በጥብቅ ጥበቃ ውስጥ ተከታታይ ጥቃት ፤ ፈረንሳይ ፤ እንዴታ ?
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2016ፈረንሳይ እና የደረሰባት አይረሴ የሽብር ጥቃት
የጎርጎርሳዉያኑ ሕዳር 2015 ለፈረንሳይ ብርቱ የሐዘን ወር ነበር ። ሆን ብለው በተቀናጁ ሁለት አስከፊ የቦምብ ጥቃቶች 130 ዜጎቿ በሞት ሲነጠቁ ከ350 የሚልቁቱ ደግሞ ቆስለዋል። ሕዳር 13 ቀን ምሽት ፈረንሳይ ከጀርመን የእግር ኳስ ግጥሚያ በሚያደርጉበት ምሽት አንድ አጥፍቶ ጠፊ በስቴዲየሙ የፍተሻ ስፍራ ላር ያፈነዳው ቦምብ እና በሌላ ከተማ የተፈጸመ ያልተገመተ ጥቃት በእርግጥ ለበርካቶች ህልፈት እን የአካል ጉዳት ቢዳርግም ፈረንሳይ እና መላው አውሮጳን ግን በከፍተኛ የሽብር ስጋት ውስጥ አስቀርቷቸው አልፏል።
አስር ዓመታት አልፈው ፈረንሳይ በሌላ ትልቅ አለማቀፍ የስፖርት ድግስ ላይ ሆና ሌላ የመጓጓዣ መሰረተ ልማት እና የሳይበር ጥቃት ተፈጽሞባታል። ጤና ይስጥልን አድማጮች በዛሬው የአውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን 33ኛውን የፓሪስ ኦሎምፒክ እያስተናገደች የምትገኘው ፈረንሳይ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ደረጃ ባደረሰችበት እንዴት ለዚያውም የተከታታይ ጥቃቶች ሰለባ ሆነች ስንል እንጠይቃለን ።
ፈረንሳይ ላይ በደረሰዉ ጥቃት ቢያንስ 84 ሰዎች ተገደሉ
ፈረንሳይ ለጥቃት አዲስ አይደለችም ።
ምናልባት የጥቃቱ አይነት ፣ የጥቃት አድራሹ ማንነት እና ዓላማው ይለያይ እንደሆን እንጂ ። የጎርጎርሳውያኑ 2015ቱ በፈረንሳይ የባህር ዳርቻዋ ከተማ ኒንስ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት ቦምብ ሳይፈነዳ ፣ ጥይት ሳይተኮስ 84 ሳዎች ከተገደሉ እና ሌሎች በርካቶች ከቆሰሉ በኋላ የሽብር ጥቃት አይነቶች እየበረከቱ መምጣታቸውን አሳይተዋል። የጥንቃቄ ደረጃቸውንም በዚያው ልክ ከፍ አድርገውታል።
ፈረንሳይን ጨምሮ ምዕራባውያኑ በመካከለኛው ምስራቅ በነበራቸው እና ባላቸው ፖለቲካዊ ሚና ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት የሽብር ማስፈራሪያ ሲደርሳቸው እና በተግባርም ሲፈጸምባቸው ዓለም በአይኑ ተመልክቷል። ይህንኑ ተከትሎ የስጋት ደረጃቸውን ከፍ ያደረጉት በተለይ አውሮጳውያኑ በህብረታቸው እና በተናጥል ሽብርተኝነትን ለመከላከል ያስችለናል ያሉትን ሁሉ ቅድሚያ ሰጥተው ሲሰሩ ቆይተዋል።
በመክፈቻ ዕለት እና ቆይቶ ምን ተፈጠረ?
33ኛውን የኦሎምፒክ ጫወታዎች በድምቀት ያስጀመረችው ፈረንሳይ ከወራት በፊት አስቀድማ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥበቃ ስታደርግበት የነበረው ሃገራዊ ደህንነት ተፈትኖ ወድቆባታል። በቀናት ልዩነት የተቀናጁ የሚመስሉ በመጓጓዣእና የኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አስተናግዳለች ።
የኦሎምፒክ ጫወታዎች የመክፈቻ ስነስረዓት ሊከናወን ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት በባቡር መሰረተ ልማት ላይ የተፈጸመ ጥቃት የሀገሪቱን የጀርባ አጥንት የሆነውን የመጓጓዣ መስመር አሽመድምዷል። ጥቃቱ ለወትሮም ከእረፍት በሚመለሱ ሰዎች ጉዞ የሚጨናነቀውን የፈርንሳይ አትላንቲክ ፤ ሰሜናዊ እና ምስራቃዊ የባቡር መስመሮች የጉዞ ሰዓት አዘግይቷል፤ አልያም እንዲሰረዙ አድርጓል ።
አሸናፊ ያልተለየበት የፈረንሳዩ የምክር ቤት ምርጫ እና አንድምታዉ
ብርቱ ጉዳት የደረሰበት የባቡር መስመሩ እስኪጠገን በርካታ የሰው ኃይል እና ረዘም ያለ ጊዜ መጠየቁ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እስከ 880 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከጉዞ እንደተስተጓጎሉ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በዘገባው አስነብቧል። እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ፈረንሳይ ባስተናገደችው ሌላ ጥቃት የቴሎኮም መስመሮች ዒላማ ተዳርገዋል። ከመዲናዋ ፓሪስ ውጭ የበርካታ ቴሌኮም ኩባንያዎች አገልግሎት መስጫ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቶቹን ማን ፈጸመ?
ለጥቃቶቹ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም። ነገር ግን የሀገሪቱ መንግስት ግራ ዘመም አክራሪ ብሄርተኞችን ተጠያቂ አድርገዋል። ዛሬ ቀትር ላይ ሮይተርስ ይዞት የወጣው አንድ ዘገባ ደግሞ ሩስያ ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን ከጥቃቱ ጋር ሊያይዙኝ እየጣሩ ነው ስትል ከሳለች። በጥቃቱ የሩስያ ዕጅ አለበት የሚለውንም ክስ ውድቅ አድርጋለች።
አቶ ናቲ ብሩክ የፓሪስ ከተማ ነዋሪ እና የዩሮ ስታር ባቡር ድርጅት ሰራተኛ ናቸው። ባለፈው ዓርብ የደረሰውን የባቡር መሰረተ ልማት ጥቃት በተመለከተ በሰጡን አስተያየት ጥቃቱ ከሽብር ጋር ባይገናኝም ብርቱ ጉዳት ያደረሰ ነበር።
«በ26 እና በ25 ሌሊት መካከል አሸባሪ ነው ልንለው አንችልም ፤ እስካሁን እንደዛ ብለው ስላልሰየሙት በአምስት የተለያዩ አካባቢዎች ከባድ የኤሌክትሪክ ገመድ የማቃጠል ገመዶቹን የመስረቅ እና የመበጣጠስ ድርጊት በጣም ከፍተኛ ጭንቀትም በህዝቡ ላይ ከፍተኛ መጉላላት ደርሶ ነበር የመክፈቻው ቀን ፤እንደሰማችሁት ከ800 ሺ በላይ መንገደኛ ተጉላልቷል። »
ጊዜው የበጋ ወቅት እንደመሆኑ መጠን በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ከውጭ በሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን የሚያስተናግደው የሀገሪቱ የባቡር መስመር በተቀናጀ መልኩ መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎች መኖራቸውን እና ዓለማቀፍ ትኩረት ለመሳብ የተፈጸመ መሆኑን አቶ ናቲ ይናገራሉ ።
በግራዎች ጥምረት አሸናፊነት የተደመደው የፈረንሳይ ምክር ቤታዊው ምርጫና የፈረንሳይ መጻኤ እድል
«የተቀናጀ መሆኑ በተመሳሳይ ሌሊት በተመሳሳይ ሰዓት ፈጣን ባቡሮች በሚሄዱበት ገመድ ላይ የዓለምን ህዝብ ትኩረት ሊስብ ይችላል በሚል ቦታዎች ላይ ነው ያደረጉት እና ምናልባት እስካሁን አሸባሪ የሚለው ስያሜ አልተሰጠውም ። ማን እንደሆነ ፍንጭ ተናግረዋል እንጂ የትኛው ቡድን የትኛው ፓርቲ ኢንታራጎስ ይባላል ፤ አክራሪዎች ይሆናሉ ተብሎ ነው የሚገመተው ።»
ከአራት ወራት ገደማ በፊት ሞስኮ ውስጥ በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ከ130 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ የሽብር ጥንቃቄ ደረጃዋን በከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ደረጃ ላይ ማድረሷን አስታውቃ ነበር። ማስጠንቀቂያው የፈረንሳይ የጸጥታ አካላት ህዝብ በሚሰበሰብባቸው እንደ ባቡር ጣቢያ እና አየርመንገድ በመሳሰሉ ቦታዎች በቀላሉ ቅኝት እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋል።
የሀገሪቱ መንግስት ምን አይነት ዝግጅት አድርጎ ነበር ?
የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚንስትር ገብርኤል አታል የፓሪስ ኦሎምፒክ ዝግጅት እየቀረበ መሄዱን ተከትሎ የሀገሪቱ የጸጥታ እና የደህንነት ሁኔታን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ከሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ዕይታ የሚሰወር አንዳችም ነገር እንደሌለ ተናግረው ነበር።
«በፈረንሳይ ውስጥ የአየር ክልልን ለመጠበቅ ቋሚ አቋም አለን። ነገር ግን በነዚህ የኦሎምፒክ እና የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተዘጋጅተናል። እዚህ እላለሁ ምንም ነገር የሚያመልጠን አይኖርም። ለዚህም ነው የመከታተያ ፣ እና የመጥለፊያ ስረዓቶቻችን እንዲሁም ከመሬት ወደ አየር መከላከያ ስረዓታችን በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ የፓሪስን ሰማይ ይቆጣጠራሉ። ይህ የጨዋታ ዝግጅቶቹን በሚያስተናግዱ ስፍራዎች ሁሉ ጭምር የሚሆን ነው ።»
የቀኝ ጽንፈኞች በፈረንሳይ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማሸነፍ አንድምታ
ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ በእርግጥ ከእይታቸው ተሰውሮ ምናልባትም አሳቻ ጊዜ እና ሁኔታን ተጠቅሞ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከተለ እንዲሁም የደህንነት ዋስትና ላይ ጥያቄ ያስነሳ ጥቃት በጥቂት ቀናት ልዩነት ነበር ያስተናገደው ። ክስተቱ ሰብአዊ ጉዳት አያስከትል እንጂ በፈረንሳያውያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ከማሳደር አልፎ መላ አውሮጳ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ሳያስገድዳቸው አልቀረም ።
የፓሪስ ከተማ ነዋሪው አቶ መስፍን እንዳሉት በመዲናዋ ፓሪስ ብቻ እንኳ የደህንነት ጥበቃው የሌሎች ሃገራትን እገዛ አክሎ እጅጉን መጠናከሩ ለነዋሪው አሰልቺ ሆኖበታል።
«ፓሪስ ላይ አሁን ብታይ ወደ 48 ሺ ፖሊስ ነው ያለው ። ከዓለም ላይ የመጡ አሉ ከየሃገሩ ፤ አሁን ለምሳሌ ከስራዬ አንጻር ከቃጣር የመጡ ፣ ከሃንጋሪ የመጡ ፣ ከስፔን የመጡ ፖሊሶች አይቻለሁ ከፈረንሳይ ፖሊሶች ጋር አብረው የሚሰሩ በትብብር ፤ ለራሷ ብቻዋን አልወጣውም ብላ ከሌሎች ሃገራት መጥተው የሚያግዙ ፖሊሶች አሉ። በእርግጥ በሄድክበት ቦታ ሁሉ የደህንነቱን ሁኔታ ስታይ ያሰለቻል።»
በፈረንሳይ ቀኝ ጽንፈኛው ፓርቲ የመጀመርያ ዙር የፓርላማ ምርጫን አሸነፈ
በቀጣይ ቀናትስ ምን ይፈጠር ይሆን?
ሊጠናቀቅ ከዚህ በኋላ ሁለት ሳምንት ገደማ የሚቀረው የፓሪስ ኦሎምፒክ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በእርግጥ ማንም አፉን ሞልቶ መናገር አይችልም። በዚህ ላይ ጥቃቱ ሀገር ውስጥ ባሉ አክራሪዎች መፈጸሙ መጠርጠሩ ደግሞ ነገሩን የበለጠ ሳያወሳስበው አልቀረም ። ለዚህም ነው አቶ መስፍን ቀጥሎ የሚመጣውን ጊዜ በስጋት መመልከትን የሚመርጡት ።
«እንደኔ እንደኔ አስተያየት ነው የምልህ ተስፋ ማድረግም አልችልም ተስፋ መቁረጥም አልፈልግም። አይፈጠርም ማለት አልችልም። ይፈጠራል ብዬም ማረጋገጥ አልችልም። ነገር ግን ደግሞ ስጋት አለ። »
ፈረንሳይ በቀናት ልዩነት የገጠማትን ጥቃት በከፍተኛ ርብርብ ዳግም ስራ አስጀምራለች። እንደዚያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ግዙፉ እና ውስብስቡ የባቡር መሰረተ ልማትን ጨምሮ ሌሎች አውታሮች ከተመሳሳይ ጥቃት እንዴት መታደግ ያስችላታል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም ። ይህ ብቻም የዓለማቀፍ አሸባሪዎች ብርቱ ስጋት ያለባት ሀገር የሀገር ቤቱ ጽንፈኛ የከፈተው መንገድ «ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል » እንዳይሆንስ ምን ዋስትና ይኖረው ይሆን ?
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ