1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የብዝኀ ሕይወት ይዞታና ተስፋው

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2016

በ1920ዎቹ ዓ,ም በተጀመረው የዘረመል ማእከሎችን የማደራጀት እሳቤ ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ ስምንት ማዕከሎች አንዷ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም በእህል ዓይነቶች ብዛትና አንዳንዶቹም በኢትዮጵያ ብቻ መገኘታቸው በብዝኀ ሕይወት ሀብት ከፍተኛው ስፍራ ላይ እንዳስቀመጣትም ይገልጻሉ። ሆኖም በምድራችን የብዝሀ ሕይወት ስብጥር መመናመኑ ይገለጻል።

https://p.dw.com/p/4eMda
ፎቶ ከማኅደር፤ ኬንያ
ብዝኀ ሕይወት የግጦሽ ሜዳ ላይ ያሉትን ጨምሮ የሚበሉም ሆኑ የማይበሉ የእጽዋትና የእንስሳት ዘሮችን ተለያይነት፣ እንዲሁም በዚህ ረገድ የኅብረተሰቡን እውቀት እና ስነምህዳሩን እንደሚያካትት የኢትዮጵያ የብዝኀ ሕይወት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ ይገልጻሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ ኬንያ ምስል Urs Schaffner

አሳሳቢው የብዝኀ ሕይወት ይዞታና ተስፋው

የእጽዋትና እንስሳት ዝርያዎች የመጥፋት ስጋት  

ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዓለም ከሚገኙ 150 ሺህ የእጽዋትና እንስሳት ዝርያዎች 30 በመቶው ያህሉ በሰዎች እንቅስቃሴ ለረሀብ በመጋለጥ፣ በጸረ ተባይ መድኃኒቶች በመመረዝ ወይም ለትርፍና ለስፓርት በሚል እየታደኑ የመጥፋት አደጋ ላይ ናቸው። እንደተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም እጅግ ብዙ ዕጽዋት እና እንስሳት በፍጥነት የሞቱበት ጊዜ ከ66 ሚሊየን ዓመታት በፊት አንድ ትልቅ ቋጥኝ ድንጋይ ፕላኔት መሬትን ሲመታ ነበር። የያኔው አደጋ ዳይኖሰርን ከምድረ ገጽ ያጠፋ፤ በጥቅሉም 75 በመቶ የሚሆኑ ዝርያዎችን ጠርጎ ያስወገደ ነውም ይላሉ። 

ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወት ሀብታቸው ከሚታወቁ ሃገራት ግንባር ቀደሟ ናት ይላሉ የኢትዮጵያ የብዝኀ ሕይወት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ። ዶክተር መለሰ፤ ከኬሚካል አጠቃቀም ጋር በተገናኘ የታዩ ለውጦት መኖራቸውን አስተውለዋል። በተመሳሳይ በውኃ አካላት ከፍሳሽ እና ኬሚካል ብክለት ጋር በተገናኘ በተለይ በአዲስ አበባ አካባቢ እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ችግሮችን መሠረት በማድረግ በአካባቢ ጥበቃ ተቋም አሳሳቢነት የእርምት ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።  

 

የኢትዮጵያ ይዞታ

ብዝኀ ሕይወት የግጦሽ ሜዳ ላይ ያሉትን ጨምሮ የሚበሉም ሆኑ የማይበሉ የእጽዋትና የእንስሳት ዘሮችን ተለያይነት፣ እንዲሁም በዚህ ረገድ የኅብረተሰቡን እውቀት እና ስነምህዳሩን እንደሚያካትት ያመለከቱት ባለሙያው፤ በተደረገው ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ እጽዋት ዝርያ ከስድስት ሺህ እንደሚበልጥ ገልጸውልናል። የእነዚህን ዘር በኢትዮጵያ የዘረመል ባንክ በአግባቡ መያዙን ያመለክታሉ። ባለሙያው እንደሚሉት የእርጥበት መጠናቸው ከአስር በመቶ በታች ሆነው በቀዝቃዛ ስፍራ ከሚቀመጡት ባሻገር በእርሻ ማሳ ውስጥ በጥንቃቄ እንዲጠበቁ የሚደረጉ ዝርያዎችም አሉ። እነዚህ ተጠብቀው ይገኛሉ ያሏቸውን አዝርእትና የእጽዋት ዘሮችን በተመለከተ የሚነሱ ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማመልከት የሚደረገውን አስረድተዋል።

እሳቸው እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች አሉ። ሾላ እና ቀጋን ጨምሮ የሚበሉ ተክል አይነቶች ደግሞ ወደ 400 የተለያዩ ዝርያዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል። ባጠቃላይም ነባር ሀገር በቀል እና በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ አይነቶችም ወደ 135 የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች መኖራቸውንም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

እንዲያም ሆኖ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ ባጋጠመው ድርቅ በደቡብ ምሥራቅ እና በሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ ከብቶች ማለቃቸው ያለው ብዛት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አመልክተዋል። እንዲህ ባለው ወቅት አርሶ አደሩ የእንስሳቱን ዘር ጠብቆ ለማቆየት ችግር ስለሚገጥመው በመፍትሄነት እንደ ግብርና ሚኒስቴር እና መሰል የሚመለከታቸው አካላት ዘሮችን ማቆየት የሚችሉበት መንገድ መኖሩን አስረድተዋል። እሳቸው የሚመሩት ተቋምም በመጥፋት አደጋ ላይ ላሉ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ለሚገኙ እና ኤኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን መርጦ የዘር ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ አልፎም በአንዳንድ አካባቢዎች ዘር እንዳይጠፋ ለአርብቶ አደሮች ኮርማዎችን ይሰጣል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ተቋም የተመሠረተበት ዋና ዓላማ ሀገር በቀል የሆኑ እጽዋት እና እንስሳት እንዲሁም በዐይን የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ ዘራቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተቋማቸው ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋርም አብሮ እንደሚሠራ ነው ያስረዱት። በዚህም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው እንደ ቀይ ቀበሮ ያሉት እንስሳት ዘራቸው እንዳይጠፋ የትብብር ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

የኖርዌይ የዓለም እህል እና ተክሎች ዘረመል ባንክ።
የኖርዌይ የዓለም እህል እና ተክሎች ዘረመል ባንክ። ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner

በሌሎች ሃገራት ጠብቆ በማቆየት ሙከራ የታዩ ችግሮች

በሌላ ሃገራት ተሞክሮ በተፈጥሮ ተጽዕኖና በተለያዩ መንስኤዎች የብዝሃ ሕይወትሀብቶች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት በተጨማሪ ጠብቆ ለማቆየት በሚል የሚደረጉ አንዳንድ ሙከራዎችም ጥፋት እያስከተሉ መሆኑ ነው የሚነገረው። ለምሳሌ እንስሳትን በማዳቀል ዝርያቸውን ለማቆየት በሚደረግ ሙከራ ከለመዱት የመኖሪያ አካባቢ ለተወሰኑ ቀናት እየተወሰዱ ጭራሽ ለችግር እየተጋለጡ መሆኑን ማዳጋስካር ውስጥ መታየቱን ለ25 ዓመታት በዘርፉ ምርምር የሚያደርጉት በሀገሪቱ በብዝሀ ሕይወት ጉዳይ የጓዳኝ የሆነው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ ኤድዋርድ ሉዊስ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

የዓለም ትልቁ የዘረመል ባንክና ኢትዮጵያ

በዓለም ደረጃ ግዙፉ የእጽዋትና እንስሳት ዘረመል ባንክ የሚገኘው ኖርዌይ ውስጥ ነው። በበረዶ ክምር ውስጥ በተዘጋጀ ማከማቻም ከበርካታ ሃገራት የተሰባሰቡ የዘር ዓይነቶች በዚያ ይገኛሉ። በዚህ ስፍራ ከኢትዮጵያ የተወሰደ የእጽዋት ዘር አለመኖሩን በማመልከት ለምን ስንል የጠየቅናቸው ዶክተር መለሰ፤ ቀደም ሲል ከነበረን ሀብት ተዘርፈናል ነው የሚሉት።

በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቫብሎቭ የተባለ ተመራማሪ ጥናት ካካሄደ በኋላ ኢትዮጵያን የብዝኀ ሕይወት ማዕከል መባሏን ከምርምሩ ታሪክ ያስታወሱት ዶክተር መለሰ፤ የተለያዩ በርካታ እጽዋትና ሰብሎች መገኛ እና ምንጭነቷን አጽንኦት ይሰጣሉ። ኖርዌይ ውስጥ በተዘጋጀው የዘረመል ባንክ የእህልና እጽዋት ዘሮች በሆነ ችግር እና አጋጣሚ እንዳይጠፉ በሚል መቀመጡ ነው የሚነገረው። ባለሙያው ኢትዮጵያም እንዲህ ላለው ስጋት አስቀድማ መጠባበቂያ ማዘጋጀቷንም ይናገራሉ። ዶክተር መለሰ እንደገለጹት ከአንዱ ሀገር ሌላው እየወሰደ ለመጠቀም የሚችላቸው በሌሎች ሃገራትም የሚገኙ የእህልና እጽዋት ዘረመል ዓይነቶችን ኢትዮጵያም በተጠቀሰው ስፍራ ልታስቀምጥ ትችላለች። ሆኖም ግን ለየት ያሉትንና ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙትን የምትሰጠው ምን ጥቅም አግኝታ ነው በሚል መቆየቱን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም የአሜሪካን የቢራ ገብስ ችግር ገጥሞት ከኢትዮጵያ በተወሰደ የገብስ ዘር መታከሙን፣ ሆኖም በለውጡ ሀገሪቱ ያገኘችው ነገር አለመኖሩንም አስታውሰዋል። በዘመነ ዲጂታል ቴክኒዎሎጂ የአንድን እህል የዘረመል መረጃ በኮምፕዩተር በማካተት ከዚያ ተነስቶ እህሉን ማብቀል ደረጃ መደረሱን ነው ባለሙያው የገለጹት። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት ሃገራት ከተፈጥሮ ሀብታቸው የሚገባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ ሊያደርግ እንደሚችልም አመልክተዋል። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር መለሰ ማርዮን እናመሰግናለን።

 ሸዋየ ለገሠ

እሸቴ በቀለ