1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዶዶላ የ14 ሰዎች ቀብር መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 15 2012

በዶዶላ ከረቡዕ ጀምሮ በተቀሰቀሰ ኹከት ሕይወታቸውን ያጡ የአስራ አራት ሰዎች ቀብር መፈጸሙን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። እማኞች እንደሚሉት የመኖሪያ ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው በርካታ ሰዎች በቤተ-ክርስቲያኖች ተጠልለዋል። በባሌ ሮቤ ትናንትና ዛሬ ብቻ ዘጠኝ ሰዎች መቀበራቸውን የሁለት ሰዎች አስከሬኖች ወደ ሌላ ቦታ መላኩን ዕማኞች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/3Rzpv
Karte Dodola Ethipia AM

በምዕራብ አርሲ ዞን በምትገኘው ዶዶላ ከተማ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በተቀሰቀሰ ኹከት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ የአስራ አራት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግሩ። በኹከቱ ምክንያት ቆስለው በአብያተ-ክርስቲያን የተጠለሉ ነዋሪዎች ወደ ሕክምና ማዕከል ለመጓዝ ሥጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።

በዶዶላ ባለፈው ረቡዕ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ቴሌቭዥን ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ከሆነው ጀዋር መሐመድ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱን የሚናገሩ የዓይን እማኝ ከዚያ በኋላ በከተማዋ ኹከት መቀስቀሱን ገልጸዋል። በኹከቱ ነዋሪዎች መደብደባቸውን እና የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም ኪዳነ ምኅረት በተባለ ቤተ-ክርስቲያን ብቻ ወደ 918 ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በኹከቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ሥርዓተ-ቀብርም በዚሁ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፅሟል ብለዋል ።

«እኔ ኪዳነ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን እና ቀጠና አራት፣ ቀጠና አምስት ቀጠና ሰባት ላይ ያለውን ነው የምነግርህ» ያሉት የዶዶላ የዐይን እማኝ «እዚህ ሰፈር የሞቱ ሰዎች ስድስት ናቸው። ዛሬ ደግሞ አንዷ ሞታ ገብረ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን ተቀብራለች» ሲሉ አስረድተዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የዓይን እማኝም ዛሬም ጭምር የቀብር ስነ-ሥርዓት መካሄዱን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ገብረ ክርስቶስ በተባለ ቤተ-ክርስቲያን ብቻ ስምንት ሰዎች መቀበራቸውን የሚናገሩት የዐይን እማኙ በከተማዋ ዛሬም ጥቃት መቀጠሉን ገልጸዋል። ሁለተኛው የዶዶላ ነዋሪ ገብረ ክርስቶስ በተባለ ቤተ-ክርስቲያን «በአጠቃላይ የቀበርንው ስምንት ሰው ነው» ብለዋል። የአይን እማኙ እንደሚሉት አሁን በቤተ-ክርስቲያን የተጠለሉ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለመመለስ አይችሉም።

«ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ቤታቸው ተቃጥሏል፤ ሁለተኛ ደግሞ ፉከራም አለ። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ምን ዋስትና አላቸው እና ወደ ቤታቸው ይመለሱ? በቤታቸውም የሚላስ የሚቀመስ ነገርም የላቸውም። የጸጥታ ክፍል እኛ አይኑን አይተንም አናውቅም። ይኸ ሁሉ ሕዝብ እንዲህ ሲሆን የህዝብ መሪዎች ነን ብለው ምንድነው ችግራችሁ? በምንድነው እንደዚህ የሆነው ጉዳዩ ያሉት አንድም ነገር የለም። ሶስት እና አራት መከላከያዎች ብቻ ደጃፉን ጠብቁ ተብለን ነው ያለንው ብለው እነሱ ብቻ ናቸው ሕይወታችንን እያዳኑት ያሉት»

የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ከማል እና የኦሮሚያ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረግንው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ ጀዋር መሐመድ በትናንትናው ዕለት በፌስቡክ እና በትዊተር ገፆቹ የዶዶላ ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ አስተላልፏል። ጃዋር « የዶዶላ ሕዝብ ተረጋግታችሁ ወደ ቤት ተመለሱ። በሐሰት ወሬ ሊያጫርሷችሁ እየሞከሩ ነው። እየተሰራጨ ያለው ወሬ ሐሰት መሆኑን አረጋግጠናል» ብሏል።

እንደ ዶዶላ ሁሉ በተቃውሞ እና በግጭት ስትናጥ በቆየችው የባሌ ሮቤ ከተማም በባለፉት ቀናት ኹከት ከቆሰሉ ሰዎች ሁለቱ ሕይወታቸው ማለፉን አንድ በከተማይቱ ያሉ የዐይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

«ትናንትና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሶስት ሰው ቀበረ። የሁለት ሰው አስከሬን ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ተልኳል። የሙስሊሞች ደግሞ ትናንትና ወደ ቀብር ሲሔድ አራት አስከሬን አይተናል። ዛሬም ደግሞ ሆስፒታል ሲታከሙ የነበሩ ሁለት ሰው ሞቷል ብለው እያወሩ ነበረ። ቀብር ሔደዋል፤ ሲቀብሩ አይተናል። እንደገና ደግሞ ከሁለቱም ወገን በጣም ተጎድተው በሆስፒታል ያሉ አሉ» ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥያቄ ከተሰማራባቸው አካባቢዎች መካከል የባሌ ሮቤ ከተማ ይገኝበታል። ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ «በአምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ሐረር ፣ ድሬዳዋ፣ ባሌ ሮቤ፣ ሞጆ እና በአዳማ አካባቢዎች» ሰራዊቱ መሰማራቱን ተናግረው ነበር።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ