሰው ውድመት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው አሁን ላይ በትግራይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 81 ከመቶዎቹ ስራ አጥ ሆነው እንዳለ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክት የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ይገልፃል። የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ስራአስኪያጅ ሰናይ ከሓሰ እንደሚሉት ስራ አጥ ከሆነው በተጨማሪ 89 ከመቶ የሚሆን በትግራይ የሚገኝ ወጣት ምንም ዓይነት ገቢ የለውም።

ከፖለቲካ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ጥናቱ ዳሰሳ ማድረጉ የሚገልፁት የወጣቶች ማሕበሩ ስራአስኪያጅ ሰናይ ከሓሰ፥ 66 ከመቶ የሚሆኑ የትግራይ ወጣቶች በፖለቲካ ጉዳዮች መሳተፍ እንደማይፈልጉ እንደሚገልፁ፥ ይህም ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተስፋ ከማጣት ሊመነጭ የሚችል እንደሆነ ጨምረው ያስረዳሉ።

 

የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ስራአስኪያጅ ሰናይ ከሓሰ
የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ስራአስኪያጅ ሰናይ ከሓሰ ምስል Million Haileselassie/DW

በተለያየ መንገድ በፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፍ እንደሚፈልጉ የገለፁ 34 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሲሆኑ፥ 10 ከመቶዎቹ በተቃውሞ የፖለቲካ ረድፍ መሰልፍ እንደሚፈልጉ የጥናቱ ውጤት ያመለክታል። ሌላው በትግራይ ወጣቶች ዘንድ እየታየ ያለ እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚገለፅለት ችግር ስደት ነው። የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ጥናት እንደሚለው በትግራይ ካሉ ወጣቶች መካከል 40 ከመቶዎቹ ትግራይን ለቀው መሰደድ ይሻሉ።

የትግራይ ወጣቶች ማሕበር ባደረገዉ ጥናት መሠረት 81 ከመቶዉ የትግራይ ወጣት ሥራ አጥ ነዉ
የመቀሌ ወጣቶች የሥራ ማስታወቂያ ሲከታተሉ።ከጦርነቱ በኋላ የትግራይ ወጣቶች ሥራ የማግኘት ከፍተኛ ችግር አለባቸዉ።ምስል Million Hailesilasse/DW

በሃገርህ ተረጋግቶ ላለመኖር የኢኮኖሚ ችግር፣ የዳግም ጦርነት ስጋት፣ አጠቃላይ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ማጣት ወጣቱ ለስደት እየገፉ መሆኑ በተለያዩ አካላት ሲገለፅ ቆይቷል። በጥናቱ የወጣቶች ማሕበራዊ ሁኔታም ለመዳሰስ የተሞከረ ሲሆን፥ 86 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ትዳር የመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው፥ ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው ኢኮኖሚያዊ መሆኑ ተገልጿል።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በተለይም ከጦርነቱ በኃላ የክልሉ ወጣቶች በአስቸጋሪ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ እንዳሉ፥ ስደት በስፋት አማራጭ እየሆኑ መምጣቱ እንደሚያሳስበው ይገልፃል። ሊወሰዱ ከሚገባ ኢኮኖሚውም የሚያነቃቁ፣ ለወጣቱ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እርምጃዎች በተጨማሪ በሕገወጥ ስደት አስከፋነት ዙርያ የግንዛቤ መፍጠር ተግባራትም እንደሚያስፈልግ ያነሳል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ