1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በውኃ ጋን ጫካ ተከባ ውኃ የተጠማችው አዲስ አበባ ፤ እንዴት ጥሟን ትቁረጥ?

ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

አዲስ አበባ ከባሕር ጠለል በላይ 2,355 ሜትር ላይ የምትገኝ በመሆኗ የገፀ ምድር ውኃን በዝናብ እና በምንጭ መልኩ በጫካ ከተከበበው ተራሮቿ ለኗሪዎቿ ስትለግስ ቆይታለች። ከዚህም ባለፈ የከርሰ ምድር ውኃን ከጉያዋ አውጥታም የሕዝቧን ጥም ስትቆርጥ ኖራለች። ሆኖም ዛሬ የከርሰ ምድር ውኃ ከአዲስ አበባ ጉያ እየነጠፈ ስለመሆኑ አጥኚዎች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4l9uz
Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Eshete Bekele/DW

ወ/ሮ ፌቨን (ስሟ የተቀየረ) በመሀል አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ  የጋራ የመኖሪያ ሕንጻ ውስጥ ነዋሪ ናት። ባለትዳርና የልጆች እናትየሆነችው ይህች የዋና ከተማዋ ነዋሪ ውኃ እነሱ በሚኖሩበት ሕንጻ የሚመጣው በሳምንት ሦስት ቀናት መሆንኑ ትናገራለች። ቅዳሜ፣ እሑድ እና ረቡዕ ወ/ሮ ፌቨን እና የእርሷ አካባቢ ነዋሪዎች ውኃ ከቧንቧ የሚያገኙባቸው ቀኖች ናቸው። 


ይህን መሰሉ የውኃ ፈረቃ በአካባቢው ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ገደማ እንደሚሞላው የተናገረችው ወ/ሮ ፌቨን ሁለት ሺህ ሊትር የሚይዝ የውኃ ማጠራቀሚያ ባይኖራቸው ኖሮ ችግሩ የከፋ ይሆን እንደነበር ትገልፃለች።  ኮተቤ አካባቢ የሚኖሩት ወላጆቿም በተመሳሳይ በሳምንት ሦስት ቀናት ብቻ ውኃ እንደሚያገኙ እንዲሁ ለዶቼ ቬለ /DW/ ስትገልጽም፤ «ውሃ ስትመጣ ጠብቀው ባሏቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች እና በርሜሎች ሁሉ በሞሙላት ነው የሚጠቀሙት።» ብላለች። 


የአዲስ አበባ ከተማ የውኃ ማማ ሊያስብላት የሚያስችል ተራሮችን ማለትም እንጦጦን በእራስጌዋ ፣ የሳንሱሲ ደንን በሰሜን ምሥራቅ ጉያዋ እና የየካ ኮተቤ ተራራማ ጫካን በሰሜን ምዕራብ አካሏ አቅፋለች። ሆኖም የውኃ ምንጮች መገኛ የሆኑ ተራራዎችን እና ጫካዎችን ያቀፈችው አዲስ አበባ የውኃ አቅርቦት ችግር ለዘመናት ሰንጎ ይዟታል። ችግሩ ዛሬም ከከተማዋ መሀል እስከ ከተማዋ ዳር የነዋሪውን ሕይወት እየፈተነው ቀጥሏል። በአዲስ አበባ የአትላስ ሆቴል አካባቢ ነዋሪዋ ወ/ሮ ተናኜ (ስማቸው የተቀየረ) ቤት በማከራየት በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን ይገፋሉ።

 

አትላስ በከተማዋ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ በርካታ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኙበት አካባቢ ነው። ለረጅም ጊዜያት ውኃ በሳምንት ሁለት ቀናት ያገኙ እንደነበር፤ አሁን ደግሞ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እንደሆነ ወይዘሮዋ ይናገራሉ። «እርሱም ማታ ነው የሚመጣው። በጄሪካን እስከ 10 ብር እየገዛን ነው የምንጠቀመው።» ይላሉ። ወ/ሮ ፌቨን ስለ ውኃ ስትናገር፤ «ከውኃ መብራት ቢጠፋ ይሻላል። ምክንያቱም የምታበስለው በውኃ ነው። ለጽዳት የምትጠቀመው በውኃ ነው። ውኃ ከሕይወት ጋር ምንም የምትነጥለው አይደለም።» ነው የምትለው። 

የውኃ እጥረት በአዲስ አበባ
የውኃ እጥረት በአዲስ አበባ ምስል Seyoum Getu/DW

የዋና ከተማይቱ የውኃ ፍላጎትና አቅርቦት 

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በአሁኑ ጊዜ ከ5.7 ሚሊየን በላይ እንሚደርስ የወርልድ ፖፑሌሽን ሪቪው መረጃ ይጠቁማል። ከተማዋ ሰፋፊ የግንባታ እና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች የሚስተዋልባት ብሎም ከተሜነት እየተስፋፋባት በመሆኑ የውኃ አቅርቦት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ከተማ አስተዳደሩ ግን ለዘርፈ ብዙ ፍላጎቶቿ ቢቂ ውኃ ማቅረብ ተስኖት ለረጅም ዘመናት ዘልቋል። ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ በውኃ ሃብት አስተዳደር የካባተ ዕውቀት ያላቸው ትውልደ ኢትዮዽያዊ ሲሆኑ በአሜሪካን አገር ደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መምህር እንዲሁም በታምፓ ቤይ የእቅድና የውሳኔ አሰጣጥ ኃላፊና የውኃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ ናቸው። የአዲስ አበባን የውኃ እጥረት በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ጥሩሰው ከተማዋ ከሚያስፈልጋት 1.2 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 40 በመቶ ብቻ ሽፋን እንዳላት አመልክተዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ የነፍስ ወከፍ የውኃ ፍጆታ ከከተማው የሕዝብ ቁጥር ጋር ያለመጣጣሙን  ከማኅበረሰቡ የአኗኗር ዘዬ መቀየር ጋር ያዛመዱት የውኃ ተመራራማሪው ማኅበረሰቡ ውኃን በባልዲ ቀድቶ ለንጽህና ከሚጠቀምበት አኗኗር ወጥቶ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መኖር በመጀመሩ የውኃ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከፍ ማለቱን ገልፀዋል። ዛሬ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት ችግር ስለገጠማቸውም ከገቢያቸው ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን ውኃ ለመግዛት እንደሚያወጡም ዶ/ር ጥሩሰው ይናገራሉ። ወ/ሮ ፌቨን በከተማዋ እየተስፋፉ በመጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ውኃ ባለመኖሩ ከመፀዳጃ ቤቶች የሚፈጠረው ሽታ ከባድ ነው ትላለች። «ውኃ የለም ብዬ አላስብም። የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ እና አዳዲስ ግንባታዎች እየተገነቡ በመሆኑ ከሕዝብ ቁጥር እድገት ጋር የተመጣጠነ የውኃ መሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር አለ ብዬ ነው የማስበው።» ስትልም ያስተዋለችውን ታስረዳለች። 

የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ
የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ምስል DW/E. Bekele Tekle


በከተማዋ የውኃ አቅርቦት ውሱንነት የተከሰተበት ምክንያት የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር የውኃ አቅርቦቱም ተያይዞ ባለማደጉ መሆኑን ዶ/ር ጥሩሰው ይናገራሉ «ዛሬ እየተሠሩ ነው የሚባሉ ፕሮጀክቶች ከ10-15 ዓመታት በፊት መምጣት የነበረባቸው ናቸው።»ም ይላሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2002 ዓ.ም. ንጹሕ ውኃን በጥራት እና በሚቻል ዋጋ ለሁሉም ማዳረስ የሰብአዊ መብቶች አካል መሆኑን ደንግጓል። ሆኖም ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የውኃ ጉባኤ የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ከዓለም 40 በመቶ ያህሉ ሕዝብ በከፋ የውኃ ቀውስ ውስጥ ይገኛል። 


የዓለም የንጹሕ ውኃ (freshwater) አቅርቦት ፍላጎትም አሁን ካለው በጎርጎሮሳዊው 2050 ዓ.ም. ላይ በ40 በመቶ እንደሚጨምር መረጃዎች ይጠቁማሉ።  ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 17ቱ የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ግብ 6፤ ማለትም ንጹሕ ውኃ እና ንጽሕና አጠባበቅ ከግብርና፣ ኃይል፣ አካባቢ እና ውኃ ጋር የተቆራኘ ነው። ከዚህ በመነሳትም ከተሞች ካለ በቂ የውኃ አቅርቦት ዘላቂ ልማት ሊያረጋግጡ እና ሕዝባቸውን ከድህነት ለማውጣት እንደሚቸገሩ ያመለክታል። 

የከርሰ ምድር ውኃ ባንክ ጉድለት እና ብክነት 

አዲስ አበባ ከባሕር ጠለል በላይ 2,355 ሜትር ላይ የምትገኝ በመሆኗ የገፀ ምድር ውኃን በዝናብ እና በምንጭ መልኩ በጫካ ከተከበበው ተራሮቿ ለኗሪዎቿ ስትለግስ ቆይታለች። ከዚህም ባለፈ የከርሰ ምድር ውኃን ከጉያዋ አውጥታም የሕዝቧን ጥም ስትቆርጥ ኖራለች። ሆኖም ዛሬ የከርሰ ምድር ውኃ ከአዲስ አበባ ጉያ እየነጠፈ ስለመሆኑ አጥኚዎች ይናገራሉ። ከተማዋ ባለፉት ዓመታት በከርሰ ምድር ውኃ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ ሆና በመቆየቷ ቀደም ብለው በአቃቂ አካባቢ 2008 ዓ.ም. የተሠሩት አሁን መድረቃቸው እና 500 ሜትር ድረስ ወደ ታች እየተቆፈረ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ጥሩሰው የከርሰ ምድር ውኃ ተመልሶ እንዲያገግም ማሳረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል። «የከርሰ ምድር ውኃ መሬት ውስጥ ዘልቆ እስኪገባ ድረስ ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት ሊፈጅበት ይችላል። እሱን ልክ እንደ ባንክ ክሬዲት ነው የምንወስደው። የምንጠቀመው ከእዚያ በላይ ከሆነ ልክ እንደ የባንክ ክሬዲት እየቀነሰ ኔጌቲቭ ሊገባ ይችላል።» ሲሉም አብራርተዋል። 


ውኃ ሸቀጥ ሳይሆን የሕዝብ ሃብት ቢሆንም በከተማዋ የከርሰ ምድር ውኃን አውጥተው በግል የሚሸጡ መኖራቸውን ነዋሪዎች ይጠቁማሉ። «በከተማው ውስጥ ውኃን አውጥተው ትልልቅ ሕንጻ ላላቸው ሰዎች የሚሸጡ አሉ። እናም ውኃው ካላ፤ ለምን መንግሥት አውጥቶ እና አጣርቶ ለዜጎቹ አያቀርብም? ብዬ እጠይቃለሁ።» ስትል ወ/ሮ ፌቨን ትዝብቷል ለዶቼ ቬለ ገልፃለች። ዶ/ር ጥሩሰውም ወደ አዲስ አበባ በተጓዙበት ወቅት አንድ ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ በ1,200 ብር ሲሸጥ መመልከታቸውን በማንሳት የአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን ግን አንድ ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃን 7.14 ሳንቲም እንደሚሸጥ ተናግረዋል። 

የአቃቂ የከርሰ ምድር ውኃ ማከፋፈያ በጎርፍ በተጥለቀለቀበት ወቅት
የአቃቂ የከርሰ ምድር ውኃ ማከፋፈያ በጎርፍ በተጥለቀለቀበት ወቅትምስል Seyoum Getu/DW

ችግሩ መፍትሄ ይኖረው ይሆን? 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን የገፀ ምድር ውኃን ከለገዳዲ ፣ ድሬ እና ገፈርሳ ግድቦች በመሳብ ለነዋሪው ሲያቀርብ ቆይቷል። ይህም የአቅርቦቱን 40 በመቶ ይሸፍናል። የተቀረው 60 በመቶ ደግሞ ከከርሰ ምድር የሚገኝ ነው። ሆኖም ከውኃ ፍላጎቱ አኳያ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመሸፈን አስተዳደሩ ከከተማዋ 90 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኝ ጅዳ ሮቢ ከሚባል አካባቢ ውኃ ስቦ በቅብብሎሽ ወደ ከተማዋ ማምጣት እንዳለበት ዶ/ር ጥሩ ሰው ጠቁመዋል። «ለምን የውኃ መሠረተ ልማቶች በከተማ አስተዳደሩ እንዳልተገነቡ እኔም አልገባኝም። መሠራት አለበት። ውኃ ማለት የሰብአዊ መብት ነው። አሁን በአገሪቱ ንጹሕ የኤሌክትሪክ ኃይል እየተመረተ ይገኛል። እሱን ተጠቅሞ ውኃ ማቅረብ ይቻላል።» ሲሉም የዘርፉ ባለሞያ ምክረ ሃሳባቸውን አጋርተዋል። 


ለመሆኑ የከተማዋ አስተዳደር ከከተማዋ እድገት እና የህዝብ ቁጥር ትንበያ ጋር የተጣጣመ መሪ እቅድ አለው ወይ? ችግሩንስ ለመፍታት ምን እየሠራ ይገኛል? የሚሉትም ጥያቄዎች በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእቅድና ልማት ቢሮ እና የውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን ኃላፊዎችን ለማነጋገር ዶቼ ቬለ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም የሚመለከታቸው አካላት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን መግለጽ እንወዳለን። 

 

ዳግም ተረፈ

ሸዋዬ ለገሠ