1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዋግኽምራ ታጣቂዎች 11 ሰዎች ገደሉ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 19 2013

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ በኒሯቅ ከተማ ታጣቂዎች ጥቃት ከፍተው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸዉ ተሰማ። የበኒሯቅ ነዋሪዎችና የወረዳው አስተዳደር በአካባቢው ላይ አሁንም ስጋትት በመኖሩ የመከላከያ ኃይል ወደ ስፍራዉ እንዲላክላቸው ጠይቀዋል፡፡ የደረሰው ጉዳት ገና እየተገመገመ ነዉ ተብሎአል።

https://p.dw.com/p/3se3H
Trockenheit im Westnordlische Äthiopien Waghmera Zone
ምስል DW/A. Mekonnen

11 ሲቪል ነዋሪዎችን ገድለዋል

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ በኒሯቅ ከተማ ትናንት ታጣቂዎች ጥቃት ከፍተው በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የወረዳው አስተዳደር አስታወቁ፡፡ አሁንም በአካባቢው ስጋትት በመኖሩ የመከላከያ ኃይል ወደ አካባቢው እንዲላክላቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡ የክልሉና የዞኑ የፀጥታ ኃላፊዎች የደረሰው ጉዳት ገና እየተገመገመ መሆኑን ገልፀዋል። 

የታጠቁ ኃይሎች ክልሉን የግጭትና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ የአማራ ክልል ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜ በሰጧቸው መግለጫዎች አስጠንቅቀዋል። በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀል፣ መዋከብና መንገላታት እንዲቆም የሚጠይቁ ሰልፎች ደግሞ በአማራ ክልል የተለያዩ በርካታ ከተሞች ሲካሄዱ ሰንብተዋል። 

ሰኞ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተኩል ሲሆን በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ በኒሯቅ ከተማ ታጣቂዎች በአደረሱት ጥቃት ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን አንድ የአካባቢው ነዋሪ ትናንት ከድርጊቱ ቦታ ሆነው ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል። ጥቃቱ የተፈጠረው በአካባቢው ከፍተኛ መዘናጋት ስለነበር አስታውሰው፣ ከአንድ ወር በፊት በዚሁ ዞን ፃታ በተባለ አካባቢ የተፈጠረውን ጥቃት እንደ ማነፃፀሪያ አቅርበዋል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ  የአማራ ክልል ሚሊሺያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደተናገሩት ታጣቂዎች 11 ንፁህ ነዋሪዎችን ገድለዋል፡፡ በመንግስት የፀጥታ ኃይልና “ጁንታ” ብለው በጠሯቸው ኃይሎችም ጉዳት መድረሱን፣ ግን ደግሞ አጠቃላይ የጉዳቱ መጠን ገና እየተጠና መሆኑን አስረድተዋል፡፡  ከወር በፊት እነኝሁ ታጣቂዎች በዞኑ ፃግብጂ ወረዳ ፃታ በተባለች ከተማ ተመሳሳይ ጥቃት አድርሰው ህይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ