1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሰመኮ ዓመታዊ ዘገባ

ዓርብ፣ ሐምሌ 1 2014

እንደዘገባው በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው በሁለቱ ክልሎች ቢያንስ 403 ሰዎች ተገድለዋል ።በጦርነቱ በተካፈሉ በሁሉም ኃይሎችና በተለይም በትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በተወሰዱ እርምጃዎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች ከፍርድ ውጪ ተገድለዋልም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4DrYB
Äthiopien | Jahresbericht Human Rights Commission in Addis Ababa
ምስል Solomon Muche/DW

የኢሰመኮ ዓመታዊ ዘገባ

በኢትዮጵያ ዘላቂ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ባለፈው አንደ ዓመት ውስጥ መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ይፋ ባደረገው የአንድ ዓመት ሪፖርቱ ተናገረ። ኢሰመኮ ከሰኔ 2013 እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም ባሉት 12 ወራቶች የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በዳሰሰበት ሪፖርቱ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶችን ፣ በማረሚያ ቤት እና በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች የነበሩትን ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎችና እና  ሰብዓዊ አያያዞችን ተመልክቷል።  
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተከስተዋል ያለው ሪፖርቱ እነዚህም እጅግ አስከፊ የሆኑት የበርካታ ሰዎች ሞት ፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ፣ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት ጥሰቶች በመንግሥት ኃይሎች እና ከመንግሥት ውጪ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎች እና ቡድኖች በጦርነትና ግጭት አውድ ውስጥ የተፈፀሙ ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ፣ በሴቶችን ፣ ሕፃናት ፣ አረጋዊያንን እና አካል ጉዳተኞችም ላይ ጭምር በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተፈፀሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው ብሏል።
"ጦርነትና ግጭት የፖለቲካ ውድቀት ውጤት ስለሆነ ስር ለሰደደው ችግራችን ዘላቂ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔ አስፈላጊነቱን የሚያስገነዝብ ነው" ብሏል ሪፖርቱ። 

የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን የተመለከተው የሪፖርቱ ክፍል "ባለፉት 12 ወራቶች በሕይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ቀጥሏል" ይላል።
በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው በሁለቱ ክልሎች ቢያንስ 403 ሰዎች ተገድለዋል ፣ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ኃይሎችና በተለይም በትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በተወሰዱ እርምጃዎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች  ከፍርድ ውጪ ተገድለዋልም ብሏል።
እንዲሁም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በተመሳሳይ ወቅት በአማራ ክልል በነበረባቸው አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀሙንና ይሄው ቡድን በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ ብሔርን መሠረት አድርጎ በፈፀማቸው ጥቃቶች ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል የአማራ ብሔር ተወላጆች በግፍና በጭካኔ መጨፍጨፋቸውን ኮሚሽኑ ተናግሯል።
እንዲሁም በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቡድኑ በፈፀመው ጥቃት 11 የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ 14 የከረዩ ሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት የሆኑ ሰዎች በክልሉ የፀጥታ አካላት ተገድለዋል ብሏል።
ኮሚሽኑ በጋምቤላ፣  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከፍርድ ውጪ ግድያዎች መፈፀማቸውንም ዘርዝሯል። 

Äthiopien | Jahresbericht Human Rights Commission in Addis Ababa
ምስል Solomon Muche/DW

በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ ከጭካኔ ፣ ኢሰብዓዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶች ጥሰቶች መፈፀማቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አቅርቧል።
በተለይ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የዘፈቀደ እሥራት ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ማሰር ፣ አስገድዶ መሰወር ፣ የቤተሰብና የሕግ ባለሙያዎች ጉብኝትን መከልከል ፣ በተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት ማቆየት በሰፊው መስተዋላቸው ተመላክቷል። 

በሰሜኑ ጦርነት ተሳታፉ የነበሩ ሁሉም ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችን እና ድንጋጌዌችን በሚጥስ መልኩ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይህንኑ ድርጊት ሲፈፅሙ እንደነበርም ተገልጿል።
በአማራ ክልል ብቻ ከ 10 ሺህ በላይ ዜጎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ በጅምላ መታሰራቸውን የገለፀው የኢሰመኮ ሪፖርት በትግራይ ክልል ከሐምሌ 2013 ዓ. ም እስከ ግንቦት 2014 ዓ. ም ድረስ በተለያዩ ወቅቶች 39 የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ተይዘው ከቀናት እስከ በርካታ ወራት በእስር መቆየታቸውን ዘርዝራል። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ወንጀል ስለመፈፀም አለመፈፀሙ በዶቼቬለ የተጠየቁት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር  ዳንኤል በቀለ ( ዶ/ ር ) ምርመራው በተደረገበት ዓመት ውስጥ የጦር ወንጀልን እና በሰብዓዊነት ላይ የተቃጡ የሚያስብሉ ወንጀሎችን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች ቢፈፀሙም ተጠያቂነቱ ግን በአገር ውስጥ ሕግ መሆን እንዳለበት ይታመናል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ