1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"በውይይት ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም እናድርግ" -አቶ ጌታቸዉ ረዳ

ሰኞ፣ ሰኔ 28 2013

ባለፈው ሳምንት መቐለን የተቆጣጠሩት የትግራይ አማጽያን ለተኩስ አቁም ላቀረቧቸው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ መንግስት መልስ ካላገኙ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ አስታወቁ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ኢትዮጵያ ላይ በቅርብ የሚታይ አደጋ እስካልመጣ ድረስ ከማንም ኃይል ጋር ውጊያ፣ ግጭት አንፈልግም" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3w3qF
Äthiopien Tigray-Krise
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

"በውይይት ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም" እንዲረግ እንፈልጋለን"

ባለፈው ሳምንት መቐለን የተቆጣጠሩት የትግራይ አማጽያን ለተኩስ አቁም ላቀረቧቸው ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል መልስ ካላገኙ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ አስታወቁ። በፌድራል መንግሥቱ "ሽብርተኛ" ተብሎ ከተፈረጀው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ "በውይይት ላይ የተመሠረተ ተኩስ አቁም" እንዲረግ እንደሚፈልጉ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ትናንት እሁድ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ካቀረቡ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ አግኝተው እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው "ምንም ነገር የለም። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እስካሁን የምንነጋገረው በጠብመንጃ ብቻ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ለመጠየቅ በጠቅላይ ምኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ለሆኑት ቢልለኔ ስዩም በኢ-ሜይል እና በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች "ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ውጊያ እንቀጥላለን" ያሉት አቶ ጌታቸው "መብራት በኃይል እናስቀጥላለን፤ ስልክ በኃይል እናስቀጥላለን። ልክ የእህቶቻችንን መደፈር በኃይል ለጊዜው እንዳስቆምንው ሙሉ በሙሉ እንስኪቆም ድረስ እንቀጥላለን። ያንን ለማድረግ ኬንያ ድረስ መሔድ ያለብን አይመስለኝም። ያንን ለማድረግ ደሴን መያዝ ያለብን አይመስለኝም። መያዝ ካለብን ግን እንይዛለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ "ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ አደጋ፤ በቅርብ የሚታይ አደጋ እስካልመጣ ድረስ ከማንም ኃይል ጋር ውጊያ ግጭት አንፈልግም" ብለዋል።

Äthiopien Getachew Reda in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Geberegeziabeher

"በሰላም፣ በትብብር መልማት፣ ማደግ እንፈልጋለን" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ "ማደግ ስለምንፈልግ ሰላም እናስቀድማለን፤ ለሰላም የሚከፈል ክፍያ ማንኛውም ነገር እንከፍላለን። ሰላም መፈለጋችን ክብራችንን፤ ሰላም መፈለጋችን ህልውናችንን የሚነካ ከሆነ ግን ተገደን ሰላምን ለማምጣት የምንገባባቸው ግጭቶች ይኖራሉ" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱ ከተገለጸ በኋላ መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ  በተናጠል የተኩስ አቁም አውጇል።  በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ስም በወጣው መግለጫ የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች ቀርበዋል። የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ወጥተው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመልሱ የሚጠይቀው ቀዳሚው ቅድመ-ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ መርማሪ አካል እንዲያቋቁም ከሥምምነት እንዲደረስም ጠይቀዋል።

ከአቶ ጌታቸዉ ረዳ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦

 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ