1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፣ ሱዳን-አል ዑቤይድ ላይ ያጠላዉ ሥጋት፤ የጊኒ ቢሳዉ ቀዉስ

ነጋሽ መሐመድ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 13 2018

ከዚሕ ዉስጥ ከ14 ሚሊዮን የሚበልጠዉ አንድም ተፈናቃይ ሁለትም ሥደተኛ ነዉ።የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) እና የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ባለሥልጣናት ባገባደድነዉ ሳምንት አጋማሽ እንዳሉት በዓለም በርካታ ሕዝብ ለረሐብ ከተጋለጠባቸዉ 13 ሐገራት ወይም ግዛቶች ግንባር ቀደሟ ሱዳን ናት።

https://p.dw.com/p/5FjYv
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ሰሜን ኮርዶፋን ትልቅ ከተማ አል ዑቤይድን ለመያዝ እየተዘጋጀ መሆኑ በሰፊዉ እየተዘገበ ነዉ
የሱዳን መከላከያ ጦር (SAF) አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን (ከመሐል) አል ዑቤይድ የሰፈረ ጦራቸዉን ሲያበረታቱምስል፦ Mohamed Sid Ahmed/Xinhua/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ፣ ሱዳን-አል ዑቤይድ ላይ ያጠላዉ ሥጋት፤ የጊኒ ቢሳዉ ቀዉስ

 

የሱዳን ምሥቅልቅል-ዓለም ይማፀናል፣ ጦርነቱ ቀጥሏል 

በማሽላ፣ ድኩን፣ ስንዴ ምርቷ የምትታወቀዉ፣ በጥጥ ሽያጯ በዓለም ገበያ የምትፈለገዉ፣ በወርቅ ማዕድኗ ብዙ የአፍሪቃ ሐገራትን የምታስንቀዉ ሰፊዋ የአረብ-አፍሪቃ ቅይጦች ምድር ዛሬ የጉልበተኞች መፋለሚያ፣ የደካሞች ማለቂያ፣ የተፈናቃዮች መናኸሪያ እና የተመፅዋቾች ሐገር ሆናለች።ሱዳን።ሙዚቃዋስ ቢሆን? ያቺን የየዋሕ-ደጎች ሐገር በጋራ ይገዙ የነበሩት የሱዳን ጦር ኃይል (SAF) እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) አዛዦች ጠብ ተካርሮ ዉጊያ ከገጠሙ ከሚያዚያ 2023 ወዲሕ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስከ 400ሺሕ የሚገመት ሱዳናዊ አልቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ግማሽ ያክል ሕዝቧ-22 ሚሊዮን ገደማ-የምግብ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።ከዚሕ ዉስጥ ከ14 ሚሊዮን የሚበልጠዉ አንድም ተፈናቃይ ሁለትም ሥደተኛ ነዉ።የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) እና የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ባለሥልጣናት ባገባደድነዉ ሳምንት አጋማሽ እንዳሉት በዓለም በርካታ ሕዝብ ለረሐብ ከተጋለጠባቸዉ 13 ሐገራት ወይም ግዛቶች ግንባር ቀደሟ ሱዳን ናት።
«በከፍተኛ ደረጃ ከሚያሳስቡት መካከል ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣የመን፣ፍልስጤም፣ ናይጄሪያና ሶማሊያ ዋነኞቹ ናቸዉ።እነዚሕ ሐገራት በርካታ ሕዝብ በረሐብ ለሞት የተደረ,ገባቸዉ ወይም ለሞት በሚያደርስ ረሐብ የሚሰቃይባቸዉ ናቸዉ።»
ይላሉ ዤን-ማርቲን ባወር የዓለም ምግብ ድርጅት የምግብ ዋስትና የበላይ ኃላፊ።

የለጋሽ ሐገራት መሰላቸት፣ ርዳታመቀነስና የሕዝቡን መከራ ከቁብ አለመቁጠር የምግብ እጥረቱን ወደ ረሐብ ሥጋት እንዲንር አድርጎታል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሐን ሐቅ በቅርቡ እንዳሉት ተፋላሚ ኃያላት በድልድዮች፣መንገዶችና የርዳታ ካሚዮኖች ላይ የሚያደርሱት ድብደባ የተገኘችዉንም እሕል ለችግረኛዉ ለማቃመስ ፈተና ሆኗል።
«በድልድዮች፣ መንገዶችና በሌሎች በጣም አስፈላጊ የሲቪል መዋቅሮች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት መባባስ፣ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦቱን እያደናቀፈዉ፣ ሰላማዊ ሰዎችን ይበልጥ ለአደጋ እያጋላጠ መሆኑን ያስጠንቅቃሉ።

ምዕራብና ማዕከላዊ ዳርፉርን የሚያገናኘዉ የጀኒን-ዛሊንጊይ አዉራ መንገድ በፀጥታ መታወክ ምክንያት ላጭር ጊዜ ከተዘጋ በኋላ አሁን እንደገና ተከፍቷል።ይሁንና የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት አሁንም አስተማማኝ አይደለም።»
የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት አንድም ዉጊያ በመቀጠል፤ ሁለትም ለችግረኛ ርዳታ እንዳይደርስ መንገድ በመዝጋትና በመዝረፍ የሕዝባቸዉን መከራ ከማባባስ ባለፍ እስካሁን ሠላማዊ አማራጭን «እንቢኝ» እንዳሉ ነዉ።እንዲያዉም ዘንድሮ የዉጊያ አድማሳቸዉን አስፍተዉ እስካሁን አንፃራዊ ሠላም የሚታይባቸዉን አካባቢዎችም ወደ ጦርነት አዉድማ ቀይረዋቸዋል።

የሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ጥቃት ያልተጠበቀ መቅሰፍት

የከፋዉ ተፋላሚዎች በተለይ የፈጥኖ ደራሹ ጦር በተደጋጋሚ የሚያዘምታቸዉ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ከተሞች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎችና ሐኪም ቤቶችን ጭምር ማጋያተቻዉ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክ ባለፈዉ ሰኞ እንዳሉት ሱዳን ዉስጥ ካለፈዉ ጥር እስከ ግንቦት በነበረዉ አምስት ወራት ዉስጥ ከ1000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ጥቃት ተገድለዋል።
«ክቡር ፕሬዝደንት!! ሱዳን ዉስጥ ዘግናኙ ግጭት እየተስፋፋና እየተባባሰ ነዉ።የሰዉ አልባ አዉሮፕላን ጥቃትም የዉጊያዉ መለያ ሆኗል።ከጥር እስከ ግንቦት 26 ብቻ ከ1000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በሰዉ አልባ አዉሮፕላን መገደላቸዉን መስሪያ ቤታችን መዝግቧል።ሴቶችን መድፈርና የፆታ ጥቃት እየተደጋጋመ ነዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ካለፈዉ ጥር እስከ ግንቦት በነበሩት አምስት ወራት በሰዉ አልባ አዉሮፕላን ጥቃት ከ1000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል
ፖርት ሱዳን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን ከተመታች በኋላ።ሱዳን ዉስጥ በሚደረገዉ ጦርነት የሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ጥቃት በተደጋጋሚ ይፈፀማል ምስል፦ Sudanese Ministry of Culture and Information/Xinhua/picture alliance

አል ዑቤይድ ዳግማዊት አል ፋሸር ትሆን ይሆን?

ጦርነቱ በርግጥም እየተስፋፋና እየከፋ ነዉ።ሰሞኑን ደግሞ የፈጥኖ ደራሹ ጦር የማዕከላዊ ሱዳን ትልቅ፣ሥልታዊና የንግድ ማዕከል ከተማ አል ዑቤይድን ለማጥቃት በርካታ ተዋጊዎቹን ወደ ከተማይቱ አስጠግቷል።የሰሜን (ሸማል) ኮርዶፋን ዋና ከተማ አል ዑቤይድ ከ3መቶ 50 ሐምሳ ሺሕ በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ትልቅ የንግድ ከተማ ናት።
«የአሸዋዎች ሙሽራ» በሚል ቅፅል የምትቆጳጰሰዉ አል ዑቤይድ ከነባር ነዋሪዎችዋ በተጨማሪ ጦርነት ካየለባቸዉ ከዳርፉር ከተሞችና አካባቢዎች የተፈናቀለ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ሠፍሮባታል።ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳሉት ከተማይቱ ባሁኑ ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ታስተናግዳለች።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ፣ የልዩልዩ ድርጅቶች ተጠሪዎች፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና ኖርዌይን የመሳሰሉ የአዉሮጳ ሐገራት ባለሥልጣናት እንደሚሉት ፈጥኖ ደራሹ  ጦር ትልቂቱን ሥልታዊ ከተማ ካጠቃ ከዚሕ ቀደም አል ፋሻር ላይ የደረሰዉ ዓይነት እልቂት መደገሙ አይቀርም።ፈጥኖ ደራሹ ጦር በሕዝብ የተጨናነቀችዉን  አል-ዑቤድን እንዳያጠቃ ዓለም አቀፍ ድርቶቹና የአዉሮጳ መንግስታት እያሳሰቡ ነዉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የፈጥኖ ደራሹ ጦርን የጥቃት ዝግጅት «ዕብደት» ብለዉታል።ዕብደቱ መቆም አለበት-እንደ ዋና ፀሐፊዉ።የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር የፎልከር ቱርክ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ከዋና ፀሐፊዉም ጠንከር፣ ጠጠር፣ ፈርጠም ያለ ነዉ።ቱርክ እንዳሉት በተዋጊዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ መንግሥታት «ይሕን ዕብደት» የማስቆም ኃላፊነት አለባቸዉ።

«ይሕን ምግባር ከዚሕ ቀደም አይተነዋል።መከላከል እየተቻለ ባለፈዉ ዓመት ሰሜን ዳርፉር አል ፋሸር ዉስጥና ዘምዘም ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የተፈፀመዉና የመዘገብነዉ ግፍ እንዲደገም መፍቀድ የለብንም።አስጊዉን ጥቃትና የተባባሰዉን ዉጊያ ለማስቆም ርምጃ ካልተወሰደ ሰላማዊ ሰዎች የከፋ አደጋ ይደርስባቸዋል።በጣም አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊደርስ ይችላል። ዓለም ይሕን እንደማስጠንቀቂያ ሊወስደዉ ይገባል።ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ መንግሥታት ይሕን ዕብደት ለማስቆም አሁኑ እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።ዓለም እያየ ነዉ።ጥፋቱን ያደረሱና የሚያደርሱ ተጠያቂ መሆን አለባቸዉ።»
ማሳሰቢያ፣ ማስጠንቀቂያ፣ ማስፈራሪያዉ ይንቆረቆራል።ጥያቄዉ ተፋላሚዎችና ደጋፊዎቻቸዉ ይሰሙ ይሆን ወይ ነዉ?  

ጊኒ ቢሳዉ የፖለቲካዊ ቀዉስ አብነት ሐገር

ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ትንሽ ሐገር ጊኒ ቢሳዉ ከቆዳ ሥፋት፣ ከሕዝቧ ቁጥር ትንሽነት፣ ከተፈ,ጥሮ ሐብት-መልከዓ ምድር አቀማመጧ በላይ በፖለቲካ ቀዉሷ ትታወቃለች።

የጊኒ-ቢሳዉ  ወታደራዊ ሁንታን በመቃወም ቢሳዉ ዉስጥ ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱ
የጊኒ-ቢሳዉ ወታደራዊ ሁንታን በመቃወም ቢሳዉ ዉስጥ ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱምስል፦ DW

በ1974 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃነትዋን ካወጀች በኋላ እንደ ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት ድሕነት፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ አመፅና ሙስና ሲፈራርቅባት እንደነበረች አለች።ነፃነቷን ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2014 ድረስ አንድም ፕሬዝደንት ሙሉ ዘመነ-ሥልጣኑን በፕሬዝደንትነት አልቆየም። 5 ዓመት የሚዘልቀዉን ዘመነ-ሥልጣን የጨረሱት በ2014 የተመረጡት ማራዮ ቫዝ  ብቻ ናቸዉ።እስከ 2019 ቆዩ።
የአዲሱ ቀዉስ መነሻ 

ባለፈዉ ሕዳር የፕሬዝደንታዊና የምክር ቤት አባላት  ምርጫ አድርጋ ነበር።ድምፅ ቆጠራ-መደመር መቀነሱ ሲሰላ፣ በድብቅ ያሴሩ ነበር የተባሉ የጦር መኮንኖች የፕሬዝደንት ዑማሮ ሙክታር ሲሶኮ ኢምባሎ መንግሥትን አሥወግደዉ ሥልጣን መያዛቸዉን አወጁ።
መፈንቅለ መንግሥቱ ከመደረጉ በፊት በሥልጣን ላይ የነበሩት ዑመሮ ሙክታር ሲሶኮ ኢምባሎም ዋነኛ ተቀናቃኛቸዉ ፌርናንዶ ዲያስ ዳ ኮስታም ማሸነፋቸዉን አስታዉቀዉ ነበር። አንዳድ ወገኖች  የቀድሞዉ ወታደራዊ መኮንን ዑማሮ ሙክታር ሲሶኮ ኢምባሎ ተቃዋሚያቸዉ  እንደሚያሸንፉ ሲያቁ ወታደሮቹ ያደረጉትን እንዲያደርጉ አዘዋቸዉ ነዉ ይላሉ።
ፕሬዝደንቱ አዘዙም አላዘዙ የመንግሥትነቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት የጦር መኮንኖች ጊዚያዊ  ምክር ቤት መስርተዉ የምርጫዉ ዉጤት አገዱ።ከተቃዋሚ ፖለቲከኞ አንዳዶቹን በቁም ሲያስሩ ሌሎቹን ባይነ ቁራኛ ይከታተሉ ያዙ።ወታደራዊ ሁንታዉ በተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አቀንቃኞች ላይ የሚወደዉ እርምጃ የሚቃወሙ የዉጪ መንግሥታትን ሁሉ «በሐገራችን የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እያለ ይወቅሳል።ይሕ አቋሙ ከጊኒ ቢሳዉ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካላት ፖርቱጋልና ከሌሎች ሐገራት ጋር አቃቅሮታል።

ወታደራዊ ሁንታዉ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የምርጫዉን ዉጤት አግዷል
ወታደራዊ ሁንታዉ ዉጤቱን ያገደዉ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ነበርምስል፦ DW

የተቃዋሚዉ ፖለቲከኛ መታሰርና መዘዙ 

በቅርቡ ደግሞ በፖርቱጋልኛ ምሕፃሩPAIGC ተብሎ የሚጠራዉን የዋነኛዉን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶሚንጎስ ሲሞስ ፔሬይራን ከ,ቤታቸዉ እንዳይንቀሳቀሱ አዝዟል።ተቃዋሚዎች ታሰሩ ነዉ የሚሉት።ፔሬይራን ከመታሰራቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ በተለይ ለዶቼቬለ በሰጡት መግለጫ የወታደራዊዉን ሁንታ እርምጃ አጥብቀዉ ተቃዉመዉ ነበር።
«ይሕ ሥርዓት ሕገ-ወጥ እንደሆነ ያዉቀዋል።በህዝብ አልተመረጠም።አቅሙ የተመሠረተዉ በኃይል ላይ ነዉ።ይሕንን እንቀበልም።በሐገራችን የሚደረገዉ ፖለቲካዊ ሒደት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሚደረግ መሆን አለበት።»
አሉ።ታሰሩ።

የሕግ ሰዎች እስራቱን ሕገ-ወጥ ይሉታል

የሕግ ባለሙያዎች የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን በተለይ የፔሬይራን መታሰር ሕገ-ወጥ ይሉታል።የፔሬይራ ጠበቃ ሮቤርቶ ኢንዴክ እንደሚሉት ደንበኛቸዉ ሁለቴ ወታደራዊ ችሎት ቀርበዉ ነበር።ይሁንና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እስካሁን ድረስ በተቃዋሚዉ ፖለቲከኛ ላይ የመሠረተዉ ክስ የለም።
«ለመታሰራቸዉ ወይም እንዳይንቀሳቀሱ ለመታገዳቸዉ እስካሁን ድረስ የተሰጠን ምንም ማብራሪያ የለም።አቃቤ ሕግ የመሠረተዉ ክስ፣ ያቀረበዉ ምክንያትም ሆነ ከፍርድ በፊት እንዲታሰሩ ለመደረጉ የሰጠዉ ማብራሪያ የለም።ያሉት እቤታቸዉ ቢሆንም እስራት እስራት ነዉ።ልዩነት የለዉም።»
ባለፈዉ ሕዳር ሥልጣን የያዙት የጦር መኮንኖች ከዉጪ በተደረገባቸዉ ግፊት በመጪዉ ታሕሳስ ምርጫ እንደሚደረግ አስታዉቀዋል።ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ወታደራዊዉ ሁንታ ሰሞኑን በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚወስደዉን ርምጃ ያጠናከረዉ በምርጫዉ እንዳይሳተፉ ለማወክ ወይም ለማደከም ነዉ።

ወታደራዊ ሁንታዉ ከፖርቱጋል ጋር የገጠመዉ ዉዝግብ

የዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ መታሰር ወትሮም መፈንቅለ መንግሥቱንና የወታደራዊ ሁንታዉን ርምጃ የምትቃወመዉን የፖርቱጋልን ቅሬታ አንሮታል።የፖርቱጋል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፓዉሎ ራንጌል ፔሬይራን ጨምሮ የታሰሩ ፖለቲከኞች በሙሉ እንዲፈቱ በድጋሚ ጠይቀዋል።ጊኒ ቢሳዉም ባስቸኳይ ወደ ሕገ-መንግሥታዊዉ ሥርዓት እንድትመለስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አሳስበዋል።
ፖርቱጋሊኛ የሚናገሩ ሐገራት ማሕበር (CPLP)፣ የአፍሪቃ ሕብረትና የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሕብት ማሕበረሰብ (ECOWAS)ም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል።የቢሳዎ ወታደራዊ ሁንታ ከተለያዩ ወገኖች የሚሰማዉን ተቃዉሞ፣ ጥያቄና ማሳሰቢያ አጥብቆ ተቃዉሞታል።ጦር ኃይሉ የሚመራዉ የጊዚያዊ  ምክር ቤት ቃል አቀባይ ፌርናንዶ ቫስ «ክብርና ነፃነታችን ለሽያጭ አይቀርብም» ብለዋል።

በፖርቱጋልኛ ምሕፃሩ PAIGC ተብሎ የሚጠራዉን የዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶሚንጎስ ሲሞስ ፔሬይራን ከቤታቸዉ እንዳይንቀሳቀሱ ወታደራዊ ሁንታዉ አዝዟል
በቅርቡ የታሰሩት የጊኒ ቢሳዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶሚንጎስ ሲሞስ ፔሬይራን ጠበቃ ማሪዮ ሊኖ ምስል፦ DW

«የፖርቱጋሉ ሚንስትር ፓዉሎ ራንጌል እና ሊዝበን የሚገኙ አድሐርያን ቡድናት በሙሉ ሊያዉቁት ይገባል።እኛ በየትኛዉም መንገድ ቢሆን የCPLP አባል መሆን አንፈልግም።ብዙ ደም ያፈሰስንለትና የታገልንለት  ክብራችንና ነፃነታችን ለዉይይትም፣ ለሽያጭም አይቀርብም።»
የቀድሞዋ የጊኒ ቢሳዉ ቅኝ ገዢ ፖርቱጋል አሁንም ለትንሺቱ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር ጥብቅ የምጣኔ ሐብት ተሻራኪ ናት።ፖርቱጋል በቢሳዉ ወታደራዊ ሁንታ ላይ ከፍተኛ ግፊት ሥታደርግ የተቀረዉ ዓለም ጉዳዩን ለፖርቱጋል ብቻ ትቶ ችላ ማለቱ የጊኒ ቢሳዉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሲበዛ ቅር አሰኝቷል።
የአትላንቲክ ባሕርን የምትዋሰነዉ ትንሺቱ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር የሕዝቧ ብዛት 2 ሚሊዮን ቢሆን ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ሥለሺ