1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለሃብቶች እና የመሬት አሰጣጥ ችግር በአማራ ክልል  

ሰኞ፣ የካቲት 15 2013

በአማራ ክልል በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዘርፍ የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም ከመሬት አሰጣጥ ጋር ያለው ችግር አሁንም ፈተና እንደሆነ ባለሀብቶች ተናገሩ፡፡ በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ 17ሺህ ባለሀብቶች መካከል 3ሺህ 690 ብቻ ወደሥራ መግባታቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/3pi4y
Äthiopien | Diskussion zu Investment in Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዘርፍ የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም ከመሬት አሰጣጥ ጋር ያለው ችግር አሁንም ፈተና እንደሆነ ባለሀብቶች ተናገሩ፡፡ ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ 17ሺህ ባለሀብቶች መካከል 3ሺህ 690 ብቻ ወደሥራ መግባታቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፣ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ «ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ በማይገቡትና ባለሀብቱን በሚያንገላቱ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል» ሲል አስጠንቅቋል፡፡ በአማራ ክልል ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በተመለከተ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በባሕር ዳር ከተማ የጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ባለሀብቶች እንደሉት ቀደም ሲል ከነበረው አኳያ ሲታይ ለባለሀብቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍ በጥሩ የሚታይ ነው እንደሆነ በደብረ ማርቆስ ከተማ የግሬስ ብስኩት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ሚካኤል ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለሀብቱ እንደሚሉት በግራናይት ልማት ለመሰማራት ከ 8 ወራት በፊት የጠየቁት የመሬተረ ጥያቄ አሁንም ምላሽ አላገኘም፣ በመሬት አሰጣጥ በኩል ያለው ችግር አሁንም ፈተና እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ ግርማ የሺጥላ እንደሚሉት ክልሉ በርካታ የልማት እምቅ ሀብት ቢኖረውም ባለፉት ዓመታት ፈቃድ ከወሰዱ 17 ሺህ ያህል ባለሀብቶች መካከል ወደሥራ የገቡት 3ሺህ 690 ብቻ ያህሉ ናቸው፡፡ አልሚዎች በሙሉ አቅማቸው ወደሥራ መግባት ባለመቻላቸው የተፈለገውን ያህል የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ እንዳልቻሉም አብራርተዋል፡፡

በክልሉ ባለሀብቱን ለመሳብ ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውንና ውጤትም እየተገኘ ቢሆንም አሁንም ባለሀብቱን የሚያንገላቱና ኃላፊነታቸውን ባግባቡ የማይወጡ ኃላፊዎች መኖራቸውን ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልፀዋል፣ በእነዚህ ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል፡፡

በባለሀብቱ በኩል  «ያልተገባ» አካሄድ ይታያል ሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ባለሀብቶች ያን ማስወገድና በቀጥተኛው መንገድ መስተናገድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ኃላፊነታቸውን የማይወጡ የመንግሥት አመራሮች እንዳሉ ሁሉ ለልማት በወሰዱት መሬት ላይ ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩ የልማት እንቅፋት ባለሀብቶች መኖራቸውን የሚያምኑት የግሬስ ብስኩት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለሚካኤል በሁለቱም ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በተካሄዳው የውይይት መድረክ ላይ ባለሀብቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ