1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ማን ያሰጋው ይሆን?

ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2016

ገዥው ፓርቲ ኤኤንሲ በግንቦቱ ምርጫ አብላጫውን ድምፅ እንደሚያጣ ከወዲሁ ተገምቷል ። ለብዙ መራጮች፣ ምርጫው በደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሲ ተስፋውን ለመመለስ ሌላ አማራጭ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ። ገዥው ፓርቲ ኤኤንሲ በግንቦቱ ምርጫ አብላጫውን ድምፅ እንደሚያጣ ከወዲሁ ተገምቷል ።

https://p.dw.com/p/4g07m
ደቡብ አፍሪካቃያን ግንቦት 21 አጠቃላይ ምርጫ ያከናውናሉ
ደቡብ አፍሪካቃያን ግንቦት 21 አጠቃላይ ምርጫ ያከናውናሉምስል Themba Hadebe/AP Photo/picture alliance

በደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሴ የተጋረጠበት ፈተና

ገዥው ፓርቲ ኤኤንሲ በግንቦቱ ምርጫ አብላጫውን ድምፅ እንደሚያጣ ከወዲሁ ተገምቷል ። ለብዙ መራጮች፣ ምርጫው በደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሲ ተስፋውን ለመመለስ ሌላ አማራጭ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

ደቡብ አፍሪቃ  አጠቃላይ ምርጫ ለማድረግ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀራታል ። ግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ የምታደርገው ደቡብ አፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ጋ ከተዋወቀች  30 ዓመታት ተቆጥሯል ። ምርጫው ላይ የተጋረጠው ተግዳሮትም ከወዲሁ ብርቱ መሆኑ ዕየታየ ነው።

በርካታ ምርጫዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፦ ገዢው የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ፓርቲ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፖዛ ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ አብላጫ ፓርቲነታቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ ። ያም ሆኖ ግን ፓርቲው ጠባብም ቢሆን አብላጫ ድምጽ ሊያገኝ ይችላል ። ይህን ያሉት በደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም የአፍሪቃ መንግሥታዊ አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ዓለም አቀፍ ተቋም ኃላፊው ስቴቨን ግሩዝድ ናቸው ።

«እኔ በግሌ የሚሰማኝ ኤን ፓርቲ ምንም እንኳን በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነቱ ቢቀንስም የሚያገኘው ድምፅ 50 በመቶ በትንሹ ከፍ እንደሚል ነው ። » እንደ ስቴቨን ግሩዝድ ከሆነ፦ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ ባለፉት ዓመታት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜያት ለነበረው ደካማ እንቅስቃሴ በምርጫ ሊቀጣ ይችላል ።

ዴሞክራሴ የተጋረጠበት ፈተና

የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ተንታኙዋ ቴሳ ዱምስ ግን ምርጫው የሚያሰጋው ኤኤን ሲን ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የምርጫ ሥርዓቱንም ነው ባይ ናቸው ። «ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በዚህ ዓመት ምርጫው የደቀነው ሥጋት  ከፍተኛ ነው   እጅግ በርካታ ሰዎች በዚህ ወቅት ዴሞክራሲ በሚለው ጽንሠ-ሐሳብ ራሱ ግራ ስለተጋቡ ሥጋቱ ከፍ ያለ ነው ።» እንደ ቴሳ ዱም ትንታኔ፦ ምርጫዎች ሕዝቡ የሚፈልገውን ባለማስገኘታቸው ዴሞክራሲ በማኅበረሰብ ግንባታ ላይ ስለሚጫወተው ሚና በርካቶች ተስፋ ቆርጠዋል ።

«እናም ሰዎች ራሳቸውን ከምርጫ ሥርዓት እያገለሉ ነው ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም በብዙኃኑ ዘንድ እየተተዉ ነው ።» ቴሳ ዱም ምርጫ የዴሞክራሲ አካል ከመሆን ባሻገር ያመጣው ለውጥ የለም የሚል ስሜት በበርካቶች ዘንድ መስረጹን አክለዋል ። 

የኤኮኖሚ ነጻነት ታጋዮች (EFF) ፓርቲ መሪ አንደበተ ርትኡው ፖለቲከኛ ጁሊዬስ ማሌማ
የኤኮኖሚ ነጻነት ታጋዮች (EFF) ፓርቲ መሪ አንደበተ ርትኡው ፖለቲከኛ ጁሊዬስ ማሌማምስል Reuters

መራጮች ቃል የተገባለቸው አልተጠበቀም

በደቡብ አፍሪቃ መራጮች በከፍተኛ ደረጃ የመከፋት ስሜት እንዳደረባቸው ቴሳ ዱም ይናገራሉ ። እናም በርካቶች ምናልባትም በግንቦት መጨረሻው ምርጫ ያጡትን እምነት መልሰው ያገኙ እንደሆነም ተስፋ ሰንቀዋል።  «እናስ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ በእርግጥም ለውጥ እና ውጤት ማስገኘት ችሎ መራጮች ያጡትን እምነት መልሰው ያገኙ ይሆን? » ይጠይቃሉ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ተንታኙዋ ቴሳ ዱምስ ።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዴምክራሲያዊ ሥርዓቱ የተፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑ በዜጎች የኑሮ ሁኔታ ላይ ተጽእኖውን አሳርፏል ።  ምንም እንኳን ደብብ አፍሪቃ የአኅጉሪቱ የአፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ቀንዲል ብትሆንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ግን በማኅበረ ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ጥልቅ አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀዋል ። ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፖሳ ባለፈው የካቲት ወር ለመላ ሀገሪቱ ነዋሪዎች ንግግር ባሰሙበት ወቅት፦ የደቡብ አፍሪቃ ድህነት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1993 ከነበረበት 71 በመቶ በ2020 ወደ 55 ከመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጠዋል ። 1993 በደቡብ አፍሪቃ የነች የበላይነት የአፓርታይድ ሥርዓት በይፋ ያከተመበት ወቅት ነው ። የዓለም ባንክ የ2008 መረጃ እንደሚያመለክተው የድሕነት መጠኑ በደቡብ አፍሪቃ  ከ62 እስከ 63 በመቶ እንደነበር ያሳያል ።

የወጣቶች ሥራ አጥነት

መሻሻል የሚገባው የወጣቶች ሥራ አጥነት ኹኔታም በምርጫው ወቅት አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ። በደብ አፍሪቃ የሥራ አጥነቱ መጠን ባለፈው ዓመት 32.4%  እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ ።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የወጣቶች ሥራ አጥነት አሳሳቢ ነው
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የወጣቶች ሥራ አጥነት አሳሳቢ ነውምስል Thomas Koehler/picture alliance/photothek

ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እሥራኤልን በጋዛ ሠርጥ ድብደባ  መክሰሷም በምርጫው ላይ የራሱ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተንታኞች ይናገራሉ ።  ስቴቨን ግሩዝድ እንደሚሉት ከሆነ የደቡብ አፍሪቃ ይህ እንቅስቃሴ በሀገሯ ምእራባዊ ኬፕ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞችን ድምፅ ለማግኘት በሚል ነው ።

«ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትላይ ያላት ጠንካራ የፍትሕ አቋም እና እሥራኤልን በዘር ፍጅት መክሰሷ በምእራብ ኬፕ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የሙስሊሞችን ድምፅ በምርጫ ለማግኘት ያለመ መሟሟት ነው ሲሉ አንዳንዶች ይናገራሉ »

የጄኮብ ዙማ ከANC ፓርቲ መልቀቅ ያስከተለው ጣጣ

የቀድሞው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ከአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ፓርቲ ለቅቀው ሌላ ፓርቲ በማቋቋማቸው ኤኤንሲ በዘንድሮ ምርጫ የማሸነፍ ዕድሉ አሽቆልቁሏል ሲሉ ቴሳ ዱምስ ይሞግታሉ ። ስቴቨን ግሩዝድ በተቃራኒው የጄኮብ ዙማ ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ኤኤንሲን በምርጫው ከማሸነፍ አያግደውም ብለዋል ። ይልቁንም ከባዱ ጉዳይ ጥምር መንግሥት ለማቋቋም መቸገሩ ይሆናል ብለዋል። 

ፕሬዚደንት ሲረል ራማፎሳ እና የኤኤንሲ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ይገጥማቸዋል
ፕሬዚደንት ሲረል ራማፎሳ እና የኤኤንሲ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል ይገጥማቸዋልምስል Denis Farrell/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

ኤኤንሲ በምርጫው አሸንፎ መንግስት መመሥረት ካልቻለ፥ ምናልባትም በአንደበተ ርትኡው ፖለቲከኛ  ጁሊዬስ ማሌማ ከሚመራው የየኤኮኖሚ ነጻነት ታጋዮች (EFF) ፓርቲ ጋ ጥምረት ሊኖር እንደሚችል ብዙዎች ከወዲሁ ይገምታሉ ።  የሁለቱ ጥምረት ግን ኤኤንሲን ጭራሽ ወደ ግራ ዘመም ወስዶት ይበልጥ ወግ አጥባቂ ሊያደርገውም ይችላል ። ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ግን ደቡብ አፍሪቃውያን መራጮች ለመላ ሀገሪቱ የሚተርፍ የኤኮኖሚ እድገት እና ደኅንነትን አጥብቀው ይሻሉ ። ደቡብ አፍሪቃውያን በስተመጨረሻ ምን እንደወሰኑ በአጠቃላይ ምርጫው ግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም መመልከት ነው ።

ኢሣቅ ካሌዲች/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ