ተቃዋሚው የዓረና ትግራይ ፓርቲ በክልሉ ለሚታየው ሕገወጥነት የመንግስት ባለስልጣናትን ወቀሰ
ዓርብ፣ ግንቦት 23 2016በትግራይ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና ግድያ እንዲሁም ሕገወጥ የማዕድናት ማውጣት እና ዝውውር ተግባራት መንሰራፋታቸው በክልሉ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ አስታወቀ። በእነዚህ ወንጀሎች ላይም የመንግስት ባለስልጣናት ተሳትፎ አለ ሲል ዓረና ከሷል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ማብራርያ የሰጠው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ በተለይም በትግራይ በስፋት እየተፈፀሙ ናቸው ያላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ሕገወጥ የማዕድናት ማውጣት ዝውውር የመንግስት ባለስልጣናት እጅ ያለበት እና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲል ገልፆታል።
በትግራይ ክልል ዕርዳታ ከሚፈልገዉ ሕዝብ 1.5 ሚሊዮኑ ርዳታ አያገኝም-ኮሚሽን
ለዶቼቬለ የተናገሩት የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ በተለይም በወጣቶች ሴቶች ላይ የሚፈፀም እገታ፣ ግድያ እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች በትግራይ መንሰራፋታቸው የሚገልፁ ሲሆን መንግስት ሕገወጥ ተግባራቱ ለማስቆም የሚወስደው እርምጃም አለመኖሩ በማንሳት ወቅሰዋል።
በትግራይ ክልል ርእሰ ከተማ መቐለ ጨምሮ በዓድዋ፣ ዓዲጉደም እና ሌሎች አካባቢዎች እነዚህ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በተደጋጋሚ መታየታቸው ሊቀመንበሩ በአብነት አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ በስፋት እየታዩ ካሉ ወንጀሎች መካከል ሌላው ሕገወጥ የማዕድናት ማውጣት እና ዝውውር መሆኑ ዓረና ትግራይ ይገልፃል። በተለይም በትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ማእከላይ ዞኖች የመንግስት ባለስልጣናት እና የሰራዊት አመራሮች የሚሳተፉበት የተባለ ሕገወጥ የወርቅ፣ ኦፓል፣ ሳፋየር እና ሌሎች ማዕድን ምዝበራ መንሰራፉቱ የሚናገሩት የዓረናው ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ይህ የህዝብ እና ሀገር ሀብት ዝርፍያ እንዲቆም ስርዓት እንዲይዝ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የዓረና ክሶች ዙርያ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በትግራይ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት በስፋት እየታዩ መሆኑ ግን የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ይቀበላል።
በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ለክልሉ መንግስት መገናኛ ብዙሐን ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ፥ አስተዳደራቸው እርምጃዎች እንደሚወስድ ገልፀው ነበር።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሚሊዮን ሀይለስላሴ
ፀሐይ ጫኔ
እሽቴ በቀለ