በኢትዮጵያ የተደጋገመው የደን ቃጠሎ | ጤና እና አካባቢ | DW | 26.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

በኢትዮጵያ የተደጋገመው የደን ቃጠሎ

ካለፈው ሐሙስ ዕለት ጀምሮ በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ ተነስቷል። እስካሁን በሁለት አካባቢዎች ከተነሳው እሳት አንዱን በአካባቢው ኅብረተሰብ እና የፀጥታ ኃይሎች ርብርብ ማጥፋት የተቻለ ሲሆን አንደኛው ገና አልጠፋም። ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደን ቃጠሎ መደጋገሙን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:28

በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ

በየዓመቱ ከ150 እስከ 200 የሚሆኑ ተራራ ወጪዎች የባሌ ተራራዎች ላይ እንደሚወጡ ሳራ ኪንግደም የተባሉ ጸሐፊ ይገልጻሉ። ሳራ ኪንግደም  የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ገድላቸውን በዘረዘሩበት ጽሑፍ የባሌ ተራራዎችን ከእሳተ ጎሞራ እሳት እና መስታወት መሰል በረዶ የተሠሩ ሲሉ ይገልጿቸዋል። ጸሐፊዋ ደመና፣ ጭጋግ እና ዝናብ አይለያቸውም ያሏቸው የባሌ ተራራዎች በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው ደረቅ የአየር ጠባይ ታክሎበት በተደጋጋሚ ሰደድ እሳት እያቃጠላቸው ነው። በ20 ቀናት ውስጥ  ዳግም ባለፈው ሳምንት በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተነሳው እሳት ዛሬም ሙሉ ለሙሉ እንዳልጠፋ የፓርኩ ኃላፊ አቶ አስቻለው ጋሻው ለዲ ደብልዩ ገልጸዋል።

በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ እሳት ሲነሳ ቶሎ የማይጠፋበትም ሆነ የጠፋ መስሎ ዳግም የሚያገረሽበት ምክንያት እሳቱን አምቆ በማቆየት የሚቀጣጥል ተክል በስፍራው መኖሩን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው ይናገራሉ።

የባሌ ተራራዎች ከባሕር ጠለል በላይ 4,000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኙ ሲሆን እንዲህ ያለ ስፍራ በሌላ የአፍሪቃ ክፍል እንደሌለ ነው የሚነገረው። እሳት ከተነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው ቱሉ ዲምቱ ተራራ በኢትዮጵያ ከራስ ዳሸን ቀጥሎ በከፍታው ሁለተኛው ተራራ ነው። 4,377 ሜትር አንዳንዶችም 4337 ሜትር ነው ይላሉ። ራስ ዳሸን ደግሞ 4,550 ሜትር።

የባሌ ተራራዎችን ከጎበኙት አንዷ የሆኑት ሳራ ኪንግደም እንደሚሉት በዚህ ስፍራ እንስሳትም ሆኑ ተክሎች እንዲሁም አእዋፍ የአየር ጠባዩን፣ የኦክስጅን እጥረቱን፤ ጠንካራውን ንፋስ እና የፀሐይ ጨረሩን ተቋቁመው እንደሚገኙ ነው የገለፁት። የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ስፍራው በብዝሃ ሕይወት የታደለ፤ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንስሳት እና እጽዋትን ያቀፈ ነው ይሉታል።

እንዲያም ሆኖ በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ያነደደው የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ላይ ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ የተነሳው ቃጠሎ ያደረሰው ጉዳትም ሆነ ያካለለው ስፋት ገና አልታወቀም። በነገራችን ላይ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ባለው የብዝሃ ሕይወት ስብጥር ጠቀሜታ ምክንያት ዓለም አቀፍ ብሔራዊ ፓርክ ሆኖ በተመ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

ዶክተር ዘውዱ እሸቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት እና የደን ሃብት አያያዝ ባለሙያ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት 18 ዓመታት ገደማ ወዲህ በየጊዜው የሚነሳው የደን ቃጠሎ መንስኤው ሊጠና እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደን ይዞታዋ በተመናመነው ኢትዮጵያ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር ያለመ የ10 ዓመት ብሔራዊ መርሃግብር ከወራት በፊት ይፋ ተደርጓል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኤኮኖሚ ስልቱን እውን ለማድረግ ደግሞ የደን ውድመት እና መመናመንን የሚያስቀር ዘዴ መከተል እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። የአካባቢ፣ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርም ይህን ማድረግ ከተቻለች ብቻ ኢትዮጵያ የታቀደውን የልማት ግብ ማሳካት እንደምትችል አመልክቷል። ለተግባራዊነቱም ከኖርዌይ እና ስዊድን የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን በዘርፉ ላይ በትብብር የሚሠራው የተመ የልማት መርሃግብር UNDP መረጃ ይገልጻል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን በፌስቡክ ገፁ ላይ በባሌ ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ከ1500 በላይ የሚገመቱ ሰዎች ከመዳወለቡ ዩኒቨርሲቲ፤ ከአካባቢው ነዋሪዎች፤ የዞን እና የወረዳ አመራር አካላት የፀጥታ ኃይሎች፤ አጋር ድርግቶች እና የፓርኩ ጽሕፈት ቤት በጋራ መሰማራታቸውን አመልክቷል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች