1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን ዉጊያ፣የአፍሪቃ ቀንድ ቀዉስ

ነጋሽ መሐመድ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 19 2015

ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁሙን ስምምነት በየጊዜዉ እንደሚጥሱ ሁለቱን ወገኖች ከሚያደራድሩት አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ አስታዉቃለች።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲዉ ሚለር ባለፈዉ ሐሙስ እንዳሉት ተፋላሚዎች ቃላቸዉን ካላከበሩ መንግስታቸዉ ማዕቀብ ሊጥልባቸዉ ይችላል።

https://p.dw.com/p/4RsVB
Tschad Flüchtlingscamp Borota Sudan
ምስል Blaise Dariustone/DW

የሱዳን ጦርነት፣ የአፍሪቃ ድርቅና ርዳታ

አባስ ሁሴይን መካከለኛ እንድሜ ላይ የሚገኝ ሱዳናዊ ነዉ።የጄኒንያ-ዳርፉር ነዋሪ።ባንድ ወቅት ባለሱቅ ነበር።አሁን ግን ከዝርፊያ፤ቃጠሎ የተረፈ ዉድቅዳቂ ይለቃቅማል።የተሰባበሩ በሮች፣መስኮቶች፣የተጎደፈሩ ግርግዳዎችን አንጋጥጦ እያየ በተጨረማመቱ የቆርቆሮ-በተገነጣጠሉ የጣዉላ ሰለዳዎች ላይ ባንድ ወቅት ተፅፈዉ የነበሩ የሱ  ቅ ስሞችን ያነባል።ደግሞ ወደሌሎቹ እያመለከተ፣-

 «ዜጎች ከወደሙ ሱቆቻቸዉ መሐል የተረፋቸዉን እየፈለጉ ይለቅማሉ።»

እሱም እንደሌሎቹ የመስተዋት ስብርባሪ፣ የአምፑል ፍርክስካሽ፣ የጨርቅ ብጥስጣሽ፣ የሱካር፣የጨዉ፣የዱቄት፣ የዘይት ፍሳሽ ያጨቀየዉን ወለል እየተዘናገረ ከዉድቅዳቂዎች መሐል የተሻለ ዉዳቂ ያነሳል።

« ሱቆቹን ዳግም ለመክፈት ሞከረን ነበር።ግን አልቻልንም።ምንም የተረፈን የለም።ይሕ የሽቶና የጥሩ መዓዛ መሸጪያ ነበር---ይህን አካባቢ ታዉቁታላታችሁ? ምን ይመስል እንደነበር ታስታዉሳላችሁ?» ይጠይቃል አብረዉት ያሉትን።

ሱቆቹ ተዘግተዉ ሸቀጡ ባደባባይ ይሸጣል ሱዳን
ሱቆቹ ተዘግተዉ ሸቀጡ ባደባባይ ይሸጣል ሱዳንምስል AFP/Getty Images

አብዛኛዉ ካርቱም፣እንዱሩማንም ከዳርፉሯ ጄኒንያ ከተማ የከፋ እንጂ ያነሰ አይደለም።የሱዳን ገዢና የሐገሪቱ ጦር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሐንና የቀድሞ ምክትላቸዉና የፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምዲቲ) የገጠሙት ጠብ ባጭር ጊዜ የሰፊዋን ሐገር ትላልቅ ከተሞች እያወደመ ነዉ።

ሁለቱ ጄኔራሎች የሚያዙዋቸዉ ኃይላት ካለፈዉ ሚያዚያ 7 ጀምሮ በገጠሙት ዉጊያ   በሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሰደዋል ወይም ተፈናቅለዋል።ተፋላሚ ኃይላት የመንግስት መስሪያ ቤቶችን፣ መደብሮችን፣ የርዳታ ቁሳቁሶችን፣ ይዘርፋሉ።

የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ተወካዮች ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ ባደረጉት ድርድር ለሰብአዊ ርዳታ ሲባል ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል።በዩናይትድ ስቴትስና በሳዑዲ አረቢያ ሸምጋይነት የሚደረገዉ ድርድር አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።

የድርድሩ መቀጠልም ሆነ ከዚሕ ቀደም ያደረጉት ተኩስ አቁም ለሱዳን ሕዝብ የጠቀመዉ ነገር የለም።የኤል ጀኒንያዋ የመብት ተሟጋች ኤናም ኑር እንደምትለዉ ተፈናቃዮች ካንዱ ሥፍራ ወደ ሌላዉ ሲጓዙ እንኳን በታጣቂዎች ይጠቃሉ።

«ታጣቂዎቹ ባሁኑ ወቅት አዲስ የጥቃት ስልት እየተከተሉ ነዉ።ሰፈሮችን ያጋያሉ።እኔ ራሴ ተፈናቃይ ነኝ።ከቤተሰቤ ጋር ደቡባዊ አዉራጃ ወደ ሰሜን ተሰድጄያለሁ።ወንድሜን ጨምሮ ብዙ ወንድ ወጣት ዘመዶቼ  በአስከፊ ሁኔታ ተገድለዋል።»

ሱቆቹ ተዘግተዉ ሸቀጡ ባደባባይ ይሸጣል ሱዳን
ሱቆቹ ተዘግተዉ ሸቀጡ ባደባባይ ይሸጣል ሱዳንምስል AFP/Getty Images

ተፋላሚ ኃይላት የተኩስ አቁሙን ስምምነት በየጊዜዉ እንደሚጥሱ ሁለቱን ወገኖች ከሚያደራድሩት አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ አስታዉቃለች።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲዉ ሚለር ባለፈዉ ሐሙስ እንዳሉት ተፋላሚዎች ቃላቸዉን ካላከበሩ መንግስታቸዉ ማዕቀብ ሊጥልባቸዉ ይችላል።

«ተኩስ አቁሙ እየተጣሰ መሆኑን እያየን ነዉ።በተኩስ አቁም ስምምነቱ ተቆጣጣሪ አማካይነት ከሁለቱም ወገኖች ጋር በተናጥል እየተነጋገርን ነዉ።በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣነዉ መግለጫ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እንዳሉት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነዉ ማዕቀብ የመጣል ሥልጣናችንን ለመጠቀም አናመነታም።»

Sudan Unruhe Konflikt
ምስል AFP via Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስና የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ትናንት እንዳሉት ግን ተኩስ አቁሙ በተሻለ ሁኔታ እየተከበረ ነዉ።ለሰብአዊነት ሲባል የተደረገዉ የተኩስ አቁም ዉል ለሰባት ቀን የሚፀና ነዉ።

የተፈጥሮ አደጋና ርዳታ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባለፈዉ ዕሮብ እንዳሉት አፍሪቃ ባንዱ ሰብአዊ ቀዉስ የሚጠፋዉ ሕይወትና ሐብት ተቆጥሮ ሳያበቃ ከሌላ ሰብአዊ ቀዉስ እየታላጋች ነዉ።ባለፈዉ ሐሙስ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበት 60ኛ ዓመት አዲስ አበባ ላይ ሲከበር ኒዮርክ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለረሐብ ለተጋለጡ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት ዜጎች ርዳታ ይማፀን ነበር።

የሶኮቶ-ሰሜን ናይጄሪያዉ ከብት አርቢ መሐመድ ሙሳ አዲስ አበባ፤ ብራስልስም ሆነ ኒዮርክ ላይ ስለሚቀመረዉ ቃል፣ ፖለቲካ ዲፕሎማሲ ወይም የተፈጥሮ ሐብት እንዲከበር በየከተማዉ ስለሚደረገዉ ስልፍ  የሚያዉቀዉ ነገር የለም።የተፈጥሮ-ክፋት ደግነትን ግን ጠንቅቆ ያዉቀዋል።ያደገበት ነዉና።

«ከብቶቼ ሞቱ።ምክንያቱም ዝናብ  የለም።ቢጥልም በቂ አይደለም።አትክልት የለም።በረሐዉ እየተስፋፋብን ነዉ።ሳር የለም።ዉኃም የለም።»

በጎቹ፣ፍየሎቹ፣ ዶሮዎቹ ተራበተራ አለቁበት።የተረፉትን ሽጦ ተሰደደ።

UN Generalsekretär Antonio Guterres / New York
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽምስል Fatih Aktas/AA/picture alliance

መሐመድና የሰሜን ናጄሪያ ብጤዎቹ ድርቅ ሲያሰድዳቸዉ ደቡብ ናጄሪያ በጎርፍ ይጥለቀለቅ ነበር።በተለይ ባለፈዉ ሕዳር  ደቡባዊ ናጄሪያን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።እንስሳዉን  የቆጠረዉ የለም።

አጥኚዎች እንደሚሉት ዘንድሮ ማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ አፍሪቃን ያጥለቀለዉ ጎርፍ መጠን በአካባቢዉ የምዕተ-ዓመት ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።ድርቅ፣ ጎርፍ፣አዉሎነፋስና መሰል የተፈጥሮ መቅስፍት የሚያደርሱትን ጉዳት የሚያጠናዉ GIFSEP በሚል ምሕፃረ ቃል የሚታወቀዉ ድርጅት እንደሚለዉ ተፈጥሮ በርግጥ ተለዉጣለች።«እኛም መለወጥ አለብን» ይላሉ የGIFSEP ባለሙያ ዴቪድ ማይክል ቴሩንግዋ።

«የአየር ንብረት እየተለወጠ ነዉ።እኛም መለወጥ አለብን።ቤቶቻችንን የምንገነባበት፣እርሻ የምናርስ፣ ከብት የምናረባበት መንገድ በሙሉ መለወጥ አለበት።መሬቱን በደን መሸፍን አለብን።በየሐገሩ የሚደርሰዉን ድርቅና ጎርፍን መከላከል አለብን።ምክንያቱም ሰዎችን ብቻ ሳይሆን የየሐገሩን የመሰረተ ልማት አዉታርንም ይጎዳሉ።»

የሚለወጠዉ የአየር ንብረትን ለመቋቋም ብዙዎች ብዙ ስልትና እርምጃዎችን ይጠቁማሉ።የእነ መሐመድ  ሙሳን ከብቶች ከእልቂት፣ እነሱን ከስደት ለማዳን ግን አንዱም-ብልሐት እርምጃ አልጠቀማቸዉም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ድርቅ፣የዉኃ ሙላትና ርዕደ ምድርን የመሳሰሉት የተፈጥሮ አደጋዎች በትንሽ ግምት 40 ሚሊዮን ሕዝብ ከየቤት ንብረቱ አፈናቅሏል።የአደጋዉን ከፍተኛነት የሚጠቁሙ ቀቢፀ ተስፈኞች እንደሚሉት ደግሞ ተፍጥሮ አደጋ ያፈናቀለና ሐብት ንብረቱን ያወደመበት የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከ200 ሚሊዮን አያንስም።

የሱዳን ተፈናቃዮች-ቻድ
የሱዳን ስደተኞች-ቻድምስል Blaise Dariustone/DW

ቁጥሩ 40ሚሊዮንም ሆነ 200 ሚሊዮን የአፍሪቃ ቀንድን ያክል የሰዉ ሕይወት ለአደጋ የተጋለጠበት አካባቢ አለመኖሩ ነዉ ዚቁ።ሶማሊያን፣ኢትዮጵያንና ኬንያን ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የመታዉ ድርቅ፣ በቅርቡ የደረሰዉ ጎርፍ ኢትዮጵያና ሶማሊያን ከሚያመሰቃቅለዉ ግጭትና ጦርነት ጋር ተዳምሮ ከ40 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ለረሐብ አጋልጧል።

በሶስቱ ሐገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች አልቀዋል።ሕፃናት እየሞቱ ነዉ።ግጭት፣ጦርነት፣ የተፈጥሮ መቅሰፍቱ አልበቃ ያለይመስል አለቅጥ ያሻቀበዉ የኑሮ ዉድነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለአደባባይ ላልበቃ ረሐብ አጋልጧል።ባለፈዉ ሚያዚያ ጀምሮ ሱዳን የሚያወድመዉ ጦርነት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት መከረኛዉን ሕዝብ ብዛትና የችግሩን ክፋት አንሮታል።

«በቀዉስ ላይ የሚደረበዉ ቀዉስ በሚሊዮን የሚቆጠር የአፍሪቃ ቀንድ ሕዝብን ሕይወትና የኑሮ መሰረት ለአደጋ እያጋለጠዉ ነዉ።ለዓመታት የዘለቀዉ ግጭት ሕዝቡን በጅምላ አፈናቅሎታል።የተንቻረረዉ የምግብ ዋጋና አሁን ደግሞ ሱዳንን የሚያተራምሰዉ ዉጊያ በአካባቢዉ በሙሉ አለመረጋጋት እያስከተለ ነዉ።»

ብዙዎች እንደሚሉት የዓለምን ሁለንተናዊ ሒደት የሚዘዉሩት ምዕራባዉያን መንግስታት ለአንዲት ዩክሬን ላንድ ሳምንት ጦር መሳሪያ መግዢያ የሚሰጡትን ገንዘብ ለአፍሪቃ ቀንድ ችግረኞች ቢሰጡ ሚሊዮኖችን ማጥገብ በተቻለ ነበር።የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳንና የሱዳንን የመሳሰሉ  የአፍሪቃ መሪዎች፣ፖለቲከኞችና የጦር አዛዦችም ለስልጣንና ትርፍ ሲሉ የገዛ ዜጎቻዉን ለጦርነት እየማገዱት ነዉ።

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመትን ለማክበር  አዲስ አበባ የተሰበሰቡት የአፍሪቃ መሪዎች፣ሚንስትሮችና ዲፕሎማቶች ከ20ና 30 ዓመታት በኋላ ምናልባት አብዛኞቹ በማይኖሩበት ዘመን ይደረጋል ስለሚሉት ዕቅድና ሐሳብ ሲደሰኩሩ ከአዲስ አበባ በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ረሐብ ስለሚፈደፍደዉ ሕዝብ ያሉት የለም።

ድርቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል
ድርቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልምስል Maria Gerth/DW

እንዲያዉም ዜጎቸዉን  በየግጭት፣ጦርነቱ እየማገዱ፣ አለያም በረሐብ እየቀጡ ለዉጪ ገበያ የሚተርፍ እሕል አመረትን እያሉ ከሚመፃደቁት የአፍሪቃ መሪዎች ይልቅ ኒዮርክ የተሰበሰቡት የቱጃሮቹ ሐገራት ተወካዮች የርዳታ እጃቸዉን ዘርግተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባዘጋጀዉ የአንድ ቀን የገንዘብ መዋጮ ስብሰባ የተካፈሉት መንግስታት ተወካዮች ለረሐብ ለተጋለጠዉ የአፍሪቃ ቀንድ ሕዝብ መርጃ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ለመርዳት ቃል ገብተዋል።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳይ ረዳት ዋና ፀሐፊ ጆይሲ ሙሱያ።

«ለመጋራት፣ ተሳታፊዎቹ በ2023 ኢትዮጵያ፣ኬንያና ሶማሊያ ዉስጥ ለሚያስፈልገዉ የሰብአዊ ርዳታ ባጠቃላይ 2.4 ቢልየን የአሜሪካን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።»

በጉባኤዉ ላይ ከተካፈሉት መንግስታት ከፍተኛዉን ገንዘብ የሰጠችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።524 ሚሊዮን ዶላር።ጀርመን 225 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ የሁለተኝነቱን ሥፍራ ይዛለች።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ