1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ

ሐሙስ፣ ግንቦት 11 2014

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ለሁለት ቀናት ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው እንደነበርና አፈና እንደተፈፀመባቸው መናገራቸውን ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለ DW ተናገሩ። ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንደነበር እና አዲስ አበባ ላይ በያዟቸው ሰዎች በቡጢ መመታታቸውን እንደሰሙ ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን ኃይሌ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4BaCS
Äthiopien Addis Abeba |  Tefera Mamo
ምስል Solomon Muchie/DW

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ለሁለት ቀናት ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረው እንደነበርና አፈና እንደተፈፀመባቸው መናገራቸውን ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለ DW ተናገሩ። ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንደነበር እና አዲስ አበባ ላይ በያዟቸው ሰዎች በቡጢ መመታታቸውን አሁን በሚገኙበት ባህርዳር 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ለጠየቋቸው ቤተሰብ መናገራቸውን እንደሰሙ ባለቤታቸው ወይዘሮ መነን ኃይሌ ለ DW ተናግረዋል። ከጅምሩ በሕጋዊ አካሄድ እና በሕግ ትጠረጠራለህ በሚል ሊያዙ ሲገባ የእሥራት ሂደቱን ባልጠበቀ ሁናቴ በመያዛቸው አፈና እንደተፈፀመባቸው መናገራቸውን DW ከጠበቃቸው ሰምቷል።

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ከተያዙ ጀምሮ ቃል አለመስጠታቸውን ፣ የተጠረጠሩበት እንዳልተነገራቸውና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ጠበቃው አብራርተዋል።
የዋስትና መብት እንደጠየቁላቸውና የዋስትናቸው ጉዳይ ቀጠሮ ነገ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ. ም መሆኑንም ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ተናግረዋል።

"ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ አሥር ሰዓት ላይ ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች የመኪና መንገድ ዘግተው ከከበቧቸው በኋላ በርከት ብለው አስገድደው ተሽከርካሪ ውስጥ እንዳስገቧቸው ነግረውኛል ያሉት ጠበቃው
ተሽከርካሪ ውስጥ ግባ አልገባም በሚል ኃይል እንደተጠቀሙና መጠነኛ ቢሆንም የእጅ ነገር እንዳረፈባቸው" እንደነገራቸው ጠበቃው አብራርተዋል።

"ከተያዙበት እለት ጀምሮ ለሁለት ቀናት ምድር ቤት በጨለማ ውስጥ ብቻቸውን እንዳደሩ እና ይህም ትክክል እንዳልሆነ ፣ ቀጥሎ በተሽከርካሪ ወደ ቢሾፍቱ / ደብረዘይት ተወስደው ከዚያም በሄሊኮፕተር ወደ ባህርዳር መወሰዳቸውንና ለእሳቸው ተብሎ ሄሊኮፕተር ተመድቦ መወሰዳቸው የመንግሥትን ሀብት ማባከን መሆኑን እንደሚያምኑ እንደነገራቸው" ጠበቃቸው ገልፀዋል።
ጠበቃ ሸጋው አክለውም "ባህርዳር 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ማንኛውም እስረኛ በሚጠየቅበት ሁኔታ መብታቸውን እንዲገለገሉ ተደርገዋል።" ብለዋል
ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ወንጀል እንዳልፈፀሙ ለጠበቃቸው እንደነገራቸውና የመናገር ነፃነታቸውን ተጠቅመው ሚዲያ ላይ በዋለ ጉዳይ እንዲሁም ቅሬታ ያላቸው አካላት አስረውኝ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው እንደነገሯቸውም ጠበቃው ለDW ተናግረዋል።

ደንበኛቸው ከተያዙ ጀምሮ ቃል አለመስጠታቸውን፣ የተጠረጠሩበት እንዳልተነገራቸውና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ጠበቃው አብራርተዋል። እነዚህ ሕገ መንግስታዊ መብቶቻቸው በመጣሳቸው ቅሬታ እንዳላቸውም ገልፀውልኛል ብለዋል።

ግለሰቡ በማረሚያ ቤት ውስጥ በተረጋጋ ሁኔታ ይገኛሉ ተብሏል። እስከ ዛሬ አመሻሹ ድረስ የፍትሕ አካላት ቃል እንዳልተቀበሏቸው ተነግሮናል ያሉት ጠበቃው የዋስትና ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው እና የዋስትና ጉዳያቸው ቀጠሮ ነገ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ. ም መሆኑንና እንደሚታይም ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ አሉበት በተባለው 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ዛሬ ጠዋት የተገኘው የባህር ዳሩ ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን ፣ጣቢያው ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የፀጥታ ኃይላት እየተጠበቀ መሆኑን ተመልክቷል።  ለአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ እና ምክትል ሃላፊ  ስልክ ቢደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ግን ተጨማሪ መርረጃ ማግኘት አለመቻሉንም ዘግቧል ።

ሰለሞን ሙጬ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ