1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተናባቢ የባንክ ካርድ አገልግሎት

ረቡዕ፣ ግንቦት 17 2008

የኢትዮጵያ ባንኮች ዘግይተውም ቢሆን ደንበኞቻቸው ከየትኛውም የኤ.ቲ.ኤም ማሽን ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉበት አሰራር ተግባራዊ አድርገዋል። ባንኮቹ በጋራ ያቋቋሙት ኢት-ስዊች አክሲዮን ማህበር ኢትዮ-ፔይ አገልግሎትን ከጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል። ኢት-ስዊች በሂደት በስልክ እና ኢንተርኔት የሚፈጸሙ ክፍያዎችን ወጥ የማድረግ እቅድ አለው።

https://p.dw.com/p/1IuGO
Symbolbild Geldscheine und Kreditkarten
ምስል picture-alliance/ZB/J. Kalaene

ተናባቢ የባንክ ካርድ አገልግሎት

የኢትዮጵያ ባንኮች የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች (ATM)በስተመጨረሻ እርስ በርስ ተገናኙ።ማሽኖቹ እርስ በርስ በመገናኘታቸው አሁን የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ካርድ ባለቤት የሆኑ ደንበኞች ከማንኛውም ቦታ በማንኛውም ጊዜ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ማክሰኞ ሚያዝያ 12 ምሽት ኢትዮ-ፔይ የተሰኘው አዲስ ግልጋሎት የባንኮቹን የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች እርስ በርስ ካስተሳሰረ በኋላ በማግስቱ ሥራ ጀምሯል።

አገልግሎቱን ለማከናወን የኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት ኢቲ-ስዊች አክሲዮን ማህበርን አቋቁመዋል። አቶ ብዙነህ በቀለ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመረው የኢቲ-ስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 1,900የኤ.ቲ.ኤም እና 13,250የክፍያ መፈጸሚያ ማሽኖች አሉ። አቶ ብዙነህ በቀለ እነዚህን የኤ.ቲ.ኤም. እና ክፍያ መፈጸሚያ ማሽኖች እርስ በርስ ማገናኘት ለ19ኙ የኢትዮጵያ ባንኮች እና ደንበኞቻቸው ገንዘብ እና ጊዜ ይቆጥብላቸዋል ሲሉ ይናገራሉ።

Äthiopien Enat Bank
ምስል DW/Y. G. Egziabher

አሁን ደንበኞች በያዙት ካርድ ከማንኛውም የኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖች ገንዘብ ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ኢት-ስዊች ወደ ሥራ ያስገባው ኢትዮ-ፔይ ሥራው የኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖችን ማገናኘት ወይም እርስ በርስ ማናበብ ብቻ አይደለም። በሁሉም ማሽኖች ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚያስችል ካርድም ጭምር ነው።

ከዚህ ቀደም በነበሩት የክፍያ ስርዓቶች አንድ ደንበኛ አንድ ሺህ ብር ከኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ሲያወጣ ለአገልግሎቱ አንድ ብር ይከፍላል። አቶ ብዙነህ በኢትዮ-ፔይ ደንበኞች ከኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ ለአገልግሎቱ የሚፈጽሙት ክፍያ ከቀደመው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረውን ኢትዮ-ፔይ እምብዛም አላስተዋወቅነውም የሚሉት አቶ ብዙነህ በቀለ ከደንበኞች ግን በጎ ምላሽ አግኝተናል ብለዋል።

የምዕራባውያኑ ማስተር እና ቪዛን የመሰሉ ካርዶች በኢትዮጵያ ውስን የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ባንኮች ውስጥ ብቻ ያገለግላሉ። ካርዶቹ በአብዛኛው ተቀባይነት ያላቸው በትልልቅ ሆቴሎች እና የአገር ጎብኚዎች በሚያዘወትሩባቸው አካባቢዎች ብቻ ነው። ኢትዮ-ፔይ የማስተር እና ቪዛ አይነት ካርድ ባለቤቶች በኢትዮጵያ የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች መገልገል እንዲችሉ በር ይከፍታል።

Stadtansicht von Addis Abeba, Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ኢት-ስዊች በቀጣይ እቅዶቹ አሁን ከጀመረው የክፍያ ካርዶችን ተናባቢ የማድረግ ግልጋሎት ባሻገር የእጅ ስልክ እና የኢንተርኔት የክፍያ መንገዶችን እርስ በርስ የማስተሳሰር እቅድ ሰንቋል። የባንኮች የተበታተኑ ክፍያ መንገዶች ይዋሃዳሉ። ደንበኞች ለሸመቷቸው ሸቀጦች አሊያም ላገኟቸው አገልግሎቶች በኢንተርኔት አሊያም በእጅ ስልካቸው ወጥ በሆነ መንገድ ክፍያ መፈጸም ይችላሉ።

ኤ.ቲ.ኤምን የመሰሉ ዘመን አመጣሽ የክፍያ መንገዶች ኢትዮጵያ ውስጥ ዘግይተው ከመጀመራቸው ባሻገር የተጠቃሚዎችም ቁጥር ውስን ነው። ኢት-ስዊች አክሲዮን ማህበር እንኳ የክፍያ ካርዶችን ተናባቢ ለማድረግ የተመሰረተው ከአምስት አመት በፊት ነበር። የኢት-ስዊች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ ኢትዮ-ፔይን ግልጋሎት ላይ ለማዋል ረጅም ጊዜ የወሰደው አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ውስን በመሆናቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ