1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፒያሳ እና አራት ኪሎ የመልሶ ማልማት ተነሽዎች አስተያየት

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አዲስ ከተገነባው የዐድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት ያሉ ቤቶች «የፒያሳ እና አራት ኪሎ አካባቢ መልሶ ማልማት» እቅድ ውስጥ የተካተቱ በመሆናቸው ነዋሪዎች በጥቂት ወራት ውስጥ ከሥፍራው እንደሚነሱ የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ አስታውቋል። ጉዳዩ የብዙ ሰው መነጋገሪያ መሆኑን ታዝበናል።

https://p.dw.com/p/4dEVX
አዲስ አበባ፤ ፒያሳ
አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ምስል Solomon Muche/DW

በፒያሳ እና አራት ኪሎ የመልሶ ማልማት ተነሽዎች

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ አዲስ ከተገነባው የዐድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት ያሉ ቤቶች "የፒያሳ እና አራት ኪሎ አካባቢ መልሶ ማልማት" እቅድ ውስጥ የተካተቱ በመሆናቸው ነዋሪዎች በጥቂት ወራት ውስጥ ከሥፍራው እንደሚነሱ የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ አስታውቋል። ዛሬ በአካባቢው ተዘዋውረን ባደረግነው ምልከታ ብዙ ሰው ይህንን ጉዳይ መነጋገሪያ ማድረጉን ታዝበናል። «ልማት ማንም የሚጠላ የለም» ያለ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ምትክ ቤት የማግኘት እና የነበረው ማኅበራዊ ትስስር የማጣት ሥጋት ሰውን እንዳሳሰበው ገልጾ የከተማ መሥተዳድሩ ሕዝቡን ያማከለ አማራጭ እንዲያዘጋጅ ጠይቋል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ከተማው ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ ልናገኝ እኛ ልቻልንም።

የአካባቢው ነዋሪ ምን ይላል ?

ዛሬ ረፋድ በስፍራው ተዟዙሬ ባደረግኹት ምልከታ ብዙ ሰው «ለልማት ተነስተን ወደ ልደታ ልንሄድ ነው»፣ እንዴት ባጭር ጊዜ ተነሱ ይባላል? የሚለውን መነጋገሩያ አድርጎት ይደመጣል። ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ሐገር ፍቅር ትያትር አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የገለፁ አንድ አዛውንት ሰሞኑን ተጋብዘው ባይገኙም በጉዳዩ ላይ ነዋሪዎች ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሁኔታውን ሲገልፁ «ተጠናቋል» ብለዋል። 

መስተዳድሩ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባከተማ መስተዳድር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናታለም መለስ ምላሽ እንዲሰጡ ደጋግመን ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቸልንም። ከንቲባ ጽ/ቤት ሰሞኑን ባወጣው አጭር መግለጫ የተነሺዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ፣ ስፍራው ምን እንደሚገነባበት ባይገልጽም «አካባቢው በመሀል ከተማ የሚገኝ ለኑሮ የማይመች በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር በጀመረው እንቅስቃሴ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው» ሲል አስታውቋል። በስፍራው ያነጋገርናቸው ሰው ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ከአካባቢው የሚነሱ ነዋሪዎች እንዴት እንደሚስተናገዱ እና በመልሶ ማልማቱ ጉዳይ ውይይት መደረጉን ከቀናት በፊት ያስታወቀው የከንቲባ ጽ/ቤት «ነዋሪዎች በመረጡት አኳኋን እንደሚስተናገዱ» በወቅቱ ሕዝቡን ያወያዩት የመስተዳድሩ የሥራ ኃላፊ መግለፃቸውን ተመልክቷል። ያነጋገርነው አንድ ወጣት እንደሚለው ግን ምትክ ቤት በማግኘት ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።

ፎቶ፤ ፒያሳ አካባቢ
ከፒያሳ በልማት ምክንያት የሚነሱትን ሰዎች ጉዳይ የሚከታትል ቡድን መዋቀሩ ተሰምቷል። ፎቶ፤ ፒያሳ አካባቢ ምስል Solomon Muche/DW

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ልደታ ቤተክርስታያን አካባቢ «ለልማት ተነሺዎች የሚተላለፍ ሁለት ባለ 9 ወለል የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ» ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመሆን ማስጀመራቸውን ገልፀው ቀድመው የተጀመሩ ቤቶች እዚያው ልደታ አካባቢ እና «ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ ለልማት ለሚነሱ ነዋሪዎች የሚሰጡ» መሆኑን ጠቅሰዋል። «ልማት ማንም ሰው አይጠላም» ያሉት አስተያየት ሰጪ «ሕዝብን ያማከለ» ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አካባቢው ምን ይዟል ?

ከፒያሳበልማት ምክንያት የሚነሱትን ሰዎች ጉዳይ የሚከታትል ቡድን መዋቀሩ ተሰምቷል። ከራስ መኮንን ድልድይ እስከ ሲኒማ አምፒየር ከዋናው መንገድ በላይ በኩል ወርቅ ቤቶች ፣ ምግብ ቤቶች፣ ልብስ ቤቶች፣ የሸቀጥ መደብሮች እና ሌሎችንም በብዛት ያቀፈው ይህ የፒያሳ እምብርት የሚባለው መንደር ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተናገድበት እና ታሪካዊ ተቋማት ጭምር የሚገኙበት ነው። አብዛኞቹ ቤቶችም ንብረትነታቸው የመንግሥት ሲሆን ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው ናቸው።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ