1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስሞታ

እሑድ፣ መጋቢት 8 2016

“ብሔራዊ መግባባት በገለልተኛ አካል ነው መመራት ያለበት፡፡ ሁሉም የውይይቱ ተካፋዮች የሚያምኑበት መሆን ይገባል” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ በኢትዮጵያ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የተቋቋመውን አገራዊ ኮሚሽን የገለልተኝነት እና አቃፊነት ሁኔታን ነቅፈዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4doms
Äthiopien Addis Abeba | Kommission für nationalen Dialog
ምስል Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ለመጋቢት 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ሁሉም በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ የምክክር መድረክ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሁንና  ከ10 የፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ አባል የሆኑበት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ኮከስ ጥሪውን እንደማይቀበለውና በውይይቱም እንደማይሳተፍ አስረድቷል፡፡

የኮከሱ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ከሆኑት አንዱ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ፓርቲያቸው በኮከሱ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በመሆን ከምክክሩ እራሱን ያገለለው በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ እምነት በማጣታቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “ብሔራዊ መግባባት በገለልተኛ አካል ነው መመራት ያለበት፡፡ ሁሉም የውይይቱ ተካፋዮች የሚያምኑበት መሆን ይገባል” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ በኢትዮጵያ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የተቋቋመውን አገራዊ ኮሚሽን የገለልተኝነት እና አቃፊነት ሁኔታን ነቅፈዋል፡፡ ፖለቲከኛው ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋሉትን የፖለቲካ ቀውሶች ለመፍታ ያደረገው ጥረትም የለም ሲሉ ተቋሙን ነቅፈውታል፡፡

Äthiopien Nationaler Dialog
ምስል Seyoum Getu/DW

የኮከስ አባላቱ ጥያቄ

የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ አካል ለመሆን እንቸገራለን ያለው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርክቶቹ ኮከስ እንዲስተካከል ብለን አቅርበናል ያለው ሃሳብ በኮሚሽኑ ውድቅ መደረጉን አንስቶ ወቅሷል፡፡ኮሚሽኑ ላነሳናቸው ጥያቄዎችና ላቀረብናቸው ማሳሰቢያዎች ትኩረት ሰጥቶ ተገቢና አሳማኝ ምላሽ ከመስጠትይልቅ የተነሳውን ጥያቄ በማድበስበስና መሸፋፈን ጥያቄኣችንን ለማዳፈንና በኮከስ አባላት መካከል መከፋፈል ለመፍጠር አስረዋል ሲል ከሷልም፡፡ ዶቼ ቬለ ስለተነሱት ጥያቄዎች ምንነት የጠየቃቸው ፕሮፌሰር መረራ፤ “ከአዋጁና አወቃቀሩ ጀምሮ ይስተካከል የሚል ጥያቄ ነው ያቀረብነው” ብለዋል፡፡ “ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ደግሞ የአንድ ፓርቲ (ገዢ ፓርቲ) አባላት ድምጽ የጠቀለለው ነው፡፡ በመሆኑም በተዘዋዋሪ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለአንድ ፓርቲ ይሆናል” የሚል ስጋታቸውንም አንስተው ሞግተዋል፡፡

ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን
ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽንምስል Seyoum Getu/DW

የኮሚሽኑ ምላሽ

ስለመሰል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኮሚሽኑ እራሳቸውን የማግለል ተግባር እና እልባቱ በዶይቼ ቬለ በቅርቡ ተጠይቀው የነበሩት አንድ የኮሚሽኑ አባል ኮሚሽናቸው በፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው የገፋቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የሉም ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ አባል አምባዬ ውጋቶ እንደሚሉት “ኮሚሽኑ የትኛውንም አመለካከት ያላቸውን አካላት ለማሳተፍ አውዱ ክፍት ነው”፡፡የትኛውም ሃሳብ አለኝ የሚል አካል አጀንዳውን ወደ ምክክር እንዲያመጣ መጠየቁንም ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር