ትኩረት በአፍሪቃ፣ የጋቦን መፈንቅለ መንግሥት አንደኛ ዓመት።አፍሪቃ በፀጥታዉ ምክር ቤት
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 25 2016
የጋቡን ጦር ኃይል የሐገሪቱን የረጅም ጊዜ አገዛዝ ከሥልጣን ካስወገደ ትናንት አንድ ዓመት ደፈነ።ትንሺቱ ሐብታም አፍሪቃዊት ሐገር ግን አሁንም ቋሚ ወይም የተመረጠ መንግስት የላትም።አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የአፍሪቃ መንግስታት የሚያደርጉት ጥሪና ጥረት እስካሁን ለፍሬ አልበቃም።ለምን? የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ሁለቱን ርዕሶች ይቃኛል።
ከመጀመሪያዉ እንጀምር።ማሊ በ2020 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀመረች።ደገመችም-መፈንቅለ መንግስት።ጊኒ ተከተለች።ቡርኪና ፋሶ አሰለሰች።ኒዠርም ተቀየጠች።ጋቡን አሳረገች። እርግጥ ነዉ መሐል ላይ ሱዳንም መፈቅለ መንሥት አከል የሥልጣን ሽሚያ ነበር።ሱዳን ስትቀነስ ከ2020 ጀምሮ ፖለቲካዊ ሥርዓታቸዉ በመፈንቅለ መንግሥት የተመሠቃቀለዉ በሙሉ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሐገራት ናቸዉ።
በየመፈንቅለ መንግሥቱ ከሥልጣን የተወገዱት የየሐገራቱ መሪዎች ወይም መንግሥታት የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ የፈረንሳይ በፈረንሳይ በኩል የምዕራባዉያን ታማኞች የነበሩትን ያክል ወታደራዊ ሁንታዎቹ ከዕራባዉያኑ ፈንጠር፣ ገሸሽ፣ራቅ እያሉ ወደ ምሥራቅ በጣሙን ወደ ሩሲያ እየተጠጉ ነዉ።ወታደራዊ ገዢዎቹ የቀድሞዎቹን መሪዎች ከሥልጣን ለማሰወገዳቸዉ ከሚሰጧቸዉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱም የቀድሞዎቹ መሪዎች ለፈረንሳይና ወዳጆችዋ ሲበዛ አጎብድደዋል የሚል ነዉ።
CDU በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉን የጀርመኑን ተቃዋሚ ፓርቲ አስተሳሰብ ያራምዳል የሚባለዉ የኮንራድ-አደናወር መታሰቢያ ጥናት ተቋም የሕግ ሥርዓት ጉዳይ ባለሚያ ኢንጎ ባዶሬክ ግን የጋቡን ወታደራዊ ሁንታ ከሌሎቹ ይለያል ባይ ናቸዉ።
«የማሊ፣የቡርኪና ፋሶ ወይም የኒዤር የጦር መኮንኖች በሕዝብ የተመረጡትን መሪዎች ከሥልጣን ያስወገዱት የየሐገሩን ሕዝብ ቅሬታና የደሕንነት ሥጋት ተጠቅመዉ የየራሳቸዉን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ነዉ።የጋቡን ወታደራዊ መንግስት ግን ከሥልጣን ያስወገደዉ የረጅም ጊዜ ፈላጭ ቆራጭ ገዢን ነዉ።»
በቃ! በቃ ነዉ።የ«ነገደ-ቦንጎ» የ50 ዘመን ሥርዓት
ጋቡን ትንሽ ናት።የአጠቃላይ ሕዝቧ ቁጥር ከአዲስ አበባ ነዋሪ በጅጉ ያንሳል።2.3 ሚሊዮን።። ይሕቺ የማዕከላዊ አፍሪቃ ትንሽ ሐገር በነዳጅ ዘይት፣ በከበሩ ድንጋዮችና በደን ሐብት የበለፀገች ናት።ከነፃነት ጊዜ ጀምሮ እስከ አምና ድረስ ሐገሪቱን እንደ ግል ሐብታቸዉ የገዙት ግን ሁለት ሰዎች ናቸዉ። አባትና ልጅ።ዑመር ቦንጎ ከ1967 ጀምረዉ ሐገሪቱን ለ41 ዓመታት ገዝተዋል።በ2009 ባይሞቱ ኖሩ ምናልባት ለተጨማሪ ዘመን ይገዙ ነበር።
ሞት አይቀር።ዑመር ሲሞቱ ልጃቸዉ ዓሊ ቦንጎ ተተኩ። በ2016 በተደረገዉ ምርጫ ዓሊ ሰባት ዓመት የቆዩበትን ያባታቸዉን መንበር እደያዙ የቀጠሉት ከብዙ ዉዝግብ በኋላ ነዉ።ዉዝግቡ ባስከተለዉ ግጭት 27 ሰዎች ተገድለዋል።አምና በተደረገዉ ምርጫም «አሸነፉ» ተባለ።ከዓሊ ቦንጎ ቤተሰብና ከሥርዓታቸዉ ተጠቃሚዎች በስተቀር ዉጤቱን ያመነ አልነበረም።በተለይ ጦሩ አመረረ።የምርጫዉ ዉጤት በተነገረ በሶስተኛዉ ቀን ፕሬዝደንታዊ ዘብ የተባለዉ የቦንጎ ልዩ ጠባቂ ጦር አስፈሪዉን መሪ ከሥልጣን አስወገደ።ከቤታቸዉ እንዳይንቀሳቀሱ አገደ።የምርጫዉን ዉጤትም ሰረዘ።ትናት ዓመቱ።
«ይሕን አሁን ጋቡን ዉስጥ ያለምንም ደም መፋሰስ የተደረገዉን ለዉጥ እንደግፋለን።ሰዉ ክቡር፣ሕይወትም ቅዱስ ነዉ።ሥልጣን የሚፈልግ ማናቸዉም ወገን ሰዉ መግደል የለበትም።»
አሉ መፈንቅለ መንግሥቱን ቀድመዉ የደገፉት የሊቨርቢል የካቶሊክ ጳጳስ ቃል አቀባይ ሰርጌ-ፓትሪክ ማቢካሳ-ያኔ።በቦንጎ ቤተሰቦች የ50 ዘመን አገዛዝ የተማረረዉ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ቦረቀ።
ጋቡን እንዳልነዉ ሐብታም ናት።የዓለም ባንክ እንደሚለዉ የሐገሪቱ ሕዝብ አማካይ የነብስ ወከፍ ገቢ ከሰሐራ በረሐ በስተደቡብ ከሚገኙ ከአብዛኞቹ ሐገራት የተሻለ ነዉ።4500 ዶላር።ይሁንና 2.3 ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ አንድ-ሶስተኛዉ ደሐ ነዉ።ብዙ ወጣት ሥራ የለዉም።ደኸዉ ለድህነቱ ተጠያቂ የሚያደርገዉ ሥርዓት ሲገረሰስ የማይደሰትበት ምክንያት በርግጥ የለም።ከዚሕም በተጨማሪ ከ2 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ጋቡናዊ የካቶሊክ ክርስትና እምነት ተከታይ ነዉ።የቦንጎ ቤተሰቦች በ1970 እስልምናን በመቀበላቸዉ ካቶሊኮቹ የረጅም ጊዜ ቅሬታ አላቸዉ።
የጦር ኃይሉ ዘዴ
መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩና ያቀነባበሩት የጦር መኮንኖች ቢያንስ ሶስት ተቃራኒ እዉነቶችን የሚያስታርቁበት ብልሐት የተከተሉ መስለዋል።በጦር ኃይሉ ዘንድ ክፍፍል እንዳይፈጠር-አንድ።የአብዛኛዉን ሕዝብ ቅሬታ መመለስ-ሁለት።ከሥልጣን የተወገደዉ ኃይል ወይም ደጋፊዎቹ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተቃዉሞ መቀነስ-ሶስት።
ተቃርኖዎቹን ሊያጣጥም የሚችል መሪ ሾሙ።ጄኔራል ብሪስ ኦሊጉይ ንጉይማን።ሰዉዬዉ በጦሩ ዘንድ የተከበሩ ናቸዉ።የካቶሊክ ክርስትና እምነት ተከታይ ናቸዉ።የዓሊ ቦንጎ ያጎት ወይም ያክስት ልጅም ናቸዉ።ተቃርኖዉን ለማጣጣም በልክ የተሰሩ።ወይም የሚመስሉ ናቸዉ።
ጄኔራሉ የሚመሩት ወታደራዊ ሁንታ ሥልጣን ላይ የሚቆይበት ጊዜ ከ24 ወራት እንደማይበልጥ ቃል ገብቷል።የሐገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቢል ማሕበራትና ሌሎች የሐገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ የተሳተፉበት ብሔራዊ ምክክርም እስካለፈዉ ሚያዚያ ማብቂያ ድረስ ተደርጓል።
የብሔራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች ከወሰኑት ጉዳይ አንዱ ፕሬዝደንት የሚመረጥበት ሒደትና ዘመነ ሥልጣኑን የሚገድብ ሕግን ማፅደቅ ነዉ።ፕሬዝደንትነቱ ሥልጣን የሚይዘዉ ለሁለት ዘመነ ሥልጣን ብቻ ነዉ።የመጀመሪያዉ ምርጫ የሚደረግበት ጊዜ ግን እስካሁን አልታወቀም።
የኮንራድ-አደናዉር መታሰቢያ ጥናት ተቋም የሕግ ሥርዓት አዋቂ ኢንጎ ባዶሬክ ከተስፋ ሌላ ሌላ ማረጋገጪያ የለም ባይ ናቸዉ
«ያለን፣ የጋቡን ወታደራዊ መንግስት እንደታሰበዉ በመጪዉ ነሐሴ 2025 ምርጫ ይጠራል የሚል ተስፋ ብቻ ነዉ።ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሚደረግበት ተጨባጭ የጊዜ ሰሌዳ የለም።ባለፈዉ ሚያዚያ የተጠናቀቀዉ ብሔራዊ ምክክር ምርጫ እንዲደረግ ወስኗል።ይሁንና ምርጫዉን የሚያዘጋጀዉ የጋቡን የሐገር አስተዳደር ሚንስቴር ተጨባጭ ዕቅዱን እስኪያስታዉቅ ድረስ መጠበቅ አለብን።»
ጄኔራል ኦሊጉይ ንጉይማ ሥልጣን አለቀቅም ቢሉስ?
ጄኔራል ኦሊጉይ ንጉይማ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ መቀጠል ቢከጅሉስ።በርግጥ አያስደንቅም።ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ የተለመደ ነዉ።የጦር መኮንኖች በመፈንቅለ መንግሥት፣ የአማፂያን መሪዎች በፊትለፊት ዉጊያ ቀዳሚዎቻቸዉን አስወግደዉ «ጊዚያዊ»ና «የሽግግር» በሚል ሽፋን የያዙትን ሥልጣን ኋላ በድምፅ አስፀድቀዉ መሎያቸዉን እያወለቁ በሱፍ-ከራባት ሐገር መግዛት ለአፍሪቃ እንግዳ አይደለም።ራቅ ሲል ሙሴ ቬኒ፣ፖል ካጋሚ፣ አል ሲሲ ሌሎችም አድርገዉታል።
ንጉይማም ተመሳሳዩን ለማድረግ እያደቡ ነዉ የሚለዉ መላምትና ወሬ ሊቨርቢል ዉስጥ እየናኘ ነዉ።ሰዉዬዉ የፕሬዝደንታዊዉን ምርርጫ ጊዜ አላሳወቁም።የአሉባልታዉ አንዱ መሠረትም የምርጫዉ ጊዜ መሸሸጉ ነዉ።የሲቢል ማሕበራት አቀንቃኞች ግን ጄኔራሉ በርግጥ የታሙበትን ካደረጉ ሌላ ሕዝባዊ አመፅ እንጠራለን ባዮች ናቸዉ።ይሆን ይሆን? ጊዜ ነዉ መልስ ሰጪዉ።
የአፍሪቃ የሩቅ ሕልም
የማላዊ ፕሬዝደንት ላዛረስ ቻክዌራ በቅርቡ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በርካታ አቻዎቻቸዉ ለዘመናት የተመኑ፣ ያሉና ያስባሉትን ደገሙት።አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተገቢዉን ዉክልና አላገኘችም።
«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሰረት ከጥቂት ሐገራት በስተቀር ብዙዎቻችን አልነበርንም።እዉነቱን ለመናገር የዚያ ስምምነት አካል አይደለንም።በዚሕም ምክንያት አፍሪቃ በተለይ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ተገቢዉ ተሳትፎ እንዲኖራት ግፊት እያደረግን ነዉ።እና ሥለጉዳዩ የመናገር እድል ባገኘሁ ቁጥር እነዚሕን ጥያቄዎች አነሳለሁ።»
ምክር ቤቱ
ምክር ቤቱ 15 አባላት አሉት።አምስቱ ቋሚ ናቸዉ።ብሪታንያ፣ ቻይና ፣ፈረንሳይ፣ ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ።እነዚሕ ሐገራት አንዱ የራሱን ወይም የወዳጆቹን ጥቅም የሚነካ ረቂቅ ደንብ ሲቀርብ ሌሎቹ ቢደግፉት እንኳን ረቂቁን ዉድቅ የማድረግ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን አለዉ።የተቀሩት 10ሩ በየሁለት ዓመቱ የሚለዋወጡ በየአካባቢዉ የሚወከሉ አባል ሐገራት ናቸዉ።ከ10ሩ ሶስቱ ለአፍሪቃ የተመደበ ነዉ።
አሁን ባለዉ ምክር ቤት ዉስጥአፍሪቃን የሚወክሉት አልጄሪያ፣ሞዛምቢክና ሴራሊዮን ናቸዉ።ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ አባላት 28 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪቃ ሐገራት በዓለም አቀፉ ድርጅት ትልቅ ዉሳኔ ሰጪ አካል ዉስጥ ያላቸዉ ዉክልና በጣም ትንሽና አቅመ ቢስ መሆኑ በርግጥ ለብዙዎች አስተዛዛቢ ላንዳዶች አናዳጅ ብጤም ነዉ።
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንዲሰፋ ጥሪና ግፊት መደረግ ከጀመረ ቆይቷል።በቅርብ ዓመታት ደግሞ ጥሪዉ ተጠናክሯል።የተገቢ ዉክልና ጥያቄ የሚያነሱት አፍሪቃዉያን ብቻ አይደሉም።ሌሎችም ይጠይቃሉ።ይሁንና ምክር ቤቱ እንዴት ይስፋ፣ ሥልጣንና ሐላፊነቱ፣ የአባላቱ ብዛት ወዘተ የሚለዉ ሐሳብ ግን እንዳከራከረ ነዉ።
የአፍሪቃ የቋማ መቀመጪያ ጥያቄ
ባለፈዉ ነሐሴ መጀመሪያ የተሰየመዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ አፍሪቃ ተገቢዉ ዉክልና እንዲኖራት በቀረበዉ ጥያቄ ላይ ተነጋግሮ ነበር።በዉይይቱ ላይ የተካፈሉት የሴራሊዮኑ ፕሬዝደንት ጁሊየስ ማአዳ ቢዮ «አፍሪቃ ተጨማሪ ድምፅ እንዲኖራት ለብዙ አስርታት ጮሐለች አሉ» ለጉባኤተኞች።ከእንግዲሕ ግን አትታገስም።አከሉ።
«አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ሁለት ቋሚ መቀመጫ ትፈልጋለች።በተለዋጩ መቀመጫ ደግሞ ሁለት ተጨማሪ መቀመጫዎች ትፈልጋለች።ይሕ ማለት ሁለት ቋሚና አምስት ተለዋጭ መቀመጫ ማለት ነዉ።አባላቱን የአፍሪቃ ሕብረት ይመርጣል።አፍሪቃ ድምፅን በድምፅ የመሻሩ ሥልጣን እንዲሰረዝ ትፈልጋለች።ይሁንና አባል ሐገራት ድምፅን በድምፅ የመሻሩ ሥልጣን እንዲቀጥል ከፈለጉ አዲስ የሚገቡት ቋሚ አባላትም ሥልጣኑ ሊኖራቸዉ ይገባል።»
ባዮ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ብዛት፣ሥልጣንና ኃላፊነትን ለማሻሻል የአፍሪቃ ሕብረት የወከለዉ ኮሚቴ ሊቀመንበር ናቸዉ።C-10 የሚባለዉ ኮሚቴ አስር አባል ሐገራትን ያስተናብራል።
አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ተገቢዉን ዉክልና ለምን ተነፈገች
ብዙዎች እንደሚተቹት አሁን ያለዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መዋቅር ኋላቀርና ያረጀ ነዉ።ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት ያሸነፉት ሐገራት እንደ ጦር ሜዳዉ ሁሉ በአለም የፍትሕ መድረክም እንዳሻቸዉ እንዲፈነጩበት ታስቦ የተዋቀረ ነዉ ባዮች ቁጥርም ቀላል አይደለም።
በመሠረቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ዓላማ የዓለምን ሠላምና ደሕንነት ማስከበር ነዉ።የዓለምን ሰላም በማስከበሩ ሒደት 54ቱ የአፍሪቃ ሐገራት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ በየሐገሩ ካዘመታቸዉ ሰላም አስከባሪዎች 40 በመቶዉ አፍሪቃዉያን ናቸዉ።ይሁንና አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ያላት ተሰሚነት ዉስን ወይም ምንም ነዉ።«ተገቢ አይደለም» ይላሉ ጉተሬሽ።
«የዓለም የሠላምና የፀጥታ አስከባሪ ግዙፍ ድርጅት ዉስጥ ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጥ ወጣትና በማደግ ላይ ያለ ሕዝብ የሚኖርባት አሐጉር ቋሚ ድምፅ እንዲኖራት አለመደረጉ ተቀባይነት ሊኖረዉ አይችልም።ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባላት 28 በመቶዎቹም የአፍሪቃ ሐገራት ናቸዉ።የሠላምና የፀጥታን ጉዳይ በተመለከተ ከአፍሪቃ የሚመነጨዉ ሐሳብም ተቀባይነት አለማግኘቱን አንቀበለም።»
ተባለ።ግን እስካሁን የሆነ ነገር የለም።እንዲያዉም አፍሪቃ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ላቅ ያለ ተሰሚነት እንዲኖራት የሚደረገዉ ግፊትና ጥረት ከሌላ አቅጣጫ ሌላ መዘዝ እየጎተተ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃዉያኑን ጥያቄ በቀጥታ ባትቃወምም የደቡብ አሜሪካና የካረቢክ ሐገራትም ቋሚ መቀመጫ ሊያገኙ ይገባል ማለት ይዛለች።ጀርመንና ጃፓንም ከድሮ ጀምሮ የቋሚ መቀመጫ ጥያቄ ሲያነሱ ነበር።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ