በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እየከፋ የመጣው የንፁሃን ግድያ
ዓርብ፣ ነሐሴ 17 2016
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በመንግስት ጦር መካከል በሚከናወን የተኩስ ልውውጥና ግጭቶች ሰላማዊ ዜጎች አስከፊ ተባለውን ዋጋ እየከፈሉ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
አስተያየታቸውን ከአከባቢው የሰጡን ነዋሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው በተለይም በቀርሳ ማሊማ፣ ሰደን ሶዶ፣ ቶሌ እና አመያ ወረዳዎች ከነሃሴ ወር መጀመሪያ ወዲህ ብቻ በትንሽ ግምት 17 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠጠራው ታጣቂ ቡድን ከመንግስት ሰራዊት ጋር በሚፈጥሩት ግጭት አለመረጋጋቱ ወደ አስከፊ ደረጃ ከተሸጋገረባቸው የክልሉ አከባቢዎች ይጠቀሳል፡፡ ለዓመታት በታጣቂ ቡድኑና በመንግስት መካከል እየተካሄደ ያለው ይህ ግጭት ማህበረሰቡን በታሪክ አይቶ ለማያውቀው መከራና ሰቆቃ እየዳረገውም ይገኛል ይላሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች፡፡ “ከአንድ ሁለት ሶስት ወራት በፊት በዞኑ አንጻራዊ መረጋጋት ታይቶ ነበር፡፡ ከአንድ ወር ወዲህ ደግሞ ግጭቶች እንደገና ተቀስቅሶ ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በብዛት የሚሙቱ በጦርነቱ ውስጥ እጃቸው የሌለው ንጹሃን ናቸው” ብለዋል፡፡
የከፋው የእገታ እና ዝርፊያ መደጋገም
በዚህ ግጭት ውስጥ፤ የአርሶ አደሮች ቤቶችን የማቃጠል፣ ከብቶችን የመዝረፍ፣ እገታ እና ማህበረሰቡ ስራውን ባግባቡ እንዳይሰራ የሚያደርጉ አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ ተግባራት እየተከናወኑም ነው ተብሏል፡፡ በተለይም ከሁለት ዓመታት ወዲህ የከፋው ይህ ግጭት ህብረተሰቡን ከምርታማነት ውጪ አድርጎ ለችጋር ዳርጎታል፡፡ “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስጋት በመኖሩ ምርትም እየተመረተ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ታጥቀው መንግስትን የሚወጉ ታጣቂዎችም ሆኑ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በዚሁ ህዝብ ስለሆነ የሚቀለበው፤ አሁን አሁን የሚላስ የሚቀመስ ያጣው ህዝብ መሄጃ ጠፍቶታልም” ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፡፡
በታጣቂዎቹ ስም የምንቀሳቀሱ ያሏቸው ኃይሎች ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያ እና የተለያዩ አፈናዎችም ይፈጸማሉ ሲል ማህበረሰቡ ያማርራል፡፡ መሰል ከማህበረሰቡ እሴት ያፈነገጠውን ተግባር የሚፈጽሙ የሰራዊቱ አባላት እንዳልሆኑ የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ስገልጹ ግን ይሰማል፡፡ መሰል ተግባራት በገለልተኛ አካል ይመርመር ሲልም ይደመጣል፡፡
ሰሞነኛው ግድያ የከፋባቸው ወረዳዎች
በዞኑ በሁሉምወረዳዎች መሰል የጸጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለይም በሰደን ሶዶ፣ ሶዶ ዳጪ፣ ቀርሳ እና ቶሌ ወረዳዎች ችግሩ አስከፊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የትራንስፖርት አገልገሎትም ጭምር በተለያዩ ወረዳዎች በጸጥታው ስጋት በመስተጓጎሉ ህብረተሰቡ ወደ ገቢያ ወጥቶ
መገበያየት ተስኖታል ነው የተባለው፡፡ ነሃሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት በቀርሳ ማሊማ ወረዳ ተኩ ለሜሳ የተባሉ የ80 ዓመት አዛውንት ሳይቀር ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር በጭካኔ በጥይት ተደብድበው ስለ መገደላቸው ተመላክቷል፡፡ ሃዘን የተቀመጠው ልጃቸውም ከቀናት በኋላ በጭካኔ መገደሉ ነው የተገለጸው፡፡ “በማህበራዊ ሚዲያም እንደ ሚታየው የ80 ዓመት አዛውንቱ ከሶስት ሰዎች ጋር ተገድለዋል፡፡ በዚህ በቀርሳ ማሊማ ብቻይ አይደለም በሰደን ሶዶም ሰዎች ተገድለዋል” ነው የተባለው፡፡
በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ብቻ ማለትም በቀርሳ ማሊማ፣ ሰደን ሶዶ እና ቶሌ ወረዳዎች ከነሃሴ 3 እስከ 11 ብቻ ስም ዝርዝራቸው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው 17 ንጹሃን ሰዎች በታጠቁ አካላት በሌሊት ስለመገደላቸው ተብራርቷል፡፡
የጸጥታ ሁኔታው የተወሳሰበባቸው የዞኑ አከባቢዎች
ከነዚህ ወረዳዎች በተጨማሪ ከምእራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ጋር የሚዋሰነው የዚሁ ዞን አመያ ወረዳም ሌላው በፀጥታ ቀውሱ የሚፈተን ወረዳ ስለመሆኑ ተነገግሯል፡፡ ከዚሁ አከባቢ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ ነዋሪም፤ “በዚህ አከባቢ በየእለቱየሰው ህይወት ያልፋል፡፡ አንድ ሁለትም አይደለም፤ እየተጠባበቁ አንዱ ሌላውን ይገድላል፡፡ ብርግጥ የመንግስት ሰራዊት በአከባቢው እየተንቀሳቀሰ ጸጥታውን ለማስከበር ስጥር ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ቦታ ሊደርስ እንደማይችል ትገነዘባለህ፡፡ አሁን በቅርቡ እንኳ ሶስት እረኞች አንድ ላይ ዘግናኝ በሚባል መንገድ ተገድለዋል፡፡ 12 ሰዎችም አንድ ላይ የተገደሉት በቅርቡ ነው፡፡ በዚህ አከባቢ መጀመሪያ የጎሳ የሚመስል ግጭት አሁን ላይ ሸነ የሚባለውም ጽንፈኞች የሚባሉትም በስፋት ማህበረሰቡን እየጎዱ ነው” ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ አንዱ ወገን ሌላውን ትደግፋለህ በሚልም መከራው በርትቷል ይላሉ ነዋሪዎች፡፡ “የታጠቁ ሃይሎች መንግስትን ትደግፋላችሁ በሚል፤ እንዲሁም መንግሰረትም የታጠቀውን አማጺ ሃይል ደገፋችሁ በሚል ማህበረሰቡ በገጠርም ሆነ በከተማ አሰቃቂ ህይወት እየመራ ነው” ብለዋል፡፡
ስለዞኑ የጸጥታ ይዞታና እልባቱ ለዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ በቅርቡ ግን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለዶቼ ቬለ እንደ ተናገሩት የክልሉ መንግስት ውጥን በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ብሆንም በመንግስታቸው ታጥቀው መንግስትን ለሚወጉ ወገኖች ቀርቧል የተባለውን የሰላም ጥሪ ባልተቀበሉት ላይ የኃል እርምጃ መወሰዱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚወሰዱ ጥቃቶችም “መንግስት የጸጥታው አካልን በሁሉም ስፍራ ማስቀመጥ ስለማይችል ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በትብብር ልሰራ ይገባል” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ስዩም ጊቱ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ