1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በዩቲዩብ እና በቲክቶክ የሚደረግ የማንቃት ስራ መሬት ላይ ለውጥ ያመጣልን?

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2016

የበይነመረብ ተሟጋችነት፤ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን፣ በይነመረብን እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የመሳሰሉ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ለውጥን ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውላል።የበይነመረብ ተሟጋችነት በጊዜ እና በቦታ ሳይገደብ በመላው ዓለም በቀላሉ ተደራሽ በመሆኑ ደግሞ ተፈላጊነቱ ጨምሯል። ለመሆኑ ጥቅም እና ጉዳቱ ምንድነው?መሬት ላይስ ለውጥ ያመጣልን?

https://p.dw.com/p/4jQlI
 የበይነመረብ ተሟጋቾች እንደ ዩቱብ ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
የበይነመረብ ተሟጋቾች እንደ ዩቱብ ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ምስል picture-alliance/dpa/M. Skolimowska

የበይነመረብ አንቂነት መሬት ላይ ለውጥ ያመጣል?

የበይነመረብ ተሟጋችነት/online activisim/ በይነመረብን ኢሜል እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የመሳሰሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለቅስቀሳ እና ለውጥን ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውላል። በጊዜ እና በቦታ ሳይገደብ በመላው ዓለም በቀላሉ ተደራሽ መሆኑም ተፈላጊነቱ እንዲጨምር አድርጓል።ለመሆኑ ይህ ዲጅታል ተሳትፎ ጥቅም እና ጉዳቱ ምንድነው? መሬት ላይስ ለውጥ ያመጣልን? የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ትኩረት ነው።
ያለንበት የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዘመን ዝግጅቶች፣ተቃውሞዎች እና እንቅስቃሴዎች የሚደራጁበትን መንገድ ሳይቀር ቀይሯል።ሰዎች ለሰብዓዊ መብት መከበር ፣ለፍትሃዊነት ፣ለህግ የበላይነት መከበር ፣ለአካባቢ ጥበቃ፣ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ለሌሎች በርካታ ጉዳዮች  የሚያደርጉት ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና የማንቃት ስራ እንኳ ከድምፅ ማጉያ እና ከትልልቅ መፈክሮች ወጥተው ወደ ዲጅታሉ ዓለም ገብተዋል።

 የአረብ አብዮት የገጠመዉ እንቅፋት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፣ የበይነመረብ እና የተንቀሳቃሽ ስልኮች ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣት ደግሞ  የበይነመረብ አንቂዎች ወይም አራማጆች/online activisits/ እንዲጨምሩ አድርጓል።
በቅርቡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በወለደው የዋጋ ውድነት የተማረሩ ናይጄሪያውያን፤ እንዲሁም በመንግስት የግብር ጭማሪ ዕቅድ የተቆጡ የኬንያ ወጣቶች ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያደርጉት ለሳምንታት የዘለቀው ሰላማዊ ተቃውሞ ቅስቀሳዎች በስማርት ስልኮች እና በቲክ ቶክ የሚደረጉ ናቸው።
ቀደም ሲልም በጎርጎሪያኑ 2011 ዓ/ም በመካከለኛው ምስራቅ የተካሄደው እና የአረብ አብዮት እየተባለ የሚጠራው የተቃውሞ እንቅስቃሴም በከፊል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተቀነባበረ ነበር። የመብቶች እና ዲሞክራሲ ማሻሻያ ማዕከል በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /CARD/ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በፈቃዱ ሀይሉ እንደሚለው የበይነመረብ አራማጅነት/online activisim/ የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ ቀይሯል።

በፈቃዱ ሀይሉ፤የመብቶች እና የዲሞክራሲ ማሻሻያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር
በፈቃዱ ሀይሉ፤የመብቶች እና የዲሞክራሲ ማሻሻያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተርምስል DW/Y. Gebregziabher

በኢትዮጵያም በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተደረጉ የበይነመረብ አራማጆች ጥረት በ2010 ለመጣው የፖለቲካ ለውጥ የነበረውን አስተዋፅኦ የሚያስታውሰው በፈቃዱ፤በአሁኑ ወቅት ግን መንግስት የበለጠ እየተጠቀመበት ነው ይላል።

 የኢንተርኔት አጠቃቀም ፍትሃዊነት ችግር በኢትዮጵያ
የበይነመረብ አራማጅነት ወይም አንቂነት /ዲጂታል አክቲቪዝም/ እንደ በይነመረብ /ኢንተርኔት/፣ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ፣ ኢሜል እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ያሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለቅስቀሳ፣ እና ለውጥን ለማነሳሳት ጥቅም ላይ ይውላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የበይነመረብ አራማጅነት ከጎርጎሪያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ ውሱን በሆነ መልኩ መተግበር የጀመረ ሲሆን፤ የበይነመረብ እና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መስፋፋትን ተከትሎ  እድገቱ ቀጥሏል።  

እንደ ቲክቶክ፣ የቀድሞው ቲውተር የአሁኑ ኤክስ ፣ ፌስቡክ እና ዩቱብን ከመሳሰሉ ዲጅታል የማኅበራዊ መድረኮች ባሻገር እንደ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም እና ሲግናል ያሉ የግል የመልዕክት መላላኪያዎችም መረጃን ለማደራጀት እና ለማሰራጨት በአሁኑ ጊዜ ለበይነመረብ አራማጆች አስፈላጊ መሳሪያዎች ሆነዋል። በበይነመረብ የሚደረግ ይህ መሰሉ የማንቃት ስራ /ኦንላይን አክቲቢዝም/በጊዜ እና በቦታ ሳይገደብ በመላው ዓለም በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን የሚስችል በመሆኑ ተፈላጊነቱ ጨምሯል።ከዚህ አንፃር አሁኑ ወቅት ሰዎች የተቃውሞም ይሁን የድጋፍ እንዲሁም የእርዳታ እንቅስቃሴ ሲያስቡ ቀድመው የሚመርጡት አንድ የእንቅስቃሴ መንገድም ሆኗል። በፈቃዱ እንደሚለው ፤በአንጻራዊነት ርካሽ መሆኑ እና ሀገር ውስጥ የሌሉ ሰዎች ባሉበት ሆነው በሀገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ ማስቻሉም የበይነመረብ አራማጅነት ሌላው ጠቀሜታ ነው።

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጥላቻ ንግግር፣ሀሰተኛ መረጃዎች፣ የተጭበረበሩ ቪዲዮዎች፣ እና የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲስፋፉ እና ሲያደርጉ ይስተዋላል።
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጥላቻ ንግግር፣ሀሰተኛ መረጃዎች፣ የተጭበረበሩ ቪዲዮዎች፣ እና የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲስፋፉ እና ሲያደርጉ ይስተዋላል።ምስል Imago Images/ZUMA Press/A. M. Chang

በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሏቸው እንደ ፌስቡክ፣ የቀድሞው ቲዊተር የአሁኑ X /ኤክስ/  እና እንደ ዩቲዩብ ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም መልዕክቶችን ማሰራጨት እና ግንዛቤን ማሳደግ ፤ ቀደም ሲል በብሮድካስትም ይሁን በህትመት የመገናኛ ብዙሃን ችላ ተብለው የነበሩ ጉዳዮች እና እንቅስቃሴዎች ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ የጎላ ጠቃሜታ አለው። 

ለኢንተርኔት ክልከላ የባለሙያ መላ
ያም ሆኖ ይህ ዲጂታል ተሳትፎ የራሱ የሆኑ ተግዳሮቶች አሉት።«ዲፕ ፌክ»ን የመሳሰሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች እያደጉ ከመምጣታቸ ጋር  ተያይዞ፤  እውነተኛ ያልሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ድምፆችን መስራት እየተለመደ መጥቷል። ይህም የሀሰት መረጃ ስርጭት፣ የተጭበረበሩ ቪዲዮዎች፣ እና የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲስፋፉ እና ሰዎች እውነታውን ለመለየት እንዲቸገሩ ሲያደርግ ይስተዋላል።

 ጥላቻ አዘል ንግግር በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

ይህም ለበይነመረብ አራማጆች  በመንግስታት ከሚደረገው የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የመዝጋት  እና የበይነመረብ እገዳ  ባሻገር ሌላው ትልቅ ፈተና ነው።በሌላ በኩል የበይነመረብ ተሟጋችነት ራስን  ደብቆ ለመፃፍ የተመቼ በመሆኑ የተጠያቂነት ችግርም ይነሳል።በይነመረብ አራማጅነት /የዲጂታል አክቲቪዝም/ ትልቁ ጥቅም ብዙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀላሉ በማግኘት ዘመቻዎችን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ መቻል ነው። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚደረግ ቅስቀሳ ለውጥ ያመጣልን? የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል። አንዳንዶችም መሬት ላይ የሚያመጣው ውጤት አነስተኛ ነው ይላሉ።በፈቃዱም በዚህ ይስማማል።ውነገር  ግን መሬት ላይ ካለ ስራ ጋር ማቀናጄት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስረድቷል። .

ስልክ የያዘ እጅ
የበይነመረብ አንቂነት መሬት ላይ ለውጥ ስለማምጣቱ የሚጠራጠሩ ቢኖሩም መሬት ላይ ከሚሰራ ስራ ጋር ከተቀናጄ ለውጥ እንደሚያመጣ ባለሙያዎች ይናገራሉ።ምስል oxinoxi - stock.adobe.com

በሌላ በኩል የበይነመረብ ተደራሽነት ችግር እና የዲጅታል እውቀት አለመኖርም በተለይ በአዳጊ ሀገራት ተግዳሮቶች ናቸው። በፈቃዱ «የቤጤዎች ጉባኤ» የሚለው በሀሳብ ከአራማጁ ጋር የማይስማሙ ሰዎችን ከመድረኩ ማገድ እና ማራቅም በበይነመረብ አራማጆች ዘንድ የሚስተዋል ሌላው ችግር ነው።
መልዕክትን ማካፈል እና ግንዛቤን ማሳደግ የአራማጅነት /አክቲቪዝም/ ወሳኝ ነገር ቢሆንም፤ባለሙያዎች እንደሚሉት እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ግን ወደ ተግባር መቀየር አለበት። ስኬታማ ለመሆንም የበይነመረብ አራማጅነት/ዲጂታል አክቲቪዝም/ ከተለምዷዊ የአንቂነት እንቅስቃሴዎች ጋር በጥምረት መጠቀም ያስፈልጋል።ለዚህም በጎርጎሪያኑ መስከረም 2019 ዓ/ም የተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የተደረገው ንቅናቄ ይጠቀሳል። ይህ እንቅስቃሴ  የአየር ንብረት ቀውስን ለመከላከል  የዓለም መንግስታትን ቁርጠኝነት ለመጠየቅ የተደረገ ነው። «ዓርብን ለመጻኢአችን» /Fridays for Future/በሚል በመላው አለም በግሬታ ቱንበርግ የተነደፈው ይህ ንቅናቄ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አድማዎችን እና ተቃውሞዎችን እንዲቀላቀሉ የበይነመረብ መድረኮች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ስማርት ስልክ
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብሮድካስትም ይሁን በህትመት የመገናኛ ብዙሃን ችላ ተብለው የነበሩ ጉዳዮች እና እንቅስቃሴዎች ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ የጎላ ጠቃሜታ አላቸው።ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

በመሆኑም በፈቃዱ፤ውጤታማ ለመሆን በአራማጆች እና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ ባለቤት በሆኑ ኩባንያዎች መደረግ አለባቸው የሚላቸው ነገሮች አሉ። «ከአራማጅነት ጋር የተያያዘው ነገር በአራማጆቹ ናቸው ዋነኛ የጉዳዩ ባለቤቶች። ስለዚህ ትልቁ ሸክምም እነሱ ትከሻ ላይ ነው የሚያርፈው።» ካለ በኋላ አራማጅነት መንግስትን መተቸት ብቻ ሳይሆን በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ያስረዳል። ከነዚህም መካከል «ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፣ዶሞክራሲያዊ ስርዓት ይገንባ፣የአካባቢ ደህንነት ይጠበቅ፣ማኅበራዊ ፍትህ ይስፈን ፣ትምህርት ለሁሉም ይዳረስ ፣ኢንተርኔት ለሁሉም ይዳረስ፣ጤና ቅድሚያ ይሰጠው ወዘተ የሚል ሊሆን ይችላል።»በማለት ዘርዝሯል።ስለሆነም እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት አራማጆች በዕለት ተዕለት በሚለዋወጡ አጀንዳዎች ከመጠመዳቸው በፊት የቆሙለትን ዓላማ በቋሚነት በመያዝ በወቅታዊ እና እየመጡ በሚጠፉ አጀንዳ ላለመጠለፍ መጠንቀቅ ፣በሁለተኛ ደረጃ መሬት ላይ የበይነመረብ ስራቸውን የሚደግፍ ስራ ለመስራት ተቋም መፍጠር እንዳለባቸው መክሯል።ያ ካልሆነ «የተወራው እዚያው ከስሞ ሊቀር ይችላል።»ሲል አክሏል።
«ከዚያ ውጭ ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች አሉ።በተለይ ከጥላቻ ንግግር፣ ከተዛባ ንግግር እና ከ«ቡሊንግ» ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማኅበራዊ «ሚዲያዎቹ» እነዚያን «ሪጉሌት» የማድረግ እና መድረኩን ጤናማ የማድረግ ሀላፊነት አለባቸው።» በማለት ገልጿል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ