1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዐማራ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት አስመልክቶ የሳንታ ባርባራ አዉራጃ ውሳኔ

ዓርብ፣ የካቲት 22 2016

በውሳኔ ዐሳቡ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፣ ሴቶች ህጻናትና አዛንቶችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የዐማራ ንጹሃን ዜጎች፣ በመንግስት ኃይሎች በድሮንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።የመንግስት የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች ታጣቂዎች፣ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጾታዊና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸማቸውንም ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4d4og
የሳንታ ባርባራ አዉራጃ አስተዳደር የአማራ ሕዝብ የሚያደርገዉን «ትግል» የሚደግፍ ዉሳኔ አሳልፏል
በካሊፎርኒያ ግዛት በሳንታ ባርባራ አዉራጃ ከሚገኙ ከተሞች አንዱምስል Getty Images/AFP/K. Grillot

በዐማራ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት አስመልክቶ የሳንታ ባርባራ አዉራጃ ውሳኔ

 

በኢትዮጵያ የዐማራ ህዝብ የሚያደርገውን ትግል የሚደግፍ የውሳኔ ዐሳብ ማሳለፉን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት፣የሳንታ ባርባራ አውራጃ አስታወቀ።የሳንታ ባርባራ አውራጃ በሙሉ ድምጽ ያሳለፈው ውሳኔ፣ በዐማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት የበርካታ ሰዎች ህይወት እየቀጠፈ፣ሰላማዊ ዜጎችን አደጋ ላይ ጥሎ፣ ሰላምን፣ብዙኃነትንና የሰብዓዊ መብቶችን እየተፈታተነ ነው ብሏል።

በውሳኔ ዐሳቡ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፣ ሴቶች ህጻናትና አዛንቶችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የዐማራ ንጹሃን ዜጎች፣ በመንግስት ኃይሎች በድሮንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።የመንግስት የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች ታጣቂዎች፣ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጾታዊና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸማቸውንም ገልጿል።

ለምኪን የዘር ማጥፋት መከላከል ኢንስቲትዩትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማጥፋት መከላከል ልዩ አማካሪ፣ በኢትዮጵያ የዐማራ ክልል ያለውን ጦርነት ተከትሎ፣የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን የውሳኔ ዐሳቡ አብራርቷል።
 
ሌሎች በክልሉ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችንና የሌሎች አካላት ማስረጃዎችን ያጤነው የአውራጃው የውሳኔ ዐሳብ ድጋፍ መስጠቱን አስታውቋል።


 "የሳንታ ባርባራ አውራጃ፣ የባይደን አስተዳደር፣ በኢትዮጵያ ለብሔር ተኮር ግጭቶች  ምላሽ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የአሜሪካ የቀረጥና ታሪፍ ነጻ መብት/ አጎዋ /ተጠቃሚነት፣ግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እስኪያገኝና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እስኪስተካከል ድረስ እንዲታገድ፣ የሱፐርቫዘሮቹ ቦርድ ለዐማራ ህዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ ያረጋግጣል።"

ወይዘሮ ሰርክዐዲስ ይግዛው፣በካሊፎርኒያ የሳንታ ባርባራ አውራጃ ነዋሪ ሲሆኑ ለውሳኔው መተላለፍ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ይነገርላቸዋል፤ ውሳኔው በተላለፈበት ስነስርዓት ላይም ንግግር አድርገዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት ኃይላትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በአማራ ክልል የሚደረገዉ ዉጊያ የርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት እያጠፋ ነዉ
በአማራ ክልል ከኢትዮጵያ መንግስት ኃይላት ጋር ከሚፋለሙት የፋኖ ታጣቂዎች አንዱ።ላሊበላምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

"በተለይ በተለይ እኛ እየሰራን ላለነው፣ድምጽና ከፊት የሚሆንልን ሰው ነበር የፈለግነው፤እና በእዚህ አንፃር ምን ላድረሰግላችሁ ሲል እኛ የጠየቅነው ውሳኔ ነበረ።ውሳኔ እንግዲህ በአጭሩ ምንድን ነው ጥያቄን መፈለግ ነው።ከእዛ ደግሞ ለእዛ ጥያቄ መፍትሔ መስጠትና ያንን መፍትሔ ደግሞ ተግባራዊ አድርጎ ችግሩን የመፍታት ስለሆነ በጀመርነው አካሄድ ውሳኔው ለእኛ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው፣ከእዛ ላይ መገንባት ስለምንችል፣በእዛ አንጻር ሄደን፣የደረስንበት ደረጃ ደርሰናል።

በሎስ አንጀለስ የዐማራ ማኀበር አባል ዶክተር ይንገስ ይግዛው፣የውሳኔ ዐሳቡን አስመልክቶ ለዶይቸ ቨለ በሰጡት አስተያየት፣ የሚከተለውን ተናግረዋል።

" በብዛት የማግባባት ስራ የሚሰራው በኮንግረስ እና በሴኔት ደረጃ ነው የምንሰማው እና አሁን ለምን በአካባቢ በቅርብ በምናገኛቸው የሕዝብ ተወካዮች ማድረግ የሚችሉትን ለምን አናየውም ከሚል አንፃር ተነስቶ የሄድንበት ሂደት ነው።"

 የአሜሪካ ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዯች ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ዋሲ ተስፋ በበኩላቸው፣ከዚህ ቀደምበካሊፎርኒያ ግዛት ሆሊውድ በተባለው አውራጃ የተላለፈው ተመሳሳይ የድጋፍ ውሳኔ ወደሚመለከታቸው የአሜሪካ ከፍተኛ የስልጣን አካላት መተላለፉን ተናግረዋል።

" የሆሊውድ ከተማን አቋም ከንቲባው ነው የፈረመው፣እሱ ደግሞ ለባይደን እና ለኮንግረስ ተላልፏል።"

ዶክተር ይንገስ፣የእነዚህ ውሳኔዎች መተላለፍ ጠቀሜታ ምንድነው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ያለውን ችግር ጥልቀት ለማሳወቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

"በእኛ በተለይ በዐማራ ጄኖሳይድ አድቮኬሲ ላይ ትልቁ ጥያቄ ብዙ ጊዜ የሚነሳው  እና የእኛ ማኀበረሰብ ተስፋ የሚቆጠርበት እነዚህ ሰዎች አይሰሙንም የሚል ብዙውን ጊዜ ስሞታ እንሰማለን።በእኔ ዕይታ ከታች ወርደን በካውንቲ ደረጃ፣በከንቲባ ደረጃ እውቅና ማግኘት ትልቁን የበር ቁልፍ እንደማግኘት አድርጌ ነው የማየው እና መሰረት ይጥላል። የችግሩን ጥልቀት ከታች ከምንመርጣቸው ተወካዮች ጋር ቀርበን የመነጋገር በቀላሉ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር የማስተዋወቅ ሂደት ነው የሚሆነው።

በጉዳዩ ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማግኘት  ጥረት ብናደርግም ምላሽ ባለማግኘታችን አልተሳካም።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ