1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፋር ጦርነቱ ለፈጠረው መፈናቀል የሰብዓዊ ድጋፍ ፈተና

ሰኞ፣ ጥር 9 2014

በአፋር እና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ በምትገኘው የአብአላ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚደረገው ውጊያ 40 ሺሕ ገደማ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ። የቢሮው ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹ በክልሉ አምስት ጣቢያዎች ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/45eGA
Äthiopien vom Krieg betroffene Binnenflüchtlinge aus Abala Afar-Region
ምስል Seyoum Getu/DW

በአፋር ጦርነቱ ለፈጠረው መፈናቀል የሰብዓዊ ድጋፍ ፈተና

ከትግራይ ክልል ጋር ሰፊ የአስተዳደር ወሰን ያለው የአፋር ክልል በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጠቁና ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ከተከሰተባቸው ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የኢትዮጵያ መንግስትን የሚዋጋው ህወሓት በአፋር በርካታ ስፍራዎችን ከተቆጣጠረበት ከወጣም በኋላ ከሳምንታት በፊት እንዳድስ የማያቋርጥ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ከፍቶበታል በተባለው የአፋር ክልል ዞን ሁለት ዋና ከተማ አብዓላ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ መከሰቱ ነው የሚነገረው፡፡ ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ 40 ኪ.ሜ. ገደማ ቅርበት ላይ እንደምትገኝ በሚነገረው አብዓላ በዚሁ የቅርብ ጊዜ ግጭት ብቻ ከ40 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተፈናቅለው አብዛኞቹ አሁን ላይ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ነው የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት፡፡ 

በሰመራ-አብዓላ-መቀሌ ኮሪደር ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ ብቸኛው መንገድ እንደሆነ የሚነገረው በዚህ የአፋር ዞን 2 አብዓላ ከተማ ላይ ቅጭት የተቀሰቀሰው የፌዴራሉ መንግስት ወታደራዊ ሰራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ ትዕዛዝ ባስተላለፈበት ማግስት መሆኑን ነው ኃላፊው ሚጠቁሙት፡፡ 
በአፋር በኩል ይህ የእርዳታው ኮሪደር እንዳይዘጋ በዑጋዞችና የአገርሽማግሌዎች ጭምር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የሚያወሱት የክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪው አቶ መሃመድ፤ ለአብዓላ ግጭት መቀስቀስም ህይሓትን ነው የሚከሱት፡፡ 

Äthiopien vom Krieg betroffene Binnenflüchtlinge aus Abala Afar-Region
የቢሮው ኃላፊ አቶ መሐመድ ሑሴን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹ በክልሉ አምስት ጣቢያዎች ይገኛሉ።ምስል Seyoum Getu/DW

ከህወሓት ይተኮሳል በተባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በአብዓላ እስካሁን ስለጠፋው የሰው ህይወት እና ስለደረሰው ጉዳት ስፋት የጠየቅናቸው አቶ መሃመድ ሁሴን አከባቢው አሁንም ከግጭት ስጋት ነጻ እንዳልሆነ፤ ነገር ግን ይሄንን ለመለየት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ በአፋር ለወራት በተካሄደው በጦርነቱ ምክኒያት 1.3 ሚሊየን ህዝብ ገደማ የእለት እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውንና ከዚህ ውስጥ 423 ሺው በ21 ወረዳ 17 መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡ እስካሁን ለተፈናቃዮቹ የእለት እርዳታ እየተደረገ መሆኑን በማመላከትም አሳሳቢው ተፈናቃዮቹ ለቀጣይ ስድስት ወራት መልሰው እስኪቋቋሙ በቀጣይነት ስለሚደረግ ድጋፍ ነውም ብለዋል፡፡ በአፋር በኩል አልፈው ወደ ትግራይ የሚሄዱ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች አሁን ላይ አለመኖራቸውንም ነው ኃላፊው አክለው የገለጹት፡፡ 

የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ ከገቡ አንድ ወር መድፈኑን በባለፈው ሳምንት ሪፖርቱ ያመለከተው የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ፤ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ መቀሌ ለመጓዝ የሚጠባበቁ 68 ተሸከርካሪዎች መተላለፊያ በማጣታቸው በሰመራ መቆማቸውን መግለጹ ይታወሳል።

ስዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ