1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፍኖተ ሰላም በተከሰተ ፍንዳታ 34 ሰዎች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ገለጹ

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016

በፍኖተ ሰላም ከተማ ገበያ መሀል በተከሰተ ፍንዳታ 32 ሰዎች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። በቅዳሜው ፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸው አብዛኞቹ ለገበያ ከገጠር ወደ ፍኖተ ሰላም የተጓዙ እናቶች እንደሆኑ አቶ እድሜዓለም አንተነህ ገልጸዋል። ባለፈው ሐሙስ በትምህርት ቤት በተከሰተ ፍንዳታ 31 ተማሪዎች ተጎድተው ነበር።

https://p.dw.com/p/4eXqv
Äthiopien I Vertriebene in Finote Selam
ምስል A. Kibret/DW

በፍኖተ ሰላም በተከሰተ ፍንዳታ 34 ሰዎች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ገለጹ

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ በአንድ የገበያ አካባቢ በተጣለ ቦምብ በርካቶች መቁሰላቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እድሜዓለም አንተነህ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና አስተዳዳሪው በጥቃቱ 3 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

“...34 ሰዎች ናቸው አሁን ጤና ተቋማት ላይ ያሉት ከነኝህ ውስጥ 3 ከባድ የአካል ጉዳት ደረሰባቸው ናቸው፣ 8ቱ መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው 23 ሰዎች ታክመው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል” ብለዋል፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ስለ መርአዊ ግድያ

ፍንዳታው ቅዳሜ ከቀኑ 5፡30 አካባቢ መፈፀሙን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፣ ጥቃቱ የተፈፀመው ገበያተኞች እህል በሚገበያዩበት የከተማው ክፍል እንደሆነም ገልጠዋል፡፡

“ ፍንዳታው የተፈፀመው ቅዳሜ 5፡30 አካባቢ ነው፣ ፍዳታው ፍኖተ ሰላም ከተማ ዋናው ገበያ “እህል ገበያ” ተብሎ የሚጠራ አለ እዛ ላይ ነው፡፡ ቁጥራቸው ከ19 በላይ የሚሆኑት እናቶች ናቸው የገጠር ነዋሪ ደካሞች ናቸው ጉዳት የደረሰባቸው፣ የገጠሩ ገበሬ ነው እህል ሊሸጥ የመጣው ጉዳት የደረሰበት፡፡”

መጋቢት 26/2016 ዓ ም እንደዚሁ በፍኖተ ሰላም ከተማ ዳሞት ቁጥር 1 በተባለ ትምህርት ቤት ላይ በተጣለ ቦምብ 31 ተማሪዎች የቆሰሉ ሲሆን የ6ቱ ከባድ እንደሆነና በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እየተሰጣቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው ተባለ

“መጋቢት 26/2016 ዓ ም በፍኖተ ሰላም ከተማ ዳሞት መሰናዶ ቁጥር 1 ትምህርት ቤት ላይ ተማሪዎች ፈተና ላይ እንዳሉ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል፣ 31 ተማሪዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 6ቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፣ 15ቱ በመካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 10 ደግሞ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡”

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሀኪም በወቅቱ አንድ ተማሪ ወደ ከፍተኛ ህክምና ስትጓዝ ህይወቷ ማለፉን እንደሰሙ በወቅቱ ገልፀው ነበር፣ ዋና አስተዳዳሪው አቶ እድሜዓለም ግን በሁለቱም ጥቃቶች የጠፋ ህይወት እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

አጣዬ በ3 ቀናት ብርቱ ውጊያ ሕይወት ጠፍቷል

መጋቢት 26 በተፈፀመው ጥቃት በፅኑ የቆሰሉ ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ ህክምና ቦታ ለማድረስ በጉዞ ላይ የነበረ ተሸከርካሪ መንገድ ላይ ከነአሽከርካሪው ታፍኖ እስካሁን እንዳልተመለሰም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፣ በመኪናው ውስጥ የነበሩ የቆሰሉ ተማሪዎች መንገድ ላይ ተገኝተው በሌላ መኪና ወደ ህክምና ቦታ መድረሳቸውንም ገልጠውልናል፡፡

በሁለቱም ጥቃቶች ኃላፊነቱን በይፋ የወሰደ አካል እስካሁን የለም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ